PBS: Escaping Eritrea … [Read More...] about ካብ ውሽጢ ቤት ማእሰርታት ኤርትራ
በኢትዮጵያ ያለው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ነውን? (ክፍል አንድ)
ይገረም አለሙ | undated | ኢትዮጵያ ዛሬ
ሕገ መንግሥታዊውን ሥርዓት በኃይል ለማፈረስ የሚል ክስ በሀገራችን ተራና የተለመደ ነገር ከሆነ አመታት ተቆጥረዋል። በስፋት የታወቀው፣ ምን አልባትም የተጀመረው በቅንጅቶች ክስ ይመስለኛል። ለሥልጣን ያሰጋሉ ተብሎ የተገመቱ ዜጎችን በዚህ እየወነጀሉ በመገናኛ ብዙሀን መናገሩንም የጀመሩት አቶ መለስ ናቸው። ለነገሩ ከደደቢት እስከ ምኒልክ ቤተ መንግሥት የተሰራ የተነገረው ሁሉ የአቶ መለስና የአቶ መለስ ብቻ አንደሆነ ተነግሮን የለ።
እናም የእኛ የሆነ የምንለውም የምንሰራውም የለንም ሁሉም በአቶ መለስ ተወጥኗል ተነግሯል የእኛ ስራ የሚሆነው የርሳቸውን ማስቀጠል ነው በማለት አሳፋሪውን ነገር በኩራት የነገሩን ሰዎችም ሕገ መንግሥታዊውን ሥርዓት በኃይል ለማፍረስ የሚለውን ውንጀላ ቀጥለውበታል። ይህም ሆነና ከወያኔ ፍላጎት በተቃራኒ የተናገረ፣ የጻፈ፣ መብቴን ያለ፣ አገዛዝ በቃኝ ያለ፣ ወዘተ ሁሉ ኦነግ፣ ግንቦት ሰባት፣ አሸባሪ፣ የኤርትራ ተላላኪ ወዘተ የሚል ሰም እየተለጠፈበት፣ ሕገ መንግሥታዊውን ሥርዓት በኃይል ለማፍረስ በሚል ውንጀላ ማሰር የሥርዓቱ ዋና ተግባር ከሆነ አመታት ተቆጠሩ። ይህ የሚሆነው ግን የሚገነባም ሆነ የሚፈርስ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ሳኖር ነው። ሌላው ቢቀር ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ባለበት ሀገር ዜጎች በዘፈቀደ አይታሰሩም በሀሰት አይወነጀሉም ተቃወማችሁ ተብለው አይገደሉም።
ብዙ ዝርዝር ውስጥ ሳይገባ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት የሚለውን ቃል እንደወረደ ብንተረጉመው በሕገ መንግሰት መሰረት ላይ የቆመ መንግሥት ያለበት ሥርዓት ማለት ነው። እዚህ ላይ ሁለት መሰረታዊ ነገሮች አሉ፤ አንደኛውና ዋናው ሕገ መንግሥት ሲሆን ሁለተኛው መንግሥት ነው። የሁለቱ መኖር ብቻ ግን አንድን ሥርዓት ሕገ መንግሥታዊ ሊያሰኘው አይችልም። ይችላል ከተባለ ደግሞ የንጉሱም የወታደራዊውም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ነበር ማለት ይሆናል።
በህዝብ ውይይት ተረቆ በህዝብ ይሁንታ በጸደቀ ሕገ መንግሥት መሰረት በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሥልጣን የያዘና ራሱን ለሕገ መንግሥቱ እያስገዛ በሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ መሰረት ሕዝብን በማስተዳደር የአምስት አመት ኮንትራቱን የሚወጣ ተጠያቂነት ያለው መንግሥት ሲኖር ነው ሥርዓቱ ሕገ መንግሥታዊ ሊባል የሚበቃው።
