PBS: Escaping Eritrea … [Read More...] about ካብ ውሽጢ ቤት ማእሰርታት ኤርትራ
ምላሽ ለሌ/ጄ ፃድቃን ገ/ተንሳይ “የሀገራችን ፖለቲካ ሁኔታና የመፍትሔ ሃሳቦች” ጽሁፍ
ነሲቡ ስብሐት፤ ከሰሜን አሜሪካ | ሐምሌ 20 ቀን 2008 ዓ.ም. (July 27, 2016) | ኢትዮጵያ ዛሬ፣
ለመፍትሔው መፍትሔ የወያኔ/ህወሓትን ዕድሜ ለማራዘም በሌ/ጄ ፃድቃን ገ/ተንሳይ የመፍትሔ ሃሳቦች [(የሌ/ጄ ፃድቃን ገ/ተንሳይን ጽሁፉ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)]
እነሆ 17 ዓመት በበረሃ 25 ዓመት በመንግሥት ሥልጣን የተቆናጠጠው ወያኔ ዛሬ የሥልጣን ዘመኑ ማብቂያው የመጨረሻው መጀመሪያ ላይ ደርሷል። በትግሉ ላይ ነበርን ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ አመራር እርከን ላይ ነበርን የሚሉ የወያኔ ባለሥልጣን፤ የድርጅታቸውን 17 ዓመት የትግል ጉዞ አብረው ፕሮግራም ሲነድፉ፣ ፖሊሲ ሲያወጡ፣ የትግራይ ነፃ አውጪ ብለው በዘር ሲደራጁ፣ የአማራ የበላይነት ሰፍኗል ብለው አማራ ላይ ሲያነጣጥሩ፣ የብሔር/ብሔረሰቦች መብት እስከመገንጠል ብለው የዘር ፖለቲካ ሲያራምዱ፣ ኤርትራ በኢትዮጵያ ቅኝ ተይዛለች ብለው ከሻዕቢያ ጋር ለኤርትራ ነፃነት ሲታገሉና ሲያታግሉ የነበሩ ዋናው የድርጅቱ አመራር ባልደረባ፤ ዛሬ የወያኔ ወንበር እንዳበቃለት ሲገለጥላቸው “ዕድሜውን እንዴት እናራዝመው?” “ትንታኔአቸውን” አስነብበውናል።
እኚህ ሰው በ1983 ዓ.ም. ወያኔ ቤተ መንግሥቱን ከተቆጣጠረ ጊዜ ጀምሮ አነጣጥረው የመጡበትን አማራ ያገለለ የሰኔው 1983 ዓ.ም. ጉባዔ ተካሂዶ በመንግሥት ደረጃ ኤርትራ ትገንጠልልኝ ብሎ ለተባበሩት መንግሥታት ዕውቅና ከመስጠት አልፎ “ኢትዮጵያ ወደብ አያስፈልጋትም” በማለት አሰብን ያስገነጠሉ፣ በበደኖና አርባጉጉ አማራ ከገደል ሲወረወር፣ ሲጨፈጨፍ ድርጅታቸው ህወሓትና መንግሥታቸው ኢህአዴግ/ወያኔ ትክክለኛና አስፈላጊውን አቅጣጫ እየተጓዘ እንደሆነ ያጨበጨቡና ያስጨበጨቡ ዛሬ እመጨረሻው ሰዓት ላይ የዘረኛውንና የሀገር አጥፊው ድርጅታቸው ዕድሜ እንዴት ይራዘም ዘንድ በማር የተለወሰ “ብዕራቸውን” ይዘው ብቅ ብለዋል።
ውድ አንባብያን! ይህንን ጽሁፍ ላቀርብ የተገደድኩት ከቅርብ ጊዜ ክስተቶች ትምህርት እየተወሰደ ዳግም ስህተት እንዳይሠራ ነው። “እኛ ከሌለን ኢትዮጵያ አበቃላት” የመለስ ዜናዊ አባባልና የእሱን “ራዕይ” አስፈፃሚዎች ዛሬ “ካንገዳገዳችሁን ሀገር ትፈራርሳለች” ባዮችን ማስፈራሪያ “በሀገራችን አትምጡ፣ ህዝባችንን እናውቀዋለን፣ በማንነታችን እንተማመናለን” በሚል ስሜት በተፋፋመ መልኩ በእስላም ወገኖቻችን በኩል የተጀመረው የመብት ጥያቄ፣ የጋምቤላ ወገኖቻችን ትግል፣ በኦሮሞ ወገኖቻችን በኩል የተነሳው እንቅስቃሴ አሁን በቅርቡ በአማራው በኩል የተስፋፋው ትግል፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ወገናችን የረዥም ጊዜ ተጋድሎ ሁሉም አንድና አንድ ብቻ መሆኑን ማስገንዘብ ይኖርብናል። የወያኔ/ህወሓት አገዛዝ እንዲያበቃለት የተደረገ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ጅምር፣ መብቱን የተነፈገ ህዝብ እንቅስቃሴ፣ የ25 ዓመት አገዛዝ የፈጠረው የተራበ ህዝብ ብሶት።
ኢትዮጵያን ለኢትዮጵያውያን ለማድረግ ይነገረን ከተባለ ኦሮሞውና አማራው አይደለም የትግሬው ብሔረሰብም ወደ ፀረ-ወያኔ ትግሉ እንደሚቀላቀል መናገር ይቻላል። ለዘመናት አብረው ከኖሩት ህዝባቸው ጋር ነገም ያላቸው ወገናቸው ወያኔ ሳይሆን የኢትዮጵያ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ጉራጌ፣ ደቡብ ህዝብ መሆኑን ተረድተው በስማቸው ሀገር ላይ ለደረሰው ጥፋት ሰልፋቸውን ማሳመር ያለባቸው ወቅት አሁን ነው። እትብታቸው የተቀበረችበት ኢትዮጵያን ከወያኔ ጋር ሊረግጡ አይገባቸውም።
የወያኔ ሕገ መንግሥት
ከሌ/ጄ ፃድቃን ገ/ተንሳይ “የሀገራችን ፖለቲካ ሁኔታና የመፍትሔ ሃሳቦች” ጽሁፍ ልጥቀስ
“ህዝባዊ ተሳትፎ በተደረገበት መንገድ የጸደቀ ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት አለን።” ገጽ 2
“ሕገ መንግሥቱ በህዝባዊ የትጥቅ ትግሉ ውስጥ አብዮታዊና ዴሞክራሲያዊ መንፈስ የተላበሰ ኢህአዴግ በሚመራው መንግሥት እንዲኖር የሚፈለገውን የመንግሥት አሰራርና ባህርይ መለኪያ (Standard) ይሆናል ብለን ያስቀመጥነው የትጥቅ ትግሉ ድሎች መቋጫ ነበር እላለሁ።” ገጽ 2
“… ቢያንስ ሕገ መንግሥቱ እውቅና የሰጣቸው መብቶች ሳይሸራረፉ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆኑ ይፈለጋል።” ገጽ 3 የጥቅሶቹ መጨረሻ።
ሌ/ጄ ፃድቃን የጽሁፋቸው ዋናው ትኩረት “በዴሞክራሲያዊ” መንገድ የጸደቀውን የወያኔን ሕገ መንግሥት ተቀብለን እንድንጓዝ ትኩረት ሰጥተውት ይደግሙልናል። በሀገሪቷ ላይ ዛሬ ለተከሰተው ውጥንቅጥ፤ አሁን በአገዛዝ ላይ ያለው ህወሓት እና ሕገ መንግሥቱ መሆኑን እንዳልዘነጉት እርግጠኛ ነኝ። ትግሉ ሁለቱም፦ ማለትም የወያኔ አገዛዝም ሆነ ሕገ መንግሥቱ መወገድ ላይ መሆኑን በደንብ ሊረዱት ይገባል።
የወያኔ ሕገ መንግሥት የመንግሥት አወቃቀርን በአግባቡ ያላስቀመጠ ከመሆኑም በላይ ለአለፉት 25 ዓመታት አፋኝና ገዳይ የሆነ ሕገ መንግሥት ነውና ከወያኔ ውድቀት ጋር ማብቃት ያለበት ሕገ መንግሥት ነው።
አዎ! ኢትዮጵያ ማንም ሥልጣን ላይ ሲወጣ የማይሽረው ለትውልድ የሚተላለፍ ሕገ መንግሥት ያስፈልጋታል። ይህ ግን አንድ አምባገነን መንግሥት ለይስሙላና በተግባር ባዶ የሆነ የዴሞክራሲያና የሰብዓዊ መብቶችን እየጠቀሰ በመርዘኛ ቁልፍ የከተበው መሆን አይገባውም።
ጄኔራሉ በጽሁፋቸው ወያኔ እየተንገዳገደና ብልሹ አገዛዝ መሆኑን የተቀበሉ ይመስላሉ። ሆኖም በኢትዮጵያ የህዝቧን አንድነት ያስጠበቀ መንግሥት ለእሳቸውና ለመሰሎቻቸው የድሮው ነፍጥ አገዛዝ ነውና ቀድመን ወያኔን በሌላ መልኩ እናድሰው ዘንዳ መልዕክታቸው በየአካባቢው የተነሳውን ህዝባዊ እንቅስቃሴ ውሃ ይቸለስበት ዘንድ ለአባሎቻቸው ሊጠቁሙ የፈለጉ ይመስላል።
የሕገ መንግሥቱን ዴሞክራሲያዊነትና ቀጣይነት ሲገልጹ በማያሻማ መልኩ በሦስት ገጽታ ሊታይ ይችላል።
የመጀመሪያው በወያኔ ሕገ መንግሥት የሰፈረው አንቀጽ 39 የብሔር/ብሔረሰቦችን መብት እስከመገንጠል የሚለውን ይጠብቅላቸውና ካልሆነም ሀገር ልትበታተን እንደምትችል ሊነግሩን ሲፈልጉ በዚህ መልክ ያስቀምጡታል፤ “ሕገ መንግሥቱ እውቅና የተሰጣቸው መብቶች ሳይሸራረፉ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆኑ ይፈልጋል።” (ሥርዝ የተጨመረበት) አጀብ ነው!
ጄኔራሉ “ሙሉ በሙሉ” ሲሉ በውስጠ ታዋቂ መገንጠልን እንደሆነ ልብ በሉ። ሊያስተላልፉ የፈለጉት መልዕክት ግልጽ ሊሆን ይገባዋል። ዛሬ በተቃዋሚነት ወያኔን ከሚታገሉት የብሔር/ብሔረሰብ ድርጅቶች መካከል እንደ ኦነግ፣ ኦብነግ ዓይነቶቹ በተደጋጋሚ አንቀጽ 39ን እንደሚደግፉ ይገልጻሉ። ማለትም በእነሱ አባባል ኦሮሚያና ኦጋዴን ሶማሊያ ከኢትዮጵያ የመገንጠል ፍላጎታቸው ስኬታማ ይሆን ዘንድ ይህ አንቀጽ ይጠቅማቸዋልና። እዚህ ላይ ነው የህወሓት መሪው መልዕክት። ይህ ሕገ መንግሥት ሳይናድባችሁ ኑ እና ከእኛ ጋር ተባበሩ መልዕክታቸው።
ሁለተኛው የሌ/ጄ ፃድቃን መልዕክት መሪያቸው መለስ ዜናዊ በተደጋጋሚ ይል የነበረው “እኛ ከሌለን ኢትዮጵያ ትበታተናለች” የሚለው ማስፈራሪያ ነው። ይህ ሕፃን ለማስፈራራት “አያ ጅቦ መጣልህ” ኩምክና ወደ ጎን ቢያደርጉት መልካም ነው። ከመነሻችሁም ኢትዮጵያ ለእናንተ ተረት ተረት የሆነች፣ ሰንደቅ ዓላማ ጨርቅ የሆነባችሁ፣ የአክሱምን ሐውልት ድንጋይ ያላችሁ፣ አድዋ ለአማራው ምኑ ነው ያላችሁ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ላይ የዘመታችሁ ለመሆኑ ሥራችሁ መስካሪ ነው። መቼ የሀገርን አንድነት ጠባቂ ሆናችሁና ነው ስለ ኢትዮጵያ አንድነት የምትሰብኩን። ገና እንደገባችሁ በሻዕቢያ መሪነት ኤርትራን ያስገነጠላችሁ፣ አሰብን የሰጣችሁ በቀጣይነትም የባድሜን ጉዳይ ያዳፈናችሁ አይደላችሁምን?
አሁን በሀገሪቷ የተነሳው የመብትና የማንነት ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የኢህአዴግ/ህወሓት ሥርዓት ማብቃት ሳይሆን መወገድ ጉዳይ ነው። የወያኔ ሥርዓት መወገድ ሲባል የወያኔ ሕገ መንግሥት መወገድ ማለት ነው። የወያኔ ሕገ መንግሥት መወገድ ሲባል አንቀጽ 39 መሠረዝና አዲስ ሕገ መንግሥት ማርቀቅ ማለት ነው። የአንቀጽ 39 መሠረዝ ሲባል በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሁሉንም ዜጐቿን መብት ያስጠበቀች አንድ ኢትዮጵያ ማለት ነው። ይህ ነው ትግሉ!
የጄኔራሉ ማስፈራራት ግልጽ ሊሆን ይገባል የእኛን ሕገ መንግሥት ተቀብላችሁ፣ ኢህአዴግን መክራችሁ ተጓዙ ማለት፤ አለበለዚያ ነገ አንቀጽ 39 ተገን አድርገን “በሕጋዊ” መንገድ ትግራይ ከኢትዮጵያ ትገነጠላለች ነው አጭሩ መልዕክት። ለዚህ የጽሁፎ መልዕክት ማንም አይደነግጥም። ገና ከጅምሩ ሀገሪቷን ለመበታተን አቅዳችሁ የሰነቀራችሁት አንቀጽ ነውና የኢትዮጵያ ህዝብ ለዚህ አዲስ አይደለም። ኢትዮጵያ የግዛት እና የህዝቧን አንድነት ጠብቃ ለትውልድ የምትሆን ሀገር ትሆን ዘንድ የወያኔ ሥርዓት ማብቃት አጠያያቂ አይደለምና ትግሉ ለዚህ መሆኑን ይረዱት።
በጽሁፍዎ የወያኔ ፀረ-ዴሞክራቲክ ባህሪ የታየዎት ዛሬ ነው ሲሉ ትንሽ ዕፍረት ቢኖር ጥሩ ይመስለኛል። ገና ሜዳ ሳላችሁ በዕርቅ ስም የቀበራችኋቸው ወንድሞቻችሁ የዴሞክራሲ ጉዞ ገጽታ ነበርን? የሐውዜን ትርይት የዴሞክራሲያዊ ትግል ውጤት ነበርን? የበደኖ ጭፍጨፋ፣ የ97ቱን ምርጫ አስታኮ በትንሹ 196 ንፁሐን ደም፣ በግለሰብ ደረጃም ይኬድ ከተባለ የፀጋዬ ደብተራው ግድያ፣ የአሰፋ ማሩ ግድያ፣ የፕሮፌሠር አስራት ወልደየስ የረቀቀ ግድያ፣ ወዘተ ወዘተ የወያኔና የሕገ መንግሥቱ ዴሞክራሲያዊ ገጽታ ነበርን? ወደ ዝርዝር ጉዳይ ሳይገባ ከራሳችሁ የወጡ አባሎቻችሁ ብዙ ብለዋል ብዙ ጽፈዋል። ህወሓት/ወያኔ ምን ያህል የማፍያ ድርጅት እንደሆነ በቅርቡ አቶ ገብረመድህን አርኣያ ድምፃቸውን አሰምተዋል። አባሎቻችሁን እንዴት እያሰቃያችሁ እዚህ እንደደረሳችሁ፣ “የባዶ ስድስት” እሥር ቤቶቻችሁን ጉድ በሁለት ክፍል በኢሳት አስደምጠውናል። (ለማድመጥ የማጫወቻ ቁልፎቹን ይጫኑ!)
ክፍል አንድ (Part 1. 11 May 2016)
ክፍል ሁለት (Part 2. 15 May 2016)
እውነት ለመናገር እናንተ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ አይደለም ወከልን ለምትሉት የትግሬ ብሔረሰብ የምትሆኑ አይደላችሁም። በእርግጥ ወያኔ አንድ የሚወክለው ባህሪ አለ የ“ጥፋት ዘመን”። ከተሳካላችሁ ሰይጣናዊ ሃሳባችሁ ብዙ ነው። አዎ! ኢትዮጵያን በዘር፣ በኃይማኖት ልታመሰቃቅሉ ብዙ ጥራችኋል። ዛሬ አድማሱን አስፍቶ መጣ እንጂ ኢትዮጵያ ላይ ጥይታችሁ ያነጣጠረው ገና ከጅምሩ ነው። አብረው በጫካ ያረቀቁትን ጉድ የያዘውን የህወሓት ማንፌስቶ እኮ ነው ዛሬ ተግባራዊ እያደረጋችሁ ያላችሁት።
ሦስተኛው ወያኔ/ኢህአዴግን ዕድሜ ማራዘሚያ ነጥቦ ጐላ ብሎ ይታያል። ይኸውም የምርጫ ፖለቲካና እንደገና የሌሎች ተቃዋሚዎች በነፃ የመንቀሳቀስ ጉዳይ ነው። እዚህ ላይ በአጭሩ ከወያኔ ጋር የምርጫ ፖለቲካ አክትሟል። ልንገርዎና አሁን ያለው ተቃዋሚ ኃይል ምንም ቅስቀሳ ሳያደርግ በመላዋ ኢትዮጵያ “ወያኔን/ኢህአዴግን ወይስ ሌላ” ብላችሁ በነፃነት ድምጽ ብታሰጡ እውነት … እውነት እልዎታለው በትግራይ ምድር እንኳ ድጋፍ አታገኙም። እጅግ ተጠልታችኋል። እጅጉን ያንን ምስኪንና መከራ ያልተለየውን ህዝብ አስመርራችኋል። በባህላችን ተደርጐ የማይታወቅ ሕፃናትና ወጣቶች ከቆሻሻ ገንዳ ምግብ እንዲለቃቅሙ አድርጋችኋል። ትርፍራፊ ጉርሻ በሠልፍ እንዲጎረስ ዕድገት አምጥታችኋል። ስንት አዛውንቶችን ልጄን አሰኝታችኋል። መለስተኛ ገቢ ያላቸውን ሠራተኞች በቀን አንዴ ያውም ከሳምቡሳና የተቀቀለ ድንች ያልዘለለ ተመጋቢ አድርጋችኋል፣ መብራት በፈረቃ፣ የውሃ ያለህ ተሰላፊው፣ ይህ ነው የየዕለት መከራው። ለኢትዮጵያ ህዝብ 25 ዓመት የአገዛዝ ተመክሯችሁ ይህ ነው። እና በአጭሩ በሀገርና ህዝብ ተጠልታችኋል።
የጄኔራሉ ዕድሜ ማራዘሚያ ክኒን ይህ ነው። ዛሬ ድርጅታቸው ህወሓት/ኢህአዴግ የደረሰበት የመጨረሻ ደረጃ ለእሳቸው ብቻ ሳይሆን ለድርጅቱ በጠቅላላ ወለል ብሎ እየታየ በመሆኑ፤ ዘዴ ያለው አማራጭ ማቅረብና ይህን የመጣ ህዝባዊ ማዕበል በማቀዝቀዝ ጥቂት ዓመታት የዝርፊያ ዘመን ይፈልጋሉ። የዝርፊያ ያልኩት እነኚህ ሰዎች በምንም መልኩ ከስህተታቸው ትምህርት ቀስመው የሚስተካከሉ አይደሉምና ነው። ለዚህም አካሄዳቸው በተለይ ከ1997 ዓ.ም. የመጣባቸውን የምርጫ ማዕበል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካሽመደመዱ በኋላ አቅጣጫቸውን “ልማታዊ መንግሥት” የሚል ስያሜ በመስጠት ተንቀሳቅሰዋል።
ኢህአዴግ/ህወሓት ያልገባው ቢኖር ልማትና ዕድገት በአንድ ሀገር ውስጥ ያለ ዴሞክራሲያ መብት ተግባራዊ እንደማይሆን ነው። ህዝብ መብቱን ሲጠይቅ እየገረፉ በልማትና ዕድገቱ አግዘኝ ማለት አይሠራም። ውጤቱ ውድቀት ነው። ለዚህም ነው በ10 ሚልዮን የሚቆጠር ህዝብ ለረሃብ መጋለጡ “የልማታዊ መንግሥት” ውጤት የሆነው። የኦሮሞን ልጆች በየእሥር ቤቱ እየወረወሩ፣ እያሰቃዩና እየገደሉ “የብሔር/ብሔረሰቦች ቀን” ብለው ቢጮኹ “ኢጆሌ ወያኔ አበደች” ያሰኛል። በጥቅሉ የዜግነት መብትን እያፈኑ ልማትም ሆነ ዕድገት የትም አይደርስም። ቅድሚያ የልማቱም የዕድገቱም ምሰሶ የሆነውን የኢትዮጵያ ህዝብ መብት ለይስሙላ በተፃፈው ሕገ መንግሥት ሳይሆን በተግባር ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው። ሀገሩን ያገኘ ህዝብ ለሀገሩ መሥራት አይደለም ሕይወቱን ይሰጣልና።
በአዲሱ ዕቅድ መሠረት “ልማታዊው ኢህአዴግ” መንገድ ሰርቷል፣ በርካታ ሕንፃዎች ተገንብተዋል፣ የከተማ ባቡር ዘርግቷል፣ ዐባይን ለኃይል ማመንጫነት ለመጠቀም ግንባታ ጀምሯል። እነኚህ የጠቀስኳቸው በሞላ በአንድ ሀገር ለሚካሄድ የልማት ጎዳና ኢንፍራስትራክቸር (ሲጠቃለሉ መጓጓዣ፣ ኃይል ምንጭ፣ መገናኛ ሲባሉ) ያልተካተቱም አሉ። ሕክምና፣ ትምህርት ቤት፣ መብራት አቅርቦት፣ ውኃ የመሳሰሉት። እነኝህን መሠረት አድርጎ ባለ ሀብቱ ካፒታሉን ያንቀሳቅሳል፣ የተለያዩ የልማት አውታሮች ይዘረጋል። በኢትዮጵያ ያለው ግና እንደስሙ ወያኔአዊ ልማት ነው። ያሉት ትላልቅ ኩባንያዎችም ሆኑ፣ ፋብሪካዎች እንዲሁም በሀገሪቷ የሚካሄዱ የአስመጪና ላኪ እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ የተያዙት በወያኔው ኤፈርት ወይም በውጭ ሀገር ዜጎች ነው። ዛሬ ወያኔ በሀገራችን ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ የበላይነቱን ተቆጣጥሯል። ከዘረፉት ንዋይና ከባዕዳን ከሚቸራቸው ዕርዳታ በመጠቀም አብዛኛውን የሀገሪቷን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በመቆጣጠራችን ከእንግዲህ ማንም ሊመጣብን አይችልምና ይህን የኢኮኖሚ የበላይነት ተገን በማድረግ ፖለቲካውን መቆጣጠር እንችላለን የሚል አቅጣጫ የወያኔዎች አካሄድ ይሆን ዘንድ የተጠና የጄኔራል ፃድቃን መልዕክት ነው።
አሁን በየአቅጣጫው የተፈጠረውን አመጽ ለማለዘብ ከማህላቸው ወያኔን እየጎነተለ አቃቂር የሚያወጣ አንድ ሰው (ሌ/ጄ ፃድቃን) ጽሁፍ ይጽፋል፣ አራጋቢዎች ያደምቁታል፣ ትግሉ አልገፋ ያላቸው ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች “እስቲ እንያቸው” ድምፃቸውን ያስተጋባሉ ወይም “ጥሩ ሃሳብ ነው” ያሉት እጃቸውን ለኢህአዴግ ይሠጣሉ። መታገስ አለባቸውና እስከ መጪው ምርጫ ይህንኑ ሲያላዝኑና በሀገር ቤት የሚንቀሳቀሰው ህዝብ ትግል ላይ ውኃ ሲቸልሱ ወያኔ እፎይታ ያገኛል።
በጥቅሉ የጄኔራሉ/ኢህአዴግ አማራጭ ዕቅዶች፦ 1. ሀገርና ህዝብ በዘርና በኃይማኖት በማተረማመስ የእርስ በርስ ግጭት በመፍጠር መበታተን፣ 2. በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 መሠረት የትግራይ ነፃነት መታወጅና ከአመቸም ለኦሮምያና ለምሥራቅ ኢትዮጵያ (ኦጋዴን) በአንቀጹ መሠረት የመገንጠል መብታቸው መከበርና ሌላው 3. በኢኮኖሚው የበላይነት በመተማመን በጄኔራሉ/ወያኔ አባባል “መለስተኛ” ስህተቶቻቸውን በመቀበል የምርጫ ትያትር በማለት ዕድሜ ማራዘም።
ከዚህ ውጭ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት፣ ስለ ዴሞክራሲያዊ መብት፣ በየእሥር ቤቱ ስለሚማቅቁ ወገኖች፣ ስለ ኢትዮጵያዊነት ብሔራዊ ስሜት መታደስ፣ ስለ ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ስለ ቅርሶቿ፣ ስለ ህዝቧ አኩሪ ባህል፣ ሀገሬ ኢትዮጵያ ዘማሪ … ለወያኔ ትላንትም፣ ዛሬም ሆነ ነገ ቦታ አይኖረውም።
የዘር ፖለቲካ
“ከፖለቲካዊ ሥርዓቱ ስንነሳ የፖለቲካዊ ሥርዓቱ ዋነኛ ችግር በገዥው ፓርቲና በመንግሥት ያለው ግንኙነት ፈጽሞ ጠፍቶ ገዥው ፓርቲና መንግሥት አንድ ከመሆናቸው የሚመነጭ ነው።” ገጽ 3 ይሉናል ተጋዳላይ ፃድቃን።
ምነዋ! ይህ ጉዳይ እኮ 25 ዓመት ሙሉ አብሮት የተጓዘ ነው። እርሶን የመሰለ በትግልም፣ በዕውቀትም ተመክሮ ያለው አንድ ልጅ ተወልዶ ዩኒቨርሲቲ ጨርሶ ትዳር እስኪይዝ በአለው ዕድሜ ምነዋ አልታይ አልዎት።
በኢትዮጵያ ለአለፉት 25 ዓመታት ፓርቲም፣ መንግሥትም፣ ምክር ቤትም፣ ዳኛም፣ ሕገ መንግሥትም፣ ሕግ አውጪም፣ አስፈፃሚ፣ ተርጓሚ፣ ነጋዴም … ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መሆኑን 100 ሚልዮን ህዝብ ይመሰክረዋል። እናም የፖለቲካ ሥርዓቱ ዋነኛ ችግር ወያኔ ህወሓት ነው አራት ነጥብ። በመሆኑም ከነ ሙስናው፣ ከነ ተዘበራረቀና ልቅ ካጣው ቢሮክራሲያዊ አሠራሩ፣ ከነ ዘረኝነቱ፣ ከነ ሌብነቱ መወገድ ያለበት ሥርዓት ነው። ለኢትዮጵያ ሀገራችን አንድነትና ለህዝቧ ነፃነት ሲባል ወደ መቃብር መወርወር ያለበት ድርጅት ቢኖር ህወሓት ነው።
ሌ/ጄ ፃድቃን ስለ መንግሥት አወቃቀር ከ17 ዓመት የሜዳ ትግላቸውና ከ25 ዓመት አመራራቸው በኋላ ትንታኔ ሊሰጡን ይፈልጋሉ።
ህወሓት አፈጣጠሩ በዘር ላይ የተሞረከዘ አገዛዝ ነበር። ነውም። ይህ ለማንም ግልጽ ነው። “ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ” ብሎ የተነሳ ድርጅት አባላቱ ሙሉ በሙሉ የትግራይ ልጆች እንደሚሆኑ ልንጠራጠር አይገባንም። ለትግራይ ነፃነት የሚታገል አማራው፣ ኦሮሞው፣ ጉራጌው፣ ሐድያው፣ ጋምቤላው፣ ደቡቡ በአጠቃላይ ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ላይ ያነጣጠረ ትግል በመሆኑ በተዋጊነትም ሆነ በአባልነት አያስገባም። በአንድ ጠባብ ዘር ነውና የተደራጀው። ለዚህም ነው ወያኔ ከጅምሩ ከክልላችን ውጡ በሚል ሕብረ ብሔር ድርጅቶች ላይ እንደ ኢሕአፓና ኢዴኅ ውጊያ ከፍቶና ከባድ ጉዳት አድርሶ ያስወጣው።
ምንም ይባል ምን ይህ በዘር የተደራጀ ድርጅት በለስ ቀንቶት ከደርግ ውድቀት በፊት ትግራይን ሙሉ በሙሉ ሊቆጣጠር ችሏል። ከዚህ በኋላ ነው የህወሓት ሌላው ገጽታ። ወያኔ ህወሓት በሚለው ስያሜው መላ ኢትዮጵያን ሊያስተዳድርም ሆነ ሊዘልቅ እንደማይችል በመገንዘቡ ሌላ ኢትዮጵያዊነት ጭምብል ማጥለቅ በማስፈለጉ የተለያዩ የዘር ድርጅቶችን በማሰባሰብና እራሱም ጠፍጥፎ በመሥራት ወያኔን/ህወሓት ማዕከል ያደረገ የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) የተመሠረተው። “ሲሉ ሰምታ …” እንደሚባለው ተረት “በትጥቅ ትግሉ ወቅት የአፋር፣ የቤንሻንጉል፣ የጋምቤላ፣ የኦሮሞ፣ የአማራ ህዝቦች ከትግራይ ህዝብ ጋር ሆነው በጋራ የተዋደቁት የተለየ ሚስጢር ስለነበረን አይደለም።” ገጽ 15 ብለው ሲነግሩን እጅጉን ሊያፍሩ ይገባዎታል።
አዎ ኢህአዴግ በሚለው የዘረኝነት ጭምብል ሌላውን የሀገሪቷን ግዛት ዘልቃችሁ ለሥልጣንም በቅታችኋል። የአፈጣጠራችሁ ታሪክ ግና ለኢትዮጵያ ብላችሁ አልነበረም አሁንም አይደለም።
በሀገራችን ኢትዮጵያ በዛሬው ወቅት ዘርን ተገን እያደረገ የተነሳው እንቅስቃሴ ሊያስደነግጠን አይገባም። ምክንያቱም አገዛዙ በዘርና በኃይማኖት ከፋፍሎናልና። የዘር አከላለልና ዘርን ያማከለ ፖለቲካ ትግሉም ዘርን ተገን ማድረጉ ጎልቷልና። ወያኔ የጫረው እሳት እራሱን ሊለበልበው ከቦታልና።
የኦሮሞ ልጆች በወያኔ 25 ዓመት አገዛዝ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ከቶም እንዳይሰሙ፣ ሰንደቅ ዓላማዋን እንዳያውቁ፣ ቋንቋዋን እንዳይናገሩ፣ ባህሏን እንዳያንጸባርቁ ተደርገው ያደጉ ዛሬ በትንሹ ከ35 ዓመት በታች ያሉት ወጣቶች በምን ሥነ ልቦና እንደተገነቡ መገንዘብ ቀላል ነው። ወያኔ የበረዘው መላ ኢትዮጵያን ነው። እንኳን እኚህ በወያኔ ዘመን የተወለዱት የዛሬ ወጣቶች ይቅርና እኛ የትላንቶቹ ሳናስበው የዘር ፖለቲካ አባዜ ውስጥ የተዘፈቅን ስንቶቻችን ነን? አምነንበትም ሆነ ሁኔታዎች አስገድደው በዘር ፖለቲካ፣ በኃይማኖት የተሳሳበው ቀላል አይደለም። ይህን አደገኛ አመጣጥ ለመመከትና ኢትዮጵያዊነት ብሔራዊ ስሜትን ለማጉላት የአንዱ ዘር ችግር የሌላውም ቁስል መሆኑን ከተገነዘብን ዘንዳ የወያኔን መርዘኛ ሕገ መንግሥት የማንንድበት ምክንያት አይኖርም። ይህ ሲሆን በወያኔ መቃብር ላይ ኢትዮጵያ ታብባለች። “ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!” ለማለት የደፈረ “ህወሓት/ወያኔ ይውደም!” ብሎ መነሳት ይኖርበታል።
ዝርፊያና ተጠያቂነት
ሌ/ጄ ፃድቃን በጽሁፋቸው ስለ ተጠያቂነት አንድም ሊጽፉ አልፈለጉም። አንድ መንግሥት አስተዳድራለሁ በሚለው ሀገር በዘመኑ ለሠራው ሕይወት ማጥፋት፣ ያለ አግባብ ብልጽግና፣ ዝርፊያ ወዘተ ይጠየቃል።
እዚህ ላይ ነው ጄኔራሉ የሚመፃደቁበት ሕገ መንግሥት ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ማዕከል ያደረገ መንግሥታዊ አወቃቀር ስለሌለው ዛሬ የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ በሙስናና በዝርፊያ የተዘፈቀ ሆኖ የምናየው።
ሰፋ ያለ ትንታኔ ላይ ባይገባም የወያኔ መንግሥት ባለሥልጣናት ዛሬ ባለ ሚሊዮኖች፣ ባለ ፋብሪካዎች፣ በርካታ ተንቀሳቃሽና ቋሚ ባለ ንብረቶች ናቸው። እጅግ በበርካታ ሚልዮን/ቢልዮን የሚቆጠር ጥሬ ዶላር በተለያዩ የዓለም ባንኮች እንዳዛወሩ ይገመታል። በልማት ስም የኢትዮጵያን ለም መሬቶች ለተለያዩ ኩባንያዎች ቸብችበዋል፣ በሊዝ ስም ሰጥተዋል። በፍቅርና በዝምድና አብሮ የኖረውን መንደርተኛ የከተማ ነዋሪ ዕድገት በሚል ፈሊጥ አውላላ ሜዳ ላይ እየጣሉ በምትኩ ቦታውን ለተለያዩ የውጭ ባለሀብቶች ቸብችበዋል። በጥቅሉ የሀገርን አንጡራ ሀብት ዘርፈዋል። ጉቦኝነት ከመቼውም በላይ በሀገሪቷ ሥር ሰዷል። ዘርን ማዕከል ያደረገ አድልዎ ተንሰራፍቷል። “ሕገ መንግሥቱ በአጎናጸፋቸው መብት” መሠረት ዛሬ በሚልዮን የሚቆጠር ፕሮጅክት የሚያንቀሳቅሱ ዘራፊዎች ብልጽግና ነው የሀገሪቷ ዕድገት እየተባለ የሚሰላልን። እና ጄኔራል ይህን ፀሐይ የሞቀውን ሀገር ያወቀውን ሐቅ ወዴት ከተቱት? በአገዛዝ ዘመኖ ያሎትን ሀብት ባላውቅም ስለ እራሶ መፃፍ ይሆናልና ነው የዘለሉት?
የሕይወት ዋጋ፦ የቁጥር መብዛት ማነስ አይደለም ወያኔ እንደ ደርግ በደም፣ በሕይወት፣ ያለ አግባብ ግድያ ይጠየቃል። መንግሥት በሥልጣን ዘመኑ ከሕግ በላይ ሥልጣኑን ሽፋን አድርጎ ወይም ሕጉን እንዳሻውና እንደፈለገው ተርጉሞ ወይም በዳኝነት አሠራር ውስጥ ጣልቃ በመግባት ሌላም ሌላም በሰው ልጆች ላይ ለአደረሰው የሕይወት ማጥፋት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ማውደም፣ የሥነ ልቦና ጥቃት ሌላም ሌላ ተጠያቂነት ይኖራል። የዚህ ተጠያቂነት ደግሞ ዛሬ በየትኛውም ጊዜና በየትኛውም ዓለም ቢሆን አቤት ሊባልበት ይቻላል። ይህ ነው የአምባገነን መሪዎችና ተባባሪዎቻቸው አንዱ ከሌላው አለመማር ችግር። ሁልጊዜ እንዳሰቃዩ፣ እንደገደሉ፣ እንደዘረፉ የሚኖሩ ይመስላቸዋል። አምባገነኖች ዝም ያለ ህዝብ የተገዛላቸው፣ በረሃብ ሲያገሳ የጠገበላቸው፣ በንዴት ሲስቅ የተደሰተላቸው ይመስላቸዋል። በሀገርና በህዝብ ላይ እንደ መንግሥትነታቸው ለሚፈጥሩት ችግር መፍትሔው በማስፈራራት፣ በማሰር፣ በመግደል መግዛት እየመሰላቸው የሰውን ልጅ ለስቃይ የዳረጉ፣ የሰውን ቤት የዘጉ፣ ተጠያቂነት አይኖርም ይላሉ አዛዥ ጄኔራል?
ወያኔ ሌላው ቀርቶ ሥልጣን እርከን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ከግለሰብ እስከ ዘር ማጥፋት ወንጀል ይጠየቃል። ዛሬ ትግሉ የወያኔ/ኢህአዴግ መስተካከል ሳይሆን በሀገርና ህዝብ ላይ ለሠራው ወንጀል በተጠያቂነት ለፍርድ ማቅረብ ነው። ለኢህአዴግ/ወያኔ ይቅርታ ዘመንና መስተካከል አንድ ዕድሉን በምርጫ 1997 ቀብሮታል።
ዛሬ ጄኔራሉ የመፍትሔ ሃሳቦች ብለው የወያኔን ዕድሜ ሊያራዝሙ የሚሰጡት ምክር በቅድሚያ እዛው አመራር ላይ ላሉት ቢያደርጉት ይመረጣል። በሌላም በኩል ጊዜው አይደለም። የ1997 ዓ.ም. የምርጫ ወቅት ዛሬ ከሚመፃደቁበት ሕገ መንግሥት በላይ በመሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ በትንሹ በ196 ንፁሐን ደም ለአሥራ አንድ ዓመት ዕድሜውን ያራዘመው የእርሶ መሪ ነበር እኮ። በደዴሳ፣ በሰንዳፋ፣ በትግራይ በበርካታ የሀገሪቷ እሥር ቤቶች በአምሳ ሺዎች ታጉረው የተሰቃዩት እኮ በተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች አማካኝነት አይደለም።
“የውጭ ኃይልና የውስጥ ኃይሎች ሀገሪቷን ሊበታትኑ አሲረዋል” ሲሉ ምነዋ አልተናነቅ አሎት? እውነት ለመናገር በመንግሥት ደረጃ በኢትዮጵያ ያለ አሸባሪ አገዛዝ ወያኔ/ኢህአዴግ ለመሆኑ እስከዛሬ በሀገሪቷና በህዝቧ ላይ የተደረገው ግፍ ምስጢሩ ብቅ የሚልበት ጊዜ ዕሩቅ አይሆንም። ምነው ንገሩን በዛ። ጠግበው ያላደጉ ሕፃናትን የሚቸበችብ አገዛዝ አይደለም እንዴ? ሴቶች እህቶቻችንን እንደሸቀጥ የሚደልል ዘመነ ጥፋት አገዛዝ አይደለምን? ይህ የወንበዴ መንግሥትና ሕገ መንግሥቱ ሊወድም ቋፍ ላይ ሲደርስ አልነበረም ድምጽ ለማሰማት መጣር፣ ጊዜ ቀድሟችሁ ሄዷል።
የፖለትካና የሕሊና እሥረኞች ጉዳይ
በዚህ 20 ገጽ ጽሁፋቸው ጄኔራሉ በወያኔ እስር ቤት እየማቀቁ ስላሉት በ100 ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አንድም ሊያነሱ አልፈለጉም። ከወቅቱ ጥያቄ አንዱ “የፖለቲካና የሕሊና እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፈታት” ጥያቄ ነው። እኮ ምነዋ! በየቦታው የታጎሩት የእስልምና እምነት ተከታዮች፣ በግርፊያና በረሃብ እየተሰቃዩ ያሉት የኦሮሞ ወጎኖቻችን፣ በጅምላ እያጎራችኋቸው ያሉት የአማራ ልጆች፣ ኑሯቸው እሥር ቤት መሆኑ አልበቃ ብሏቸው የተለቀሙት የጋምቤላ ኢትዮጵያውያኖች፣ በአሸባሪ ስም የለቀማችኋቸው የምሥራቅ ኢትዮጵያ ሶማልኛ ተናጋሪ ዜጎቻችን፣ ወያኔ ከገባ ጀምሮ ማንነቱን ያላስነካው የደቡብ ብሔረሰብ ጀግኖች መከራ ይህ ሁሉ በወያኔ እሥር ቤት እየማቀቁ ያሉ አይደሉምን?
በስም ስንጠቅስ የዞን ዘጠኝ ጦማሮች፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ እስክንድር ነጋ፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከብዙ በትንሹ እየተሰቃዩ ያሉ ወገኖቻችን ለምን ተቃወሙን፣ ለምን ጻፉብን ብላችሁና “ብርቅዬውን” ሕገ መንግሥት ተገን አድርጋችሁ እግር ብረት ያስገባችሁላቸው መሆኑን ዘነጉት ተጋዳላይ ፃድቃን?
ዳግም ስህተት እንዳይሠራ እንጠንቀቅ
ወያኔ ከማደንቀው ጉዳይ አንዱ የተቃዋሚውን ሥነ ልቦና በሚገባ ተረድቷል። ተቃዋሚውን እንዴት አድርጐ እንደሚከፋፍልና እንደሚያዳክም በተለይ ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ ወዲህ የማያቋርጥ ጥረት አድርጓል። ስኬታማም ሆኗል። ሁሌም ግና አይሠራም። የሌ/ጄ ፃድቃን የሰሞኑን ጽሁፍ ተገን አድርጐ ማራገቡ በሠፊው ይቀጥላል። ጄኔራሉ “ወያኔን ተቃውመው ፃፉ” በሚል በተለያዩ የመገናኛ ሚድያዎች ለውይይት ይቀርባሉ፣ የፓል ቶክ አዳማቂዎች ያናፍሱላቸዋል። በቀጣይነትም ተጋብዘው በየስቴቱ እየተዘዋወሩ መግለጫ እንዲሰጡ ይደረጋል። በተቃዋሚነት የተሰለፈውም አንዱ ሲደግፋቸው ሌላው እንዴት ተደርጎ ሲል ከዓመት በላይ የሚዘልቅ ንትርክ ይገባል። በዚህ ሂደት የዴያስፖራው ተቃዋሚ አንቀላፍቶ ሲባንን ሰውየው እድሮው ቦታቸው ናቸው። ለዚህም ነው መግቢያው ላይ እንዳልኩት ከአለፉት ስህተቶች ተምረን ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል። የዚህ ጽሁፍ ዋና መልዕክት።
የወያኔው መሪ አቶ ስዬ አብርሃና አቶ ገብሩ አሥራት በጊዜአቸው የውጭውን ተቃዋሚ እርስ በርስ ማተራመስ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ድርጅቶችን አናግተው ሄደዋል። ይህ ዛሬ ላይ ሆነን ስንመለከተው የጠቀመው ወያኔን ነው። አቶ ስዬና አቶ ገብሩ በ17 ዓመት የሜዳ ትግላቸውና በ10 ዓመት የወያኔ ሥልጣናቸው ያጠፉትን ጥፋት ለኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርታ ጠይቆ፣ ኢትዮጵያ ወደ አንድነቷ እንድትመጣና የዘር ፖለቲካ እንዲያከትም ከማታገልና ከማስተባበር ይልቅ፤ አሁንም የትግራይ ህዝብ ተገን ያስፈልገዋል ብለው “ዓረና ትግራይ” ብለው ዳግም ለዘራቸው መቆማቸው ስንቶችን እንዳበጣበጠ አይዘነጋም። ይህ ነው በወያኔ ፖለቲካ የተከተበ ዳግም የዘሩን ሲፈልግ።
አቶ ስዬም በወቅቱ መድረኩን ሞሉት። ኢትዮጵያ ሰው ያጣች ይመስል “ምሩን” ተባሉ። የኦሮሞን ትግልና ስቃይ “እሳቸው እንዳሉት” ይባልላቸው ጀመር። “ኧረ እባካችሁ!” ቢባል “ምን ታውቃላችሁ” ይሉ የነበሩ ዛሬ አቶ ስዬ የት እንዳሉ ሊነግሩን ይችላሉ? ለትግል ጫካ ገቡ ወይስ …?
የመፍትሔ ሃሳብ
ወያኔ 14 ዓመት ሙሉ የረጨው የዘር ፖለቲካ እንዳልሠራ ትልቅ ትምህርት ሰጥቶ ያለፈው 1997 ዓ.ም. የምርጫ ትርይት ነበር። ለአብነት በአዲስ አበባ ያለ የሁሉም ዘር ሳይከፋፈል እስላም ክርስቲያኑ በአንድነት ሁሉም እጅ ለእጅ ተያይዞ በጋራ የተዋደቀበት የሰልፍ ትርይት የህዝቡን አንድነት አንጸባርቆ አልፏል። አሁንም ከአሥራ አንድ ዓመት በኋላ ህዝባዊ አመጽን ይዞ የተነሳው የጋራ ጥያቄ በመሆኑ ወደ አንድነቱ ያስጉዘዋል። ኢትዮጵያና ህዝቧ ዛሬ ያላት ዋናው ጠላት ህወሓት ነውና።
መፍትሔው በየቦታው ያለውና የተጀመረው ትግል ተቀናጅቶ መቀጠል ነው። ያለምንም ጥርጥር እስላሙ ሕብረተሰብ ክርስቲያን ወገኑን አልጠላም። የኦሮሞ ልጆች በአማራው ላይ አይነሱም፣ የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያዊነት ማኅተቡ ነው። በየቦታውና በየክልሉ የተነሳው እንቅስቃሴ የወያኔ 25 ዓመታት የግፍ አገዛዝ የወለደው ነው። ሀገር ለህዝብ ለልጆቿ እንድትሆን መስዋዕትነት ግድ ነው። አዎ! አንጠራጠር ወያኔ ገና ብዙ ይገድላል። ግና የመጨረሻ ድሉ የህዝብና የኢትዮጵያ ነው። ለወያኔ የሚያመቸው የተናጥል ማጥቃት ነውና ጉራጌው፣ ደቡቡ፣ ጋምቤላው፣ ኦሮሞው፣ አማራው፣ ሱማሌው፣ ሐዲያው፣ የአዲስ አበባ ህዝብ፣ የትግራይ ልጆች፣ ጅማ፣ ኢልባቡር፣ ባሌ፣ ከፋ፣ ጎሙጎፋ፣ አርሲ፣ ሲዳሞ፣ ሐረርጌ፣ ወሎ፣ ወለጋ፣ ጎጃም፣ ጎንደር፣ መቀሌ፣ ሸዋ ሁሉም ሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች በጋራ ተነሱ። በየአቅጣቻው ወያኔን አጣድፉት። ጊዜውና ወቅቱ አሁንና አሁን ነው። መፍትሔው ትግል ብቻ ነው። ትግላችሁን እራሳችሁ እንደአካባቢያችሁና እንደባህላችሁ አቀናጅታችሁ ተጓዙ። የምትከፍሉት የሕይወት መስዋዕትነት ለሀገር ህልውና፣ ለህዝብ አንድነት ነውና ታሪክ ምንግዜም አይረሳችሁም። ድል የህዝብ ነው!
ታጋይ የፖለቲካ ድርጅቶች፦ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም ያላችሁ ወያኔን ምትቃወሙና የምትታገሉ የፖለቲካ ድርጅቶች በሙሉ፤ ወያኔ ጥሎልን የሚሄደው የቤት ሥራ እውነት ለመናገር ቀላል አይደለም። 25 ዓመት የረጨው የዘር ፖለቲካ ወደ ኢትዮጵያዊነት ብሔራዊ ስሜት ይመጣ ዘንድ ብዙ መስራት ይጠይቃል። ወያኔ ይወድቃል አሳሳቢው ቀጣዩ ነውና ለሀገርና ህዝብ ሲባል የጋራ መድረክ በመክፈት ትግሉን አቅጣጫ ለማስያዝ ጥረት ማድረግ የሚገባችሁ ወቅት እየራቃችሁ ነው። ህዝብና ትግሉ ቀድመዋችኋልና ልታስቡበት ይገባል። ይህ ካልሆነም እየታገለና እየተሰቃየ ላለው ህዝብ ድጋፋችሁን ከማሰማት ባሻገር “እኛ አለንበት፣ እኛ እየመራነው ነው፣ የእኛ ሥራ ነው ወዘተ” እያላችሁ ሌላውን ግራ አታጋቡ፣ ሚታገለውንም አታደናግሩ። ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማው ይቅር።
ተጋዳላይ ሌ/ጄ ፃድቃንና ለወያኔ አመራሮች፤ እውነት እውነት እላችኋለሁ የሥልጣን ዘመናችሁ፣ የአገዛዝ ጊዜያችሁ አብቅቷል። በዚህ ፀሐፊ አመለካከት ሁለት አማራጭ አላችሁ።
አንደኛው፦ በሀገርና ህዝብ ጉዳይ ወደዳችሁም ጠላችሁ ተጠያቂዎች ናችሁ። በሀገር ሌብነት ትጠየቃላችሁ። በዘረፋ፣ በዘር ማጥፋት ወንጀል ትጠየቃላችሁ። ከፊታችሁ የተደቀነው ስለ ፍትህ ጠያቂ ህዝብ ነውና ቤታችሁ ወህኒ ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬ አይግባችሁ። አጭሩ መንገዳችሁ እስከዛሬ የዘረፋችሁትን ዘርፋችኋል፣ ያተራመሳችሁትን አተራምሳችኋል፣ ለሀገርና ህዝብ ደንታ የሌላችሁ አፍቃሪ ነዋይ ናችሁና ይበቃችኋል። የያዛችሁትን ይዛችሁ ከሀገርና ህዝብ ጫንቃ ላይ በሰላም ውረዱ። እፈለጋችሁት ሀገር ሄዳችሁ ኑሩ። የኢትዮጵያ ልጆች ሀገራቸውን ፈልገዋል። በዘር የከፋፈላችኋቸው ብሶት አንድ አድርጓቸዋል። የዘረኝነትን ጦሱንና መዘዙን በሚገባና በተግባር በትንሹ ለአለፉት 25 ዓመታት አይተዋል። ጆሮ ያለው ይስማ ቤቱን ለባለቤቱ ልቀቁ። ይህ ቀና ምክሬ ነው።
ሌላው የኢህአዴግ/ወያኔ ዕጣ ፈንታ በህዝብ ድል መጠናቀቅ ነው። ያኔ ዋይታው እናንተ ላይ ይበረታል። እጅግ የመረረው፣ በእናንተ የመጀመሪያው ገፈት ቀማሽ ነውና የሚያገኛችሁ ቅጣቱን የሚያስቆመው የለም። ጦሳችሁ ከእናንተ ተሻግሮ ለሌላ ይተርፋልና የዘረፋችሁትንም ያከማቻችሁትንም ያን ጊዜ አታገኙትም። የዚያ ጊዜ ጆሮ “አድኑን!” የሚለውን ቃል አይሰማም። ሁሉም ነገር ለእናንተ ይበረታል። መንገዶች ይታጠሩባችኋል። በአራቱም ማዕዘን የሀገርና የህዝብ ብሶት አፍጥጦባችኋልና ዕይታውን፣ ማስተዋሉን ይስጣችሁ። ለእናንተ “እግዚዎ!” ባይ አይገኝም።
በፈርሃ እግዚአብሔር የተገዛው ህዝብ የችግሩ መጠን በንጉሡ ላይ እንዲያምጽ አድርጐት ምን ዓይነት አወዳደቅ እንደወደቁ ከእሳቸው ተማሩ። ኢትዮጵያን በጥሩ ስም አስጠርተው ወደ መጨረሻው ማስተካከል ተስኗቸውና ለማዳመጥ ዝግጁ ባለመሆናቸው ማን ላይ እንደጣላቸው ተገንዘቡ። ችግራቸው ከእሳቸው አልፎ በአንድ ለሊት ለተረሸኑት ባለሥልጣኖችና በየጊዜው የፍየል ወጠጤ ለተዘመረባቸው መኳንንትና መሣፍንት እንደነበር ትምህርት ውሰዱ።
ከግማሽ ሚሊየን ሠራዊት ያላነሰ የነበረው የፋሽስት መንግሥቱ ኃይለማርያም አገዛዝ በወራት ጊዜ መናዱ የራሳችሁ ትዝታ ነው። ከአፍሪካ በግዙፍነቱ የታወቀው አየር ኃይል የሸሸበት ዘመን ነበር፣ ታንክ በማርቼዲስ ፍጥነት ወደ ኋላ የፈረጠጠበት ጊዜ ነበር፣ ሠራዊቱ የልብስ ያለህ እያለ መለዮውንና አልባሳቱን በመሣሪያው እየቀየረ እግሬ አውጭኝ ያለበት ዘመን የዛሬ 25 ዓመት ነበር። እራስ ወዳዱ መንግሥቱ ኃይለማርያም አብረው የተጓዙትን አጋሮቹን ሳይቀር አጋፍጦ የፈረጠጠው የሚሉትን አልሰማ ባይ በመሆኑ ነበር። ከነዚህ ሁለት መንግሥታት አወዳደቅ ትምህርት ውሰዱ።
እናንተ “እኛ ከሌለን ኢትዮጵያ አበቃላት” ትላላችሁ። እኛ ደግሞ “ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር! ትኖራለች!” እንላለን። አቅማችሁ በየት በኩል ባዶ እንደሚሆን አታውቁትም። ደርግ ሁሉ ተይዞበት አዲስ አበባ ተከባ “የጦርነት ማቆም አድርጌአለሁ፣ እንደራደር …” ብሎ ቢጮህ ወሳኙ ኃይል ነበርና ኃይሉ ተሟጧልና ማን ሊሰማው። እናንተም ዛሬ በድብቅ ያከማቻችሁት የሠራዊት ኃይል፣ የገነባችሁት የጦር ሠፈር፣ በህዝቡ ውስጥ የቆላለፋችሁት የስለላ መረብ፣ ህዝብ ላይ ያነጣጠራችሁት የሚሳይል ክምችት በአንድ ጀንበር የውኃ ሽታ እንደሚሆን ገምቱ፣ ውድቀቱ ከየት አቅጣጫ እንደሚመጣ አታውቁትም። የዚያን ጊዜ ልመናችሁ ቢበረታ ጆሮዎች አይሰሙም፣ ዓይኖች አያዩም፣ እጆች አይራሩምና ከአለፉ ታሪኮች ተምራችሁ ኢትዮጵያን ልቀቋት። ህዝቡን እፎይታ ስጡት።
ከግብጹ ሙባረክ፣ ከሊቢያው ጋዳፊ አወዳደቅ ተማሩ። የውጭ ኃይሎች አሉልን ብላችሁ አትመፃደቁ። ሁሉም የውጭ ኃይል ለሀገሩ ጥቅም የቆመ ነውና የኃይል ሚዛኑን ተመልካች ነው። የኃይል መለኪያው ሚዛኑ ህዝብ ነውና የኢትዮጵያን ህዝብ አድምጡ። የምታደምጡት በሥልጣን ለመቆየት ሳይሆን ለመልቀቅ። ይህ ነው መልዕክቴ።
የትግራይ ህዝብ
ሌ/ጄ ፃድቃን በአጭሩ የምልዎ የትግራይን ብሔረሰብ መነገጃ አናድርገው። በእምነቱና በኢትዮጵያዊነቱ ኮርቶ ያለ ሕብረተሰብ ነው። ለትግራይ ሕብረተሰብ የአክሱም ሐውልት ኢትዮጵያዊነት መኩሪያው ነው። በርካታ አብያተ ገዳማት የእምነቱ መሠረቶች ናቸው። ትግራይ የኢትዮጵያ መሠረት ናት። አድዋ ለትግራይ የኢትዮጵያዊነት ብቻ ሳይሆን የጥቁር ህዝቦች መኩሪያ ድሉ ነው። ይህ ሕብረተሰብ ኢትዮጵያን ሊያጠፋ አልተነሳም። ይህ ሕብረተሰብ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ላይ ሊዘምት አልከጀለም። አዎ ከውስጡ የበቀላችሁና የወጣችሁ ጉዶች አላችሁ። ኢትዮጵያዊነቱን እንዲክድ ጥራችኋል እየጣራችሁም ነው፣ የእምነት አድባራቱን እንዲዘርፍ፣ እንዲያወድም ሞክራችኋል፤ አሁንም ትጥራላችሁ፣ ወገኑ አማራው ላይ እንዲዘምት አጣብቂኝ ከታችሁታል፤ ይህ ያሳፍረዋል፣ አንገት ያስደፋው ይሆናል።
ትልቁ መከራና ሃሳብ ከማንም በላይ በትግራይ ተወላጆች እጅ አለ። በስሙ ሀገር እያጠፋችሁ፣ ህዝብ እየፈጃችሁ ነውና ሊቆጠቁጣቸው፣ ሊያማቸው ይገባል። በነፃነት ስም ተቀፍድዶ ተይዟል። ማንነታችሁን በሚገባ ያውቃልና ከማንም ባላነሰ ጉልበታችሁንና እመቃችሁን ተሸክሟል። ለዚህም ነው የትግራይ ወገናችን ኢትዮጵያን በማዳኑ ሂደት ትልቁን ሚና መጫወት የሚጠበቅበት። የትግራይ ገበሬና ገጠሬ ሕይወት በስሙ መጠቀሚያ አደረጋችሁት እንጂ የስቃዩ ተጋሪ ነው።
በሌላ በኩል አሁን በልማትና በዕድገት አስመዘገብን በምትሉት ዘረፋ ከማንም በላይ በወያኔ ዙሪያ የተኮለኮሉት የትግሬ ተወላጆች ተመቻችቶላቸዋል። እነኚህ ኢምንት ዘራፊዎች መላ የትግሬውን ሕብረተሰብ ሊወክሉ ከቶም አይገባውም። አዎ በአዲስ አበባና በአንዳንድ ከተሞች በተደረጉ ፀረ-ወያኔ እንቅስቃሴዎች እየተመረጡ የትግራይ ዘራፊ ንብረቶች ጋይተው ይሆናል። ይህ ማለት የትግራይ ተወላጆች ላይ ማነጣጠር ሳይሆን የወቅቱ ዘራፊ ባለሀብቶች የጊዜው ሚዛን ያደላላቸው በአብዛኛው ከትግሬው ወገን ስለሆኑ ብቻ ነው። የትግራይ ሕብረተሰብ ከማንም በላይ ተንኮላችሁንና አካሄዳችሁን ጠንቅቆ ያውቃል። ይህን ማንነታችሁን ደብቆ የሚቀመጥበት ጊዜ ማብቃት ይኖርበታል። እናት ሀገሩን ኢትዮጵያ በስሙ ከምትነግዱ የጥፋት መልዕክተኞች ለማዳን ዝምታውን ሰብሮ ከምንጊዜውም በበለጠ ሰልፉን ከሀገሩና በየቦታው ከወያኔ ጋር እየተፋለመ ካለው ህዝብ ጋር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ይህ ነው መልዕክቴ!