PBS: Escaping Eritrea … [Read More...] about ካብ ውሽጢ ቤት ማእሰርታት ኤርትራ
የሕግ የበላይነትን የሚጋፉ ድርጊቶች ይወገዱ!
በ ጋዜጣዉ ሪፓርተር | 31 Aug, 2016
የሕግ የበላይነት ከሌለ ሕገወጥነት ይሰፍናል፡፡ ሕገወጥነት የበላይነቱን ሲይዝ ዜጎች በሰላም ወጥቶ የመግባትና የመኖር መብታቸው ለአደጋ ከመጋለጡም በላይ፣ ሥርዓተ አልበኝነት ሰፍኖ አገር የማትወጣው አደጋ ውስጥ ትገባለች፡፡ ማንም ሰው በሰላም የመኖር፣ የመሥራት፣ የመማር፣ የመንቀሳቀስ፣ ሀብት የማፍራት፣ የመሰለውን አመለካከት የማራመድና የመሳሰሉት መብቶች የሚከበሩለት የሕግ የበላይነት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ተቃውሞዎች ሳቢያ የዜጎች ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ ተቃውሞዎቹን እንደ አጋጣሚ በመጠቀም ለሕገወጥነት ተግባራቸው መጠቀሚያ ያደረጉ ወገኖችም ታይተዋል፡፡ ሕገወጥነት በመስፈኑ ምክንያት ሥጋት የገባቸው በርካታ ዜጎች የሕግ ያለህ እያሉ ነው፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች ሕዝብ ጥያቄ አለኝ ብሎ ምላሽ ሲፈልግ፣ መንግሥት በአግባቡ ተገቢውን መልስ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ ለጥያቄዎቹ ተገቢው ምላሽ በአግባቡና በጊዜው መስጠት ካልተቻለ ግን፣ የሕዝብ ጥያቄዎችን በመንተራስ ለጥፋትና ለውድመት የሚነሱ ኃይሎች ይኖራሉ፡፡ በተግባርም ታይተዋል፡፡ ግለሰቦች ጥረው ግረው ያፈሯቸውን መኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ መደብሮች፣ ማምረቻዎች፣ እርሻዎችና የመሳሰሉትን በእሳት በማጋየት መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ውድመት ታይቷል፡፡ በመንግሥት በጀት የተገነቡ መሠረተ ልማቶች፣ የመስተዳድር ጽሕፈት ቤቶችና ትምህርት ቤቶች ሳይቀሩ ወድመዋል፡፡ በተለያዩ ሥፍራዎች በግለሰቦችና በመንግሥት ተቋማት ላይ የተፈጸሙት የማውደም ተግባራት በዝርፊያ የታጀቡ በመሆናቸው የሕዝብ ጥያቄ ላልተፈለገ ዓላማ መዋሉን አንድ ማሳያ ናቸው፡፡ በየአካባቢው የሚገኙ የመስተዳድር አካላትና የፀጥታ ኃይሎች ሳይቀሩ ዓይናቸው እያየ የሚፈጸሙ ሕገወጥ ተግባራት፣ በብዙዎች ላይ ፍራቻን ከመፍጠራቸውም በላይ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እየከተታቸው ነው፡፡
ሕዝብ ጥያቄ አለኝ ብሎ ሲነሳ በአግባቡ መስተናገድ ይኖርበታል፡፡ መብትም ነው፡፡ የሕዝብ ጥያቄ እየተደራረበና የምላሽ አሰጣጥ ሥርዓቱ ዘገምተኛ ሲሆን ነውጥ ይፈጠራል፡፡ ለዝርፊያ ዓላማ ሊጠቀሙበት የሚፈልጉ ኃይሎች ደግሞ አሳቻ ሰዓትና ጨለማን ተገን በማድረግ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ሕገወጥ ድርጊቶች ሃይ ባይ ሲያጡ የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮች ይደናገጣሉ፡፡ ማንኛውም የሕዝብ ጥያቄ አንግቤያለሁ የሚል ወገን ሕገወጦች የሚፈጽሙትን ተግባር ማውገዝ አለበት፡፡ በሥርዓቱ ላይ ደስተኛ ያልሆኑ ዜጎች ሳይቀሩ አገርንና ሕዝብን የበለጠ ትርምስ ውስጥ ሊከቱ የሚችሉ አደገኛ ድርጊቶች እንዲወገዱ፣ የሕዝብ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች በሕገወጦች እንዳይጠለፉና የሕግ የበላይነት ልዕልና እንዲያገኝ መትጋት አለባቸው፡፡
መንግሥት ሕግ የማስከበር ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ከማንም በላይም ለሕግ የበላይነት መኖር መሥራት ይኖርበታል፡፡ ሕግን በማስከበር ስም ከሚፈጸሙ ሕገወጥ ተግባራት መራቅም አለበት፡፡ የሕግ የበላይነት መኖር ዋናው ጠቀሜታ ሥርዓተ አልበኝነት አደብ እንዲገዛና ዜጎች ነፃነታቸው እንዲጠበቅ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ የሚፈልግ ዜጋ ሕገወጥነት ከዴሞክራሲ ይልቅ ወደ አምባገነንነት እንደሚያመራ መገንዘብ ይኖርበታል፡፡ ‘የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው’ ዓይነት ኃላፊነት የጎደለው ተግባር እያራመዱ ስለዴሞክራሲም ሆነ ስለሰብዓዊ መብት መረጋገጥ መነጋገር አይቻልም፡፡ የሕግ የበላይነት ሲኖር ማንም ከሕግ በላይ አይሆንም፡፡ ዜጎች ሁሉ በሕግ ፊት እኩል ይሆናሉ፡፡ ብዙኃን የበላይነት ሲኖራቸው የአናሳዎችም መብት ይከበራል፡፡ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽና ተጠያቂነት ያለበት ይሆናል፡፡ የእያንዳንዱ ዜጋ መብትና ግዴታ በሚገባ ይታወቃል፡፡
የሕግ የበላይነት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተግባር እንዲረጋገጡ፣ ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል እንዲሰፍን፣ ዜጎች በመንግሥት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ቀረፃ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ውክልና እንዲኖራቸው፣ በሥልጣን ያላግባብ መገልገል እንዳይኖር፣ በሙስና መበልፀግ ነውር እንዲሆን፣ በአገር ጉዳይ ዜጎች የባለቤትነት ስሜታቸው እንዲጎለብት፣ ወዘተ የሚረዳ ፍቱን መሣሪያ ነው፡፡ በዚህ ደግሞ ከአድልኦና ከመድልኦ የፀዱ የፍትሕ ተቋማት፣ የዴሞክራሲ ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰብና የሙያ ማኅበራት ያብባሉ፡፡ ለዴሞክራሲያዊና ለሰብዓዊ መብት መረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶች ዋስትና ያገኛሉ፡፡ ይህንን ዓይነቱን የሠለጠነና ዘመናዊ አካሄድ ሐዲዱን በማሳት ሕገወጥነት እንዲሰፍንና ሰላምና መረጋጋት እንዲጠፋ ማድረግ ለአገር ታላቅ በደል ነው፡፡ የሕዝብን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች ተገን በማድረግ አገርን የሚያወድም ተግባር ውስጥ መሳተፍ ሕገወጥነት ነው፡፡ ለአገርና ለሕዝብ የማይጠቅም ድርጊት ነው፡፡
አገር መመራት ያለበት በሕግ የበላይነት ነው፡፡ በሕግ የበላይነት ስም የሚፈጸሙ አጓጉል ድርጊቶች ሕዝብን ሲያስቆጡና አመፅ ሲቀሰቅሱ እየታየ ነው፡፡ በዚያው ልክ የሕዝብን ጥያቄ እየታከኩ ለዝርፊያ ያቆበቆቡ ወገኖችም ውድመት እያደረሱ ነው፡፡ በተቃውሞው ምክንያት እየደረሰ ካለው ጥፋት በተጨማሪ፣ ለዝርፊያ በተደራጁ ኃይሎች የሚፈጸመው አሳዛኝ ድርጊት ብዙዎችን እየጎዳ ነው፡፡ እነዚህ አሳቻ ሰዓትና ጨለማን ተገን የሚያደርጉ ኃይሎች እርሻዎችን፣ ጎተራዎችን፣ መጋዘኖችንና የመሳሰሉትን ከመዝረፍና ከማቃጠል በተጨማሪ በሰው ሕይወት ላይም አደጋ ደቅነዋል፡፡ በአንዳንድ ሥፍራዎች በግልጽ ገንዘብ አምጡ ያለበለዚያ እናቃጥላለን እያሉ ይዝታሉ፡፡ አቤት ሲባል የሚያዳምጥ የመስተዳድር አካል የለም፡፡ በስንት ሙከራ ጉዳያቸው ወደ ሕግ የደረሰም በሰበብ አስባቡ ችላ እየተባለ በአቤት ባዮች ላይ ዛቻ ይሰነዘራል፡፡ የሕግ የበላይነት ሳይኖር ሲቀር ሕገወጥነት ይነግሥና ዜጎች ለበለጠ ጥቃት ይጋለጣሉ፡፡
የሕግ የበላይነት ዜጎች በሕግ ጥላ ሥር መብታቸው ተከብሮ እንዲተዳደሩ ብቻ ሳይሆን፣ ማንም ሰው በሥልጣኑ ወይም በሀብቱ ምክንያት ከሕግ በላይ እንዳይሆን ማለት ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ዜጎች በምንም ዓይነት ሁኔታ ለጥቃት እንዳይጋለጡ፣ የሚወጡ ሕጎች በሙሉ መብቶቻቸውን እንዲያስከብሩ፣ እነሱም በአግባቡ ግዴታቸውን እንዲወጡ፣ ፍትሕ እንዲሰፍንና የዜጎች ሁለንተናዊ መብቶች እንዲከበሩ ይጠቅማል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባውም ሆነ አገር ሰላም የምትሆነው የሕግ የበላይነት ሲሰፍን ብቻ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት በሌለበት አምባገነንነትና ፀረ ዴሞክራቲክ ድርጊቶች ይበዛሉ፡፡ የሕዝብን ቅሬታ በማባባስ ወደ አመፅና ብጥብጥ ይመራሉ፡፡ ከሕግ የበላይነት በተቃራኒ የሚፈጸሙ ድርጊቶች በሙሉ ለአገር አይበጁም፡፡ እንዲህ ዓይነት ለሕዝብ የማይጠቅሙ ድርጊቶችን በቸልተኝነት ማለፍም የድርጊቶቹ ተባባሪ መሆን ነው፡፡ የሕግ የበላይነትን የሚጋፉ ድርጊቶች ይወገዱ የሚባለው ለዚህ ነው!