በኢትዮጵያችን ከእነዚህ አንዱም የሌለ በመሆኑ ነው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት አለ ወይ? ብሎ መጠየቁ ግድ የሚሆነው። ሌሎቹን ትተን አንዱንና ዋናውን ሕገ መንግሥቱን ብቻ እንኳን ነጥለን ብናይ የምናገኘው ውጤት በኢትጵያ ያለው የወያኔ ሥርአት ሕገ መንግሥታዊ ሊባል የማይበቃ መሆኑን ነው። ሕገ መንግሥተን አስመልክቶ የሚነሱትን የወያኔ የፖለቲካ ፕሮግራም ግልባጭ ነው፤ የሀገራችን ህዝቦች በትግላቸው የተቀዳጁት ነው ህዝብ ያልተወያየበትና ያላጸደቀው ነው፣ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ህዝቦች ወደውና ፈቅደው ያጸደቁት ነው ወዘተ የሚሉትን ላለፉት ሀያ ዓመታት የተሰሙና አሁንም ያሉ ክርክሮችን ለግዜው አቆይተን ወያኔዎች የሚመጻደቁበትንና በመቃብራችን ላይ ካልሆነ በስተቀር አይነካም እያሉ የሚፎክሩበትን ሕገ መንግሥት ያውቁታል ወይ? ያከብሩታል ወይ? ይገዙበታል ወይ? ብለን ብንጠይቅ የምናገኘው ምላሽ አረ በፍጹም የሚል ይሆናል። ይህ ከሆነ ታዲያ ራሱ ያወጣውን ሕገ መንግሥት የማያከብር መንግሥት የመሰረተው ሥርዓት እንደምን ሕገ መነግስታዊ ስርኣት ሊባል ይበቃል የሚለው አብይ ጥያቄ ይሆናል። በሕገ መንግሥቱ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለግዜው ስንተዋቸው ግን ሕገ መንግሥቱን ዴሞክራሲያዊ፣ በህዝብ የጸደቀ፣ ወዘተ እያሉ ለሚያንቆለጳጳሱትና አሁን ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሕገ መንግሥቱ ከጸደቀ ወዲህ የተወለደ ይመስል ራሳቸው ተሞኝተው እኛንም ተጨፎኑ እናሞኛችሁ ለሚሉን ስለ ሕገ መንግሥቱ አረቃቅም ሆነ አጸዳደቅ የሕገ መንግሥት ጉባኤን በሊቀመንበርነት ከመሩት ዶ/ር ነጋሶ በላይ አታውቁምና ርሳቸው ስለ ሕገ መንግሥቱ የተናገሩትን መለስ ብላችሁ ተመልከቱ የሚል የወገን ምክር በመለገስ ነው። ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት በማለቴ እጸጸታለሁ ማለታቸውን በማስታወስ ጭምር።
አንድን ሥርዓት ሕገ መንግሥታዊ ሊያሰኙት የሚበቁ ሌሎች ጉዳዮች ሁሉ ቀርተው በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሕገ መንግሥቱን የማያከብርና ለሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች የማይገዛ ከሆነ ያ ሥርዓት ህግ መንግሥታዊ ሥርዓት ሊባል እንደማይበቃ ወያኔዎችም አሌ የሚሉ አይመስለኝም። ባይሆን እኛ የብሔር ብሔረሰብ ህዝቦችን መብት ያረጋገጥን፣ልማት ያመጣን፣ ሰላም ያሰፈንን በመሆናችን ሥርዓታችን ሕገ መንግሥታዊ አይደለም ሊባል አይችልም፣ ይህን የሚሉት ምንትሶች ናቸው፣ እንዲህ ለማድረግ የሚያስቡ ናቸው ወዘተ ይሉ ይሆናል እንጂ። (የሚሉትን መድገም አስፈላጊ መስሎ ስላልታየኝ ነው)
ሆኖም ግን ራሳቸውም ሕገ መንግሥቱን ለማጥቂያ መሳሪያነት የሚያውሉት እንጂ የሚገዙበትና ህዝብ የሚያስተዳድሩበት እንዳልሆነ፤ ስለሚያውቁ፣ እናድርግ ቢሉም የሥልጣን እድሜአቸው የሚያጥር መስሎ ስለሚታያቸው ጥያቄ ሲነሳባቸው የሕገ መንግሥቱን አንቀጾች ጠቅሰው አይከራከሩም። እኛ ግን እነሆ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስ እያላችሁ በየግዜው ዜጎችን በአሸባሪነት በጸረ ሰላምነት ወዘተ አየከሰሳችሁ የምታስሩት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በሌለበት ሀገር ነው። ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ቢኖር ሌላው ቢቀር ንጹሀን ዜጎችን በማን አለብኝነት ስም እየሰጣችሁና ወንጀል እየፈበረካችሁ፣ አባይ ምስክር እያሰለጠናችሁና ታዛዥ ዳኛ እየመደባችሁ አታስሩም ነበር፣ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እንቦቀቅላ ህጻናት ሰልፍ ወጡ፣ እኛን ተቃወሙ ብላችሁ ገዳይ ሰራዊት ማሰማራት አትችሉም ነበር፤ብታደርጉት ደግሞ ለህግ ቀርባችሁ ተገቢ ቅጣታችሁን ታገኙ፣ ከፍ ሲልም ሥልጣናችሁን ትነጠቁ ነበር፤ ይህን ሁሉ ማድረግ የቻላችሁት መንግሥቱ ለሕገ መንግሥቱ የሚገዛና ሥርዓቱ ሕገ መንግሥታዊ ባለመሆኑ ነው ብለን እንሞግታቸዋለን። ሙግታችንም እንደ እነርሱ በጡንቻ ወለድ የፕሮፓጋንዳ ዋይታ ሳይሆን የሚመጻደቁበትን ሕገ መንግሥት እየጠቀስን ይሆናል።
በማስረጃነት/መከራከሪያነት የማቀርባቸውን የሕገ መንግሥቱን አንቀጾች ለመለየት አስራ አንድ ምዕራፎችንና 106 አንቀጾችን የያዘውን “ሕገ መንግሥታችንን” እንደ አዲስ አነበብኩት ። ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እነርሱም እንደ ወያኔ የፕሮፓጋንዳ ጩኸት እንጂ ሕጋዊ ክርክር ተግባራቸው ባለመሆኑ እንጂ ብዙ ሊሰሩባቸው ይችሉ የነበሩ አንቀጾችን የያዘ ነው። የህግ ባለሙያዎችም ከቃላት አጠቃቀሙና ከአረፍተ ነገር አሰካኩ የህግ ቋንቋ መሆን አለመሆን ጀምሮ ብዙ ሊሉበት የሚችል ሆኖ ነው የታየኝ። አንተስ እስከ ዛሬ የት ነበርክ እንዳትሉኝ ብቻ። እስቲ አንቀጽ 39/ 1 ተመልከቱት፡ እንዲህ ይላል፤ “በዚህ ሕገ መንግሥት ውስጥ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ህዝብ ማለት ከዚህ ቀጥሎ የተገለጸውን ባህርይ የሚያሳይ ማህበረሰብ ነው። ሰፋ ያለ የጋራ ጸባይ የሚያንጸባርቅ፣ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልምድ ያላቸው፣ ሊግባቡበት የሚችሉበት የጋራ ቋንቋ ያላቸው፣የጋር ወይንም የተዛመደ ህልውና አለን ብለው የሚያምኑ፣ የሥነ ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓምድር የሚኖሩ ናቸው።”
መጀመሪያ ሶስቱንም ማህበረሰብ አላቸው፣ ከዛም ለሶስቱም አንድ አይነት መግለጫ ነው የቀረበው። እንዴት ነው ነገሩ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ አንድና ተመሳሳይ ናቸው፣ ከሆነስ ለያይቶ፣ ስም አበጅቶ መጥራቱ ለምን አስፈለገ? ዝርዝር ውስጥ ሳይገባ የዚህ አንቀጽ አገላለጽ ትክክል ነው፣ አይደለም በማለት ባለሙያዎች እውቀት ቢያስጨብጡን።
ነገርን ነገር ያነሳዋል ሆኖ እንጂ የሕገ መንግሥቱ ጉድለቶች የዚህ ጽሁፍ አጀንዳ አይደሉም። የተጻፈው አለመከበሩን እንዲያም ሲል አለመታወቁን በማሳየት ሕገ መንግሥት በማይከበርበት ሀገር ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ሊኖር አይችልም የሚለውን ለማሳየት ነው ወደ ሕገ መንግሥት ንባብ የገባሁት። እናም ለማስረጃነት ሊቀርቡ የሚችሉት አንቀጾች በዙብኝ፤ ቀንሼ ዋና ዋና ያልