PBS: Escaping Eritrea … [Read More...] about ካብ ውሽጢ ቤት ማእሰርታት ኤርትራ
በህወሃት ኣምባገነናዊ አገዛዝ እዝ ስር የሚገኘው “የጠንካራው ሰራዊት” አፈታሪክ
ነአምን ዘለቀ (ቨርጂኒያ ) |
“በጠንካራ ሞራል/እሴት የተገነባ ሰራዊት ሶስት እጅ ጠላት ድል ያደርጋል” ናፖሊዮን ቦናፓርቴ
“ህዝብን እንደአመራሩ በእኩልነት አላማ ማነጽ ያለምንም ፍርሃት ሞትንም ህይወትንም እንዲጋሩ ያደርጋል” ሱን ትዙ
በአናሳው የህወሃት ኣምባገነንናዊ አገዛዝ ስር የምትማቅቀውን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ “አስተማማኝና የተረጋጋች አገር” ናት የሚለው የተሳሳተ አመለከካከት ለተወሰኑ አመታት ሲነገር መቆየቱ ይታወሳል። ይህ መሰረተ ቢስ አኣባባል በምዕራብያውያን አገሮች በተለይም አሜሪካና ታላቋ ቢሪታኒያ ዉስጥ በስፋት ሲነገር ቆይቷል። በዚህ ጽሁፍ በህወሃት አገዛዝ የሚታዘዘውንና “ጠንካራው ሰራዊት” እየተባለ የሚነገርለትን የኣገር መከላከያ ሰራዊት ባህርያትና ውስብስብ ችግሮችን ይዳስሳል ።
የፕሩሺያው የጦር ፈላስፋ፥ ወታደራዊ ሊቅና በምዕራብያውን ወታደራዊ ስትራቴጂ ንድፍ ዉስጥ ትልቅ ሚና የተጫወተዉ ክላስዊትዝ፣ በጦርነትና በወታደራዊ ኦፐሬሽን ውጤታማ ለመሆን “ሶስት” ስላሴዎች በህብረት አንድ ሆነዉ መቀናጀት እንዳለባቸው ይናገራል። ሶስቱ ማገሮች እርስ በርሳቸዉ ግንኙነት፣ ውጥረት፣ ግጭትና፣ ፍጭት ቢኖርባቸውም ሚዛን መጠበቅ ይኖርባቸዋል። ክላዊዝ ሶትቱ ስላሴዎች (trinity) ያላቸዉ ህዝብ፣ መንግስትና ሰራዊትና ናቸዉ።
ከፕሩሲያዉ ክላዉዝ ሁለት ሺህ አመት በፊት የነበሩት ሱን ትዙ የተባሉ ቻይናዊ የጦር ፈላስፋና ስትራቴጂስት ከክላዉዝ ጋር ተመሳሳይ አመለካከት ይጋራል። ፍልስፍናቸዉ በምዕራቡና በምስራቁ አለም በብዛት የተጠና የስትራቲጂ ፈላስፋ የመንግስትና የህዝብ አላማዎች ተመሳሳይ ከሆኑ፣ ታዎ (መንገድ) ይኖራል ይላሉ። ሱን ትዙ መንግስትና ስራዊቱ ተመሳሳይ አላማ ካላቸው ይህ እዉነታ ታዎ ወይም (መንገድ) ነው ካሉ በኋላ ታዎ ጦርነት ለመክፈትም ለማሸነፍም በቂ ቅድመ-ሁኔታ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በመንግስት፣ በህዝብና በሰራዊቱ መካክል ክፍተት ካለ ግን በአገርና በህዝብ ላይ ከፍተኛ ችግር ያስከትላል፥ ጦርነት ማሸነፍም አይቻልም።
በዛሬዋ ኢትዮጵያ መንግስትና ሰራዊቱ ተመሳሳይ አላማ ስለሌላቸዉ በሁለቱ መካከል ያለዉ ክፍተት ከአመት አመት እየሰፋ መጥቷል። በተለይም በህውሃት አገዛዝና በኢትዮጵያ ህዝብ፣ በሰራዊቱ አዛዦችና በኣብዛኛው ሰራዊት መካከል ከፍተኛ የሆነ ክፍተት ተፈጥሯል። በጥቂት የትግራይ ጄነራሎች የሚመራዉ የህወሃት ሰራዊት በብዙ ችግሮች ተተብትቦ የሚገኝ ሲሆን፣ በውጭና በውስጥ በሚደርስበት ግፊት በቀላሉ ሊፈረካከስ የሚችልበት ሁኔታ ላይ ይገኛል።
በአናሳው የህወሓት አገዛዝ የሚመራው የመከላከያ ሰራዊት በደርግ ስርዐት ዉስጥ ከነበረው የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት በባሰ መልኩ ከፍተኛ ቀውስና ዉድቀት ውስጥ የሚገኝ ሰራዊት ነዉ። በደርግ ዘመን የነበረዉ የኢትዮጵያ ሰራዊት ሌላ ቢቀር የሱማሊያን ወራሪ ሃይል አባርሮ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ያስከበረ ጀግና ሰራዊት ነበር። ከዚህ በተጨማሪ በአገሪቱ ዉስጥ በሁሉም አቅጣጫዎች ከተለያዩ አማጽያን ጋር ለ30 ኣመታት በኤርትራ ለ17 ኣመታት ደግሞ በትግራይ ፡ አንዲሁም በልዩ ልዩ የኣገሪቱ ክፍሎች የተራዘመ ከፍተኛ ውጊያ ሲያደርግ የነበረ ሰራዊት ነዉ።
የታሪክ ባለሙያ የሆኑት ገብሩ ታረቀ “የኢትዮጵያ አብዮት፣ ጦርነት በአፍሪካ ቀንድ” በሚለው መጽሃፋቸው ዉስጥ በደርግ ዘመን የነበረውን የጦርነት ሁኔታ ሲገልጹ የሰራዊቱ ውድቀት ዋናው ምክንያት መንግስት ፊቱ ላይ የተደቀኑትን ችግሮችና ተግዳሮቶች መቋቋም የሚችል ስትራቴጅካዊ የአስተሳሰብ ብቃትና ልምጥነት ስላልነበረዉ ነው በማለት ጽፈዋል። የኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ (ኢሰፓ) ያራምድ የነበረው የማርክሳዊ ሌኒናዊ ጽንሰሃሳቦች፣ ኢኮኖሚያዊና በመንግስት የተወሰዱ ሌሎች ፖሊሲዎች፥ መንግስት የወሰዳቸዉ አፋኝ እርምጃዎችና በአራቱም ማዕዘናት የተደረጉት ጦርነቶች ሁሉም የደርግ አገዛዝና የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲለያዩና እንዲራራቁ አድርገዋል ሲሉ ገብሩ ታረቀ ገልጸዋል። ማርክሳዊ ሌኒናዊዉ የደርግ-ኢሰፓ መንግስት ኤርትራንና ትግራይን ጨምሮ በአማጽያን ላይ ባደረገው ጦርነት፣ ዕርዳታ የሚሰጠውንና የጥንካሬውን መሰረት የሆነውን ህዝብ ያጣው ከላይ ተጠቀሱት ምክንያቶች ይገኙበታል።
የህዝብ ድጋፍ ማጣት ለኢሰፓ ስራኣት ውድቀት መንስኤ ከሆኑ ብዙ ምክንያቶች ዉስጥ አንዱና ዋንኛው ነበር ። የማንም አገር ጦር ሰራዊት መሰረቱ ህዝብ ነዉ። በዚህ ዘመን ስር የነበረው የኢትዮጳያ ሰራዊት መሰረት የሆነዉ ህዝብ ለሰላሳ አመታት ኤርትራ ዉስጥ፣ 17 አመት ደግሞ ትግራይ ዉስጥ በተደረገዉ እጅግ በጣም አሰልቺ ጦርነት ሞራሉ ላልቶ ነበር፥ በመንግስት ላይ ያለዉ እምነት ጥያቄ ዉስጥ ገብቷል። ይህ በእንዲህ እንዳለ እንደ አዉሮፓ አቆጣጠር በ1989 ዓም የተደረገው መፈንቅለ መንግስት የአገሪቱን ምርጥ ወታደራዊና ሲቪል ስትራተኢጅካኢው ኣዛዦችና መሪዎች ህይወት ቀጥፎኣል። መፈንቅለ መንግስቱ የኢትዮጵያ ህዝብና ሰራዊቱ በወታደረዊዉ ደርግ፥ ጀኔራሎችና ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ደግሞ በጦርነት መሰላቸታቸውን፡ የቅራኔዎች መባባስ አንዲሁም በስሜን የሚደረጉት ጦርነቶች የደረሱባችውን የችግሮች ግዝፈት ደረጃ መገለጫ ነበር። ይህ ሁሉ ተደምሮ የኢትዮጵያ ህዝብ የደርግ የፖለቲካ ስርዓት አየገፋበት የነበረውን ጦርነት የመሸከም ፍላጎት እንደሌለዉ በግልጽ አሳይቷል።
የህወሃት/ኢህአዴግ ስር የሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ወታደራዊ ይዞታና የዉጊያ ብቃት በተለያዩ ግንባሮች ከተለያዩ ሀይሎች ጋር ከተፋለመዉ በኢስፓ ስራኣት ስር ከነበረው የኢትዮጵያ ሰራዊት ጋር ሲነጻጸር በይዘቱም በብቃቱም እጅግ በጣም ያነሰ ነዉ። “የግጭት አስተዳድርና መፍቻ” ሳይንስ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ተረንስ ላየንስ ኢትዮጵያን በተመለከተ ባጠኑት ጥናት እንዳመለከቱት የህወሃት/ኢህአዴግ ሰራዊት ሆነ የፖለቲካ ስራኣቱ ነው “ተሰባሪ” ብለዋል። በተለይም በረጅሙ ጊዜ ሲገመገም። ፕሮፌሰር ተረንስ ላየንስ የህወሃት/ኢህአዴግ የፓለቲካ ስርኣትም ሆነ በስሩ የሚገኘው ሰራዊት ለአጭር ጊዜ ጠንካራና የተረጋጋ መስሎ ቢታይም ዉሎ አድሮ መፍረከረኩ የማይቀር ነዉ ሲሉ በጥናታቸው ላይ ኣስምረውበታል፡፡ ይህ የሚሆነው ህዝባዊና ፍተሃዊ ስራኣት ስላልሆን ነው። በእርግጥም የህወሃት ስር የሚገኘው ሰራዊት ከተለያዩ አቅጣጫዎች ብረት አንስተው የሚዋጉ ቡድኖች ጉልበት እያገኙ፣ በውስጥም ህዝባዊ አመጽና የህዝብ ኣልገዛም ባይነትና አምቢተኝነቱ እየበረታና ኣየተቀጣጠለ በመጣ ቁጥር ከፍተኛ የመፍረክረክ አደጋ የተጋረጠበትና ሰራዊት ነዉ።
ለመሆኑ ለምን ይሆን የህወሃት ሰራዊት የመፍረስ አደጋ የተጋረጠበት? በህወሃት ኣገዛዝ ውስጥ የሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት በአጭር ግዜ ዉስጥ ሊያፈርረከርኩት የሚችሉ ብዙ ምክንያቶች አሉ። ከዚህ በፊት የተሰበሰቡ አያሌ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በሰራዊቱ ውስጥ ያለው ውስጣዊ ሽኩቻ፣ ክፍፍልና ከፍተኛ የሞራል ዝቅጠት ለሰራዊቱ መፍረክረክ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ከሚያደርጉ ምክንያቶች ዉስጥ ዋና ዋናዎቹ ናቸዉ። እነዚህ መረጃዎች የተሰበሰቡት በወያኔ ሰራዊት ዉስጥ የተለያየ የስልጣን ደረጃ የነበራቸው መኮንኖች፥ ሰራዊቱን የከዱ የሰራዊቱ አባላት፣ የአየር ሃይል አብራሪዎችና ወታደራዊ ቴክኒሽያኖች ከሰጡት የቃልና የጹሁፍ መረጃዎች መሰረት ያደረገ ነዉ።
ዛሬ ሙሉ በሙሉ በህወሃት ቁጥጥር ስር የሚገኘው የምድርና የአየር ሃይል ሰራዊት ሞራሉ የወደቀና የውጊያ መንፈሱ የደከመ ሰራዊት ነው። ከታመኑ የአገር ዉስጥ በርካታ ምንጮች ሆነ በኢሳት ከተሰራጩ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከጥቂት ወራት በፊት የህወሃት መከላከያ ሚኒስቴር ዋና የመነጋገሪያ አጀንዳ ከሰራዊቱ እየከዱ ከሚጠፉና ተቃዋሚዎችን (ሽምቅ ተዋጊዎችን) የሚቀላቀሉ ወታደሮች መብዛት ጉዳይ ነዉ ። የመከላከያ ሚኒስቴር በሚያደርጋቸዉ ስብሰባዎች ላይ ተገኝተዉ ወታደሮቹ የሚከዱበትን ምክንያት ለማወቅ ምርመራ ላይ ከተገኙት መካከል የመከላከያ ሚኒስትሩ ሲራጅ ፈርጌሳ፣ የጦር ሃይል ዋና አዛዥ ሳሞራ የኑስና ሌሎች የሰራዊቱ ከፍተኛ አዛዦች ይገኙበታል። በአሁኑ ወቅት የወያኔን ሰራዊትን በመተው ኤርትራ ዉስጥ የሚገኙ ተቃዋሚ ድርጅቶችን የሚቀላቀሉ ወታደሮች ቁጥር በግልም በቡድንም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመሄድ ላይ ነዉ። ይህ የሆነበት ዋናዉ ምክንያት በተደጋጋሚ በሰራዊቱ መካከል የሚታየው አድልዖ፣ ዘረኝነትና የማግለል ሂደት አንዱሁም በህወሃት ካድሬዎች የሚፈጸመዉ ጭቆና አንደምከነያትነት የሚቀርቡአ ሲሆኑ። እስክዛሬ የተጠናቀሩት መረጃዎች እንደሚያሳዩት በቁጥር ቀላል የማይባሉ የወያኔ ሰራዊት አባላት አርበኞች ግንቦት ሰባትንና ሌሎች ድርጅቶችን ተቀላቅለዋል፣ አሁንም እየተቀላቀሉ ይገኛል።
ወደ አየር ሃይሉ ስንመለከት ደግሞ ዛሬ ኢትዮጵያ የጦር አዉሮፕላኖች እንጂ አየር ሃይል አላት ማለት አይቻልም። የህወሃት አገዛዝ በሚያደርጋቸዉን በማያደርጋቸዉ ድርጊቶች የኢትዮጵያን አየር ሃይል ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ከትቶታል። የአየር ሃይሉን ዝቅጠትና ዉድቀት በግልጽ ከሚያሳዩ ዋና ዋና ሁኔታዎች ዉስጥ አንዱ ላለፉት ሁለት አስርተ አመታት ከፍተኛ የማብረር ችሎታና ብቃት ያላቸዉ አብራሪዎች የሚያበሩትን አውሮፕላን እየያዙ ወደ ጎረቤት አገሮች የመሄዳቸው ጉዳይ ነው። ህወሓት ስልጣን ሲይዝ በደርግ ዘመን የነበሩ ምርጥ የአየር ሃይሉን አብራሪዎችና ሙያተኞች “የደርግ ነበራችሁ” በሚል ሰበብ ስላባረረ ዛሬ በህወህት ቁጥጥር ስር የሚገኘዉ አየር ሃይል “አብራሪ አልባ” አየር ሃይል ነዉ።
እኤአ በ2006 እና 2007 በቤላሩስ እና በእስራዔል ስልጠና የወሰዱን አብራሪዎችን ጨምሮ ባለፉት 11 አመታት ብዛት ያላቸው ሌሎች አብራሪዎችና ባለሙያዎች አየር ሃይሉን ከድተዋል። ይህ አየር ሃይሉን የመክዳት ችግር እየተባባሰ ሄደ እንጂ አሁንም አልቀነሰም። በቅርብ ጊዜ ሁለት ፓይለቶችና አንድ ከፍተኛ ቴክኒሽያን ሩሲያ ሰራሽ ተዋጊ ሄሊኮፕተር ይዘዉ ኤርትራ አንደገቡ ይታወቃል። ባጠቃላይ ባለፉት ሁለት አመታት ብዛት ያላቸው የአየር ሃይል መኮንኖች፡ፓይለቶችና የቴክኒክ ባለሙያዎች የነጻነትና የዲሞክራሲ ትግሉን ተቀላቅለዋል።
በወያኔዋ ኢትዮጵያ ዉስጥ የአየር ሃይልና የምድር ጦር ሰራዊት ህወሓትን እየከዳ ተቃዋሚዎችን የሚቀላቀልበት በርካታ ምክንያቶች አሉ። ዋናዉ ምክንያት ግን ሰራዊቱ በዘር የተደራጀ መሆኑ፥ በኣብዛኛው ከአንድ ዘር በተዉጣጡ የህወሓት መኮንኖች የበላይነት የሚታዘዝ መሆኑና አዛዦቹ በሙስናና በለየለት ዝርፊያ በመዘፈቃቸዉ ነዉ። ከዚህ በተጨማሪ የህወሓት አዛዦች በጦር ሰራዊቱ ዉስጥ የሚያደርሱት የስነልቦናና የአስተዳደር ችግር እጅግ በጣም ስር የሰደደ መሆኑም ጭምር ነው።
ኢትዮጵያ ዉስጥ ለመከላከያ ሰራዊት አባላት የሚከፈለዉ ደሞዝ እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነዉ። ከዚህ ዝቅተኛ ደሞዝ ዉስጥ ወያኔ ያለሰራዊቱ ፍላጎት መለስ ፋውንዴሽን፣ ህዳሴ ግድብና ተሃድሶ እያለ የሰራዊቱን ደሞዝ እየቆራረጠ ያስቀራል። ይህ ከፍተኛ ወታደራዊ ሃላፊዎች የበታች ወታደሮችን ሳያማክሩ ከወርሃዊ ገንዘባቸው ላይ እየቆረጡ የሚወስዱት ገንዘብ በሰራዊቱ ዉስጥ ከፍተኛ ምሬትና ቁጭት ፈጥሯል።
የመከላከያ ሚኒስቴር መሪዎች የሰራዊቱ አባላት ለህሴዉ ግድብ፥ ለመለስ ፋውንዴሽንና ለሌሎችም የወያኔ ፕሮጀክቶች መዋጮ ከደሞዛቸው ለማዋጣት እንደማይገደዱ ቢገልጹም፣ በተግባር እንደሚታየዉ ግን መዋጮ የማይሰጡ የሰራዊት አባላት በጥቁር መዝገብ ዉስጥ ስማቸዉ እንዲሰፍር ይደረግና የሙያ ስልጠና፣ የትምህርት ዕድልና የማዕረግ ዕድገት እንዳያገኙ ምክንያት ይሆናል።
በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ18 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎቿ እየተራቡ ባሉባት ኢትዮጵያ፣ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በዘረኝነት እየተሰቃዩ ባሉባት አገር፣ ከፍተኛ የህወሃት ወታደራዊ ሹማምንቶች ራሳቸውን በሀገሩት ታሪኣክ ውስጥ ተሰምቶ በማይታወቅ መጠን በሙስና እያበለጸጉ ይገኛሉ። ውብ የመኖሪያ ቪላዎችና ትላልልቅ ንግድ ቤቶች፡ በውጭ ሀገራት መኖሬያ ቤቶች ጭምር የገነቡ የህወሃት ጄኔራሎች አጅግ በርካታ ናቸው።
የወያኔ ሰራዊት አብዛኛዉን ግዜዉን የሚያጠፋዉ በግምገማ ነዉ። የሰራዊቱ አባላት ለግምገማ ሲቀመጡ ያላጠፉትን ጥፋት እንዲያምኑ ይደረጋሉ ደግሞም በሚያሳፍር መልኩ በጓደኞቻቸው ላይ እንዲመሰክሩ ይደረጋል። የህወሃትን ሰራዊት ከድተው አርበኞን የተቀላቀሉ ወታደሮች እንደተናገሩት፣ የሚገመገሙ የሰራውት አባላት ቅስማቸው ይሰበራል፣ ሃፍረት ይሰማቸዋል። የሰራዊቱ አባላት ሰቆቃን ጨምሮ በተለያዩ ወተደራዊ ቅጣቶች ይቀጣሉ። ብዙ ግዜ ጨለማ ቤት ዉስጥ ለብቻቸው ታስረው ድብደባና እንግልት ይደርስባቸዋል።
የሰራዊቱ አባላት ግምገማ ሲቀመጡ አላስፈላጊ የሆኑ ጸያፍ እንካስላንትያና ስድቦች ይስተናገዳሉ። ትግርኛ የማይናገሩ ወታደሮችና ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ከትግራይ ክልል በመጡ የበታች ሹማምንቶች ይሰደባሉ። ከረር ያለ ጥያቄ መጠየቅ አይቻልም። ከትግርኛ ተናጋሪዎች ዉጭ ጥያቄ የሚጠይቁ ወታደራዊ መኮንኖች ሊጠፉ ወይም ሊወገዱ ይችላሉ። በእነዚህ ሁሉ ጉዳዮች የተንሳ በወያኔ የሚታዘዘው ስራዊት ወታደራዊ ሞራል የተዳከመ ፥ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ የሚገኝ ነው፤
የሰራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖች ለአገዛዙ ታማኝ ነን ቢሉም፣ አገዛዙን ከድተው አርበኞችን ከተቀላቀሉ የምድር ጦርና የአየር ሃይል አባላት የተገኘው ማስረጃ እንደሚያመለክተው አብዛኛው የሰራዊቱ አባል በሙስና ለበለጸጉ ጄኔራሎችና በዘር ለያይቶ ለሚገዛዉ ጨቋኝ አገዛዝ ህይወቱን ለመገበር አይፈልግም። በመሆኑም ሰራዊቱ አገሪቷን ከሚቃጣባት ከማንኛውም ጠላት ለመከላከል ያለዉ ዝግጅትና ፍላጎት እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነዉ። ይህ የሚያሳን አገዛዙ ስለሰራዊቱ ጥንካሬ የሚነግረን ፕሮፓጋንዳ አደንቋሪና፥ ተስፋ የሚያስቆርጥና አሰልቺ መሆኑን አንጂ አውነታውን አንዳልሆኑ መረጃዎቹ ይጠቁማሉ።
ትግርኛ ተናጋሪ ያልሆነዉ የኢትዮጵያ ወታደር በሰራዊቱ ውስጥ ተጠቅመው እንደሚጥሉት ዕቃ ስለሚቆጠር ግዳጅ ሲላክ እንኳን እየተመረጠ ለአደጋና ለሞት ወደተጋለጠ ቦታ ነዉ የሚላከዉ። ከፍተኛ እንክብካቤና ጥበቃ የሚደረግላቸዉ የትግራይ ካድሬዎችና ጄኔራሎች ግን ምንም አይነት አደጋ ወዳለበት ቦታ አይሄዱም። በቅርቡ በኤርትራ ላይ የውያኔ ኣገዛዝ በሞከረው የወረራ ትንኮሳ በጾረና ግናባር በስራዊቱ ላይ የደረሰው ከፍትኛ ውድቀትና ሽንፈት ሳያንስ የሞቱትም ሆነ የቆሰሉት ሙሉ በሙሉ ትግርኛ ተናጋሪ ያልሆኑ የስራዊቱ የበታች መኮንኖችና ወታደሮች አንደሆኑ በቂ መረጃ ኣለ።
ተራው ወታደር ሶማሊያና ኤርትራ ድንበሮች ላይ ሲዋጋና ሲሞት፣ የህወሃት ጄኔራሎች ግን አዲስ አበባ ዉስጥ የተደላደለ ህይወት ይመራሉ። ይህም በእኤአ 1998-2000 በተካሄደው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ታይቷል። ሶማሌ ዉስጥ በየቀኑ እየሞቱ ለቀብር እንኳን የማይበቁት የኢትዮጵያ ወታደሮችና ጓዶቻቸዉ የህወሃት ጄኔራሎችና ባለሌላ ማዕረግ መኮንኖች በኮንትሮባንድ ንግድ እንደሚከብሩና በሞቃድሾ ከተማ ነዳጅ ጭምር እየሸጡ ሀብት እንደሚያካብቱ ያውቃሉ። በዚህ የተነሳ ብዙ የሰራዊቱ አባላት አለቆቻቸው በንግድ እየከበሩ እነሱ ለምን አልሻባብን እየተዋጉ ህይወታቸውን እንደሚያጡ በተደጋጋሚ ጥያቄ በማቅረብ ላይ ናቸዉ። የሰራዊቱ የበላይ አለቆች ንግድ ስለሚነግዱ በሶማሊያዉ ጦርነት እንዲቆም አይፈልጉም። እንድያዉም የወያኔ ጄኔራሎች የአልሻባብ ሚሊሺያዎች በሚንቀሳቀሱበትን አካባቢ ለመመደብ ዳጎስ ያለ ገንዘብ እንደሚከፍሉ የሚናፈስም መሆኑአ ይታወቃል።
የህወሃት ጄኔራሎች ሰማይ ጠቀስ ህንጻዎች እያሰሩና የተመድ ሰላም አስከባሪ ሆኖ ለተሰማራዉ ሰራዊት የሚከፈለዉን 25 ሺ ዶላር በየወሩ ኪሳቸዉ ዉስጥ እየከተቱ ሰራዊቱ ግን የራሱን ዩኒፎርምና ጫማ እንዲገዛ ያደርጋሉ። የሰራዊቱ ቤተሰቦች በችጋር አለንጋ ሲገረፉ የህወሃት ጄኔራሎች ልጆች ግን አዉሮፓና አሜሪካ ለትምህርት ይሄዳሉ ።
ከኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ ስድስት በመቶ ከሆነው የትግራይ ብሄር የወጡና አንወክላለን በሚሉ የትግራይ የፖለቲካ ልህቃን ላለፉት 25 አመታት የኢትዮጵያን ወታደራዊና ደህንነት ተቋሞች እንዲሁም ኤኮኖሚዉንና ቢሮክራሲውን በበላይነት ተቆጣጥረወና ይህ ነው የማይባል ኢፍትሃዊ ስራኣት በማስፈን ቀጥለዋል። በመከላከያ ሰራዊቱ ዉስጥ ካለይ እስከታች ባለዉ የዕዝና ቁጥጥር መዋቅር ዉስጥ ከክፍለጦር እስከ ጋንታ ያለዉን የአዛዥነት ቦታ ጨብጠዉ የያዙት የትግራይ ተወላጆች የሆኑት የህወሃት መኮንኖች ናቸው። የህወሃት የጦር መሪዎች ኢትዮጵያ ዉስጥ በየቦታዉ የሚፈነዳዉን የህዝብ አመጽና እምቢተኝነት በጠመንጃ ሀይል ለማዳፈን የተሾሙ ጨካኝ ነብሰ ገዳዮች ናቸው እንጂ ወታደራዊ ሳይንስም ሆነ መደበኛ ትምህርት ያልተማሩ ከዘመናዊ ውትድርና ስነምግባርና የማይተዋወቁ ናቸዉ። ይህንን ደግሞ እነሱ እንመራሃለን የሚሉት ሰራዊትም በሚገባ ያዉቅዋል።
ጆን ናጌልና ዴቪድ ኪልኩለንን የመሳሰሉ የዘመናችን የጸረ ኣማጺ ንድፈሃሳብ አፍላቂዎች እንደሚናገሩት ወታደራዊ ጉልበት ብቻውን ህዝብን ማሸነፍ አይችልም። የየጸረ ኣማጺ “” (counterinsurgency) ወታደራዊ ሃይል ስላለ ብቻ የሚደረግ ዉግያ አይደለም፥ ይልቁንም “የጸረ ኣማጺ” ማለት ህዝብ ዉስጥ ገብቶ የህዝብን ልብና ፍቅር መግዛት ማለት ነዉ። በሽምቅ ዉጊያ ጥቃት ስልጣን ላይ የወጡ የህወሃት ጄኔራሎች የህዝብን ልብና ፍቅር መግዛት አለመቻላቸዉ ብቻ ሳይሆን በዘመናዊ የጦር ስልትና ስትራቴጂ መደበኛ ውጊያ ማካሄድ የማይችሉ ወይም እግረኛ፥ ሜካናይዝድ ጦርና አየር ሃይልን አቀናጅተው መዋጋት የማይችሉ የይስሙላ ጀኔራሎች ናቸዉ።
የሽምቅ ዉግያን የሚያውቅ ሀይል “የጸረ ኣማጺ” ምንነት የማወቅ ችግር ሊኖርበት አይገባም፣ ሆኖም ስግብግቦቹ የህወሃት ጄኔራሎች እንኳን አዲስ የዉግያ ዘዴ ሊማሩ ስልጣን ላይ ያወጣቸዉን የዉግያ ስልትም የረሱ ይመስላሉ። የወያኔ ጄኔራሎች ብቻ ሳይሆኑ የህወሓት አገዛዝ እንዳለ ወታደራዊ ድል የሚጘኛዉ በወታደራዊ ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን፣ የህዝቡን ልቦና በማሸነፍ መሆኑን አያዉቁትም። የህወሃት አገዛዝ ወታደሮቹ ንጹህ ኢትዮጵያውያንን በገደሉ ቁጥር እልፍ አእላፍ ጠላቶችን እያፈሩ መሆኑን በዘረፋ የተደፈነው ህሊናቸው ዘንግቶታል። ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ የተበላባቸው በየአመቱ የሚሰጡ ስልጠናዎች እስካሁን ምንም ለውጥ አላመጡም። ህወሃት አማጽያንን ለማጥፋት በኦጋዴን፣ በጎንደር፣ ጋምቤላ የሄደበት ሂደት እጅግ አሰቃቂ፣ በአለም አቀፍ ደረጃ የተወገዘ በንጹሃን ዜጎች የተወሰደ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ፈጽሞኣል። በመፈጽመም ላይ ይገኛሉ። ለዚህም ነው በእነዚህ አካባቢዎች ለዲሞክራሲና ለነጻነት የሚታገሉ የታጠቁ ሃይሎች የሚፈሉበት አካባቢዎች የሆኑት።
የህወሃት ጀኔራሎች ለሃያ አምስት አመታት በአዛዥነት ሲቀመጡ፣ ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማሪያምና በአጼ ሃይለስላሴ ዘመን የገነባችውን ዘመናዊ የጦር ሀይል፥ የጦር ስትራቴጂና ዕዝ ሙሉ በሙሉ አፍርሰዋል። የህወሃትን ወታደራዊ ክህሎት በተመለከተ ከተስፋዬ ገብረዓብ “የደራሲው ማስታወሻ:” ላይ የተወሰደው ገለጻ እንዲህ ይላል።
ወያኔዎች ኤርትራን ለመውጋት 10 ክፍለጦር አሰማሩ፥ አንዱ ክፍለጦር ሜካናይዝድ ነበር። አንዱ ብርጌድ ደግሞ ኮማንዶ ነበር። እኤአ በ1998 ጦርነቱ ሲፈነዳ የወያኔ ሰራዊት በአራት አቅጣጫዎች ማለትም በቡሬ በዛላምበሳ፣ በጾረናና በባድሜ ጦርነት ከፈተ። የመጀመሪያው ጦርነት በጣም አስቃያሚ ነበር። የወታደራዊ እና አዛዦች ሙያዊ ብቃት በተመለከተ በጣም አሳፋሪ ጦርነት ነበር። በጣም በመጥፎ እቅድ ላይ የተመሰረተ ነበር። ለጠፋው ህይወት ለፈሰሰው ደምና ለወደመው ንብረት እስካሁን ማንም ሰው ሃላፊነት አለመውሰዱ በጣም አሳዛኝ ነው።
በደርግና በሃይለስላሴ ዘመን 30 አመታት በፈጀዉ የኤርትራ ጦርነት በግምት ከ250,000 እስከ 300,000 ወታደሮች ተገድለዋል። ይህንን ቁጥር በ1990 ዓም ከኤርትራ ጋር በተደረገውን ጦርነት በአንድ አመት ብቻ ከተገደሉት 98,000 ወታደሮችና ከቆሰሉት 194,300 ወታደሮች ጋር ስናወዳድር የህወሓት የዉግያ ስልት ምን ያህል ኋላ ቀር እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን። ከወያኔ መከላከያ ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች በግልጽ እንደሚያሳዩት በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት የወያኔ ጦር ከታጠቃቸዉ ከባድ መሳሪያዎች ዉስጥ ሁለት ሶስተኛ የሚሆነው የወደመዉ በመጀመሪያዉ ዙር ጦርነት ነበር። ይህንን በሰዉ ሀይል፥ በመሳሪያና በንብረት አክሳሪ የሆነዉን ትርጉም የለሽ ጦርነት የመሩት ሰዓረ መኮንን፣ ሳሞራ የኑስ፣ ዮሃንስ ገብረመስቀል፣ ታደሰ ወረደ እና አብርሃ የተባሉ ከወታደራዊ ሳይንስ ጋር በፍጹም የማይተዋወቁ ጀኔራሎች ናቸው።
በአገርና በህዝብ ላይ ይህንን የመሰለ በደል ያደረሱት ሳሞራ የኑስን ጨምሮ አብዛኞቹ የህወሃት ጀኔራሎች የሰራዊቱ ከፍተኛ አመራር ሆነዉ ዛሬም ድረስ አሉ።
“ለአንድ ሳምንት ውጊያ ተደርጎ የህወሃት ፕላን ሙሉ በሙሉ ከከሸፈና ከፍተኛ ጥፋት ከደረሰ በኋላ፣ ጦርነቱ የሚመለከታቸው ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳዔ ኢንፋራ በተባለ የዕዝ መቆጣጠሪያ ቦታ ላይ ከሌሎች የሰራዊቱ አዛዦች ጋር ስብሰባ ተቀምጠው ነበር። ጄኔራል ጻድቃን ስሜታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ማልቀስ ጀመሩ። ሁሉም ተሰብሳቢዎች አብረው አለቀሱ። ኢንፋራ የቀብር ቦታ መሰለች። ጄኔራል ጻድቃን ከተረጋጉ በኋላ ሌሎችን ማስተዛዘን ጀመሩ። እንዲህም አሉ፣ “በወታደራዊ ሙያዬ ብዙ ጦርነቶችን ተዋግቻለሁ፣ ብዙ ሽንፈትና ማሸንፍም አይቻለሁ። እንደዚህ ያለ ውድቀት ግን አጋጥሞኝ አያውቅም። ይህ ስብሰባ የተጠራው እነዚህን ትልልቅ ዉድቀቶች ለመመርመርና መፍትሄ ለመፈለግ ነው።” ተሰብሳቢዎቹ አንድ በአንድ እየተነሱ ለዉድቀት የዳረጋቸዉ ጦርነቱ ሲጀመር ከግምት ዉስጥ ያልገባዉ የመልክዓምድር አቀማመጥና ወታደራዊ ሳይንስን ያላገናዘበዉ የጦርነት ፕላን እንደሆነ ገለጹ። ጠላት የመሸገበት መልክዓምድር ለመከላከል እጅግ በጣም ምቹ ነበር፣ በእኛ በኩል ይህንን ጠላት የመሸገበትን አመቺ መልክዓምድር ያገናዘብ በቂ ዝግጅት አልነበረም። የጠላታችንን ብዛትና አቅም በደምብ አልገመገምንም ወይም ንቀነዋል። ጠላት መልክዓምድሩን ለራሱ በሚመች መልኩ በደምብ ተጠቅሞበታል። ይህ ከተባለ በኋላ ወደዝርዝ ሳይገባ ስብሰባው ተቋጨ። ይህንን ሃሳብ በመጠቀም፣ ከዛላምበሳ እስከቡሬ ባሉ ቦታዎች የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን አቆምን። የውጊያ አቅማችንን ለመጨመምር፣ በጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖት የሚመራው ቡድን የአየርና የምድር ሃይል መሳሪያዎችን እንዲገዛ ተላከ። በረከት ስምዖን ደግሞ የአዳዲስ ወታደሮች ምልመላ ኮሚቴ እንዲመራ ተደረገ። አባዱላ በበኩሉ የወታደራዊ ስልጠናን እንዲከታተል ተደረገ። የወታደራዊ ክፍለጦሮች ከ12 ወደ 30 በአጭር ጊዜ ማደግ እንዳለባቸዉ ተወሰነ። እስከዚያ ድረስ ግን በመከላከል ላይ ብቻ ተወስነው እንዲቆዩ ተደረገ።”
ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ በ1998-2000 ዓም የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት የህወሃት ከፍተኛ ወታደራዊ መሪዎች ከሽምቅ ውጊያ በስተቀር ዘመናዊ የመደበኛ ውጊያ ስልጠና ያልወሰዱ፣ ወታደራዊ ሳይንስ ክህሎት የሌላቸውና እንዲያዉም ብዙዎቹ ከአንደኛ ደረጃ የዘለለ ትምህርት ያልተማሩ መሆናቸዉን አስመስክረዋል። ህወሓት በእነዚህ መሪዎቹ ጦርነቱን እንደማያሸንፍ ስለተረዳ ሂዱ አታስፈልጉም “የደርግ ሰራዊት” ብሎ ያባረራቸዉን እነ ጄኔራል ተስፋዬ ሃበትማሪያምን፣ ጄኔራል በሃይሉ ክንዴን ፣ ጄኔራል ንጉሴ አዱኛን (በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ የተሰዉ)፣ እነ ጄኔራል ተጫነ መስፍንን የመሳሰሉና ሌሎችንም በብዙ ሺ የሚቆጥሩ የቀድሞ ሰራዊት መኮንኖችና ወታደሮች ዉግያዉን እንዲቀላቀሉ አድርጓል። በመጀመሪያዉ ዙር ጦርነት ለብዙ ኢትዮጵያዉያን ሞትና መቁሰል ምክንያት የሆኑት ጀኔራል ሳሞራ የኑስና ጓደኝኞቹ በከፍተኛ ደረጃ የተማሩና የብዙ ግዜ የዉግያ ልምድ ያላቸዉ ጄኔራሎች ጦርነቱን መቀላቀላቸውን ባይወዱም በሁለተኛው ዙር የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት ክፍተኛ ከኣስተዋጻኦ ያደረጉት ወያኔ አታስፈልጉም ብሎ ያባረራቸዉ ጄኔራሎች፥ የመሳሪያ ባለሙያዎች፣ የውጊያ መሃንዲሶች፣ የአየር ሃይል ፓይለቶችና ሌሎች ከፍተኛ ባለሙያዎች እንዲሁም ተራ ወታደሮች ነበሩ።
ሌላው ወያኔ የፈጸመዉ እጅግ በጣም አሳፋሪ ስራ ለአገራቸዉ ለኢትዮጵያ የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉ ወታደሮችን በወጉ አፈር እንኳን ሳያለብሳቸዉ ሜዳ ላይ ጥሎ የአዉሬ ሲሳይ እንዲሆኑ ማድረጉ ነዉ። ብዙ የአይን ምስክሮች እንደተናገሩት ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ የኢትዮጵያ ወታደር አስከሬን የጦር ሜዳ ጓዶቻቸዉንና ቤተሰቦታቸውን በሚረብሽ መልኩ በየቦታው ተጥሎ እንዲበሰብስና የአሞራ ቀለብ እንዲሆን ተደርጓል። ይህ ሁሉ አልበቃ ያለዉ የወያኔ አገዛዝ በኤርትራና ሶማሊያ ጦርነት ወቅት የሞቱ ወታደሮችን ቁጥር ጦርነቱን ለተዋጋዉ የኢትዮጵያ ህዝብ አላሳውቀም። የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ለህወሃት ሰራዊት ያለው ጥላቻ የሚመነጨው ለኢትዮጵያ ለተዋደቁ የሰራዊቱ ኣባላት ያለው ስር የሰደደ የባአድነት ስሜትና ንቀት መገለጫዎች ናቸው።
በእነዚህ ሃቆች ተመስርቶ፣ የሚከተሉትን ነጥቦች ማለት ይቻላል።
ከ90% በላይ የሆነዉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እንደ ሲቪል ወገኖቹ ከአንድ ብሄር የበላይነት ተላቅቆ ሰላም፥ ፍትህና እኩልነት በሰፈነባት ኢትዮጵጵያ ዉስጥ መኖር ይፈልጋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጽኑ ፍላጎት ምንም አይነት ጭቆናና መድሎ በሌለበት ስርዐት ዉስጥ ከአባቶቹ የተረከባትን አገር የግዛት አንድነት አስከብሮ ለሚቀጥለዉ ትዉልድ ማስረከብ ነዉ እንጂ ወያኔና ምዕራብያውያን እንደሚያስቡት ለ “ምግብ ለመኖር” ብቻ የሚዋጋ ሰራዊት አይደለም።
“ውትድርና ዲሞክራሲያዊ ሳይሆን አምባገነን ነው።” ሆኖም ትክክለኛ ውለታውን የሚያከብርለት ጠንካራ አመራር ይፈልጋል። የታችኛው ሰራዊት የበላይ አመራሩን ጀግና፣ ትክክለኛና በውትድርና ሳይንስና ዕውቀት የታነጸ ክህሎት ያለው አድርገው ለማመን ለመከተልም ይፈልጋሉ።
ወታደሩ በዘር በተመሰረተ አድሎ ሳይሆን፣ በተግባር፥ በልምድና በአገልግሎት ላይ የተመሰረተ ዕድገት፣ የደሞዝ ጭማሪና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች እንዲሰጠው ይፈልጋል።
ሰራዊቱ አገራዊ ግዳጁን በሚወጣበትና በአገልግሎት ላይ ባለበት ግዜ ሁሉ ለስራዉ የሚያስፈለገዉን ቁሳቁስ ሁሉ መንግስት የማቅረብ ግዴታ አለበት፥ ይህ ሎጂስቲክን፥ ወታደራዊ ዩኒፎርንና የምግብ አገልግሎትን ያጠቃልላል።
ሞራሉ የላሸቀና አቅምና ብቃት በሌላቸው የህዝባዊ ወያኔ ኣርነት ትግራይ ጄኔራሎች የሚመራ ሰራዊት፣ ሙሰኛና ኢፍትሃዊ የሆነን ስርዓት ማገልገል አለመፈለጉ ብቻ ሳይሆን አገሩን ከጠላት መከላከልም አይችልም። የህዝብ ትግል ሲጎመራ፣ ሰራዊቱ በዘራፊና ዘረኛ ኣዛዦቹ ላይ አመጽ ማቀጣጠልና አፈሙዙን ወደ አነዚህ ጨቋኞች መመለሱ አይቀሬ ይሆናል።
ህወሓት ዘረኛ አገዛዝ ነዉ።ኣምባገነናዊ ጸረ-ሕዝብ ስራኣት ነው። ኢትዮጵያን የሚመራዉም በኣንድ ብሔር የበላይነት ላይ በተመሰረ ኣስተሳስብና ከዚሁ በሚመነጩ ፖሊሲዎች ነዉ። የወያኔ ስርዐት የመከላከያ ሰራዊት አባላትና ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠይቀዉን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ የማይችል ስርዐት ነዉ። ህወሓት የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠይቀዉን ጥያቄ መመለስ የማይፈልገዉ የጥያቄዎቹ መልስ የሱ መጨረሻ መሆኑን ስለሚያዉቅ ነዉ።
አሁን ያለው የህወሓት ፖለቲካዊና ወታደራዊ አመራር ኢትዮጵያ ዉስጥ መሳሪያ አንስተዉ በተለያዩ ግንባሮች የሚንቀሳቀሱ አማጽያንን ለማጥፋት የሚያስችለዉ ምንም አይነት ህዝባዊ ድጋፍ የለውም። በመጠነ ሰፊ ችግሮችና ቅራኔዎች የተዘፈቀ ሰራዊት በሁሉም ኣቅጣጫ በሚጠመድ የህዝብ ትግል ኣካል ይሆናል አንጂ በሃዝብ ላይ የማያባራ መከራና ግፍ ለሚፈጽም የዘረኛና የጨቋኙ የህወሃት ኣገዛዝ መሳሪያ ሆኖ በረጅሙ ሊቀጥል ኣይችልም።
ማጠቃለያ
በህወሃት አገዛዝ ስር የሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ሞራል እጅግ የላሸቀ ነው። መንፈሱ የደከመ፣ አንድነቱ የላላ፣ በራሱ የማይተማመንንስ እርስ በእስር በጎሪጥ ኣንዲተያይ የተደረገ፡ ዘረኛና ዘራፊ ጄኔራሎች የሚያዙት ነው። እንዲህ አይነቱ ሰራዊት ደግሞ በአንድነት በረጅሙ ለመዋጋት የሚያስችለው ሆኔታ ውስጥ የሚገኝ ኣይደለም፤
ናፖሊዮን “መንፈሰ ጠንካራ ሰራዊት የራሱን ሶስት እጥፍ ወታደር ያሸንፋል’” በማለት አንድ ሰራዊት ሊኖረዉ ስለሚገባ የመንፈስ ጥንካሬ አስፈላጊነት ተናግሯል። ይህን ያለዉና ታላቅ የወታደራዊ ስትራቴጂና ታክቲክ ክህሎት አንደነበረው በሰፊው የተጻፈለት ናፖሊዮን 300,000 አባላት የለዉን “ታላቁ ሰራዊት” ይዞ የተሸነፈዉ የሽምቅ ዉግያ በገጠሙት ስፓኒሾችን በስፓንያ በሰራዊቱ ላይ ያደረሱበት ቡርቦራ ኣይነተኛ ምክነያትና ለውድቀቱም ከትልልቆቹ መንስኤዎች ኣንዱ ነበር። ከናፖሊዮን በኋላ ሽምቅ ተዋጊዎች ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙ አገሮች ዉስጥ ትልልቅ መደበኛ ሰራዊቶችን ለሽንፈት ተደርገዋል። አልጄሪያ፥ ቻይና፥ ቬትናምና በቀዝቃዛዉ ጦርነት ወቅት የነበረችዉ አፍጋኒስታን የሽምቅ ዉግያ አይነተኛ ምሳሌዎች ናቸዉ። በሽምቅ ውጊያ የደርግን ስርእት በማዳከም መቻላቸውም ከምክነያቶች ኣንዱ ሆኖ ስልጣን ላይ የወጡት የህወሃት መሪዎች ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ በአራቱም ማዕዘን የገጠማቸዉን የአማጽያን እንቅስቃሴ ማሸነፍ የሚችሉበት ምንም አይነት ህዝባዊ ድጋፍ ሰለሌላቸዉ እነሱ በመጡበት መሸነፋቸዉ አይቀርም። ህወሃት ሽምቅ ተዋጊዎች ለማጥፋት የሚያደርገው “ቆሻሻ ጦርነት” ከጦር ወንጀለኝነት ጋር ስለሚያያዝ፣ በአለም አቀፍ ማህበረሰብም ይሁን በኢትዮጵያውን መመርመሩ አይቀርም። ከአለም አቀፍ ማህበረሰብ ህወሃት የሚደረግለት ድጋፍ መቀነሱ አይቀርም። አሁን እንደሚታየው በህወሃትን ስር የሚማቅቀው ሰራዊት ጠንካራ የተቀናበረ ሽምቅ ውጊያና የህዝብ ኣልገዣም ባይነት በሁሉም የኢትዮጵያ ኣካባቢዎች ከተጠመደና ከተቀጣጠለ ኣገዛዙም “የስፓኝ ነቀርሳ” ይሆንበትና ወደመፍረክርኩ ለጥቆም ኣብዛኛው የሰራዊቱ ኣባላት ወደ ህዝብ ትግል የሚቀላቀሉበት ሁኔታ ይፈጠራል።
ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለሚገኙ ስር የሰደዱ ችግር ተጠያቂዎቹ የሆኑት የህወሓት መሪዎችና የትግራይ ጄኔራሎች ናቸዉ። የእነዚህ መሪዎችና ጄኔራሎች ዘረኝነት፥ ጭካኔ፥ ስግብግብነትና ገንዘብ ማሸሽ አገራቸዉን ዋጋ እንደሚያስከፍል ሁሉ እነሱንም ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከፍል ሊያዉቁ ይገባል። የኣምባገነናዊነትና የዘረኝነት ተግባሮች የሌላ ብሄር ዜጎችን እንደሁለተኛ ዜጋ፡ ከዚያም በታች የመቁጠር አባዜቸው፥ ለከት ያጣው ኢፍትሃዊ ተግባሮቻቸው፥ ዘረፋቸው፡ ኣፈናና ጭቆናቸው ሳቢያ ከህዝቡም ሆነ ከኣብዛው የመከላከያ ሰራዊት ኣባላት የተነጠሉ መሆናቸውን ሊያውቁ ይገባል። ይህንን ሁሉ በአይኑ የሚያየዉና የገፈትና የመከራ ህይወት ኣስከኣፍንጫው የተጋተው ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ትዕግስቱ ተሟጥቶ አልቋል። በኦሮሞ ክልል ኣየታየ የሚገኘው ህዝባዊ የቁጣ ማዕበል ፡ ዛሬ በጎንደር ዉስጥ በከፍተኛ ሁኔታ በመደገም ላይ የሚገኘው በማያሻማ ሁኔታ ይህንኑ የሚያረጋግጡ ናቸው። ትግሉ በመላ የኢትዮጵያ ኣካባቢዎች የሚዛመትባትና የሚቀጣጠልበት፡ ኣገዛዙ አውር ድንብሩ ወጥቶ የሚጨብጠውን የሚለቀውን የሚያጣበት፥ ብሎም ተፍረክሮኮና ተንኮታክቶ በህዝብ ትግል የሚንበረክክበት ጊዜ ኣሩቅ ኣይሆንም፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ለነጻነት ለፍትሃና ለአኩልነት የሚያደርገው የኣመጽ ትግልና የኣልገዛም ባይነት ትግል፥ የህዝባዊ አምቢተነንት ትግል የህወሓት ኣገዛዝ እስኪወገድ ድረስ በየኣካባቢው አንደ ሰደድ አሳት የሚቀጣጠል እንጂ የሚቆም ኣይሆንም።
ማስታወሻ፥- ለዚህ ጽሁፍ ግባት የሆኑ መረጃዎን በማሰባሰብ፡ በትርጉምና በአርማት ለተባበሩኝ የትግል ጓዶች ምስጋና ለማቅረብ አወዳለሁ።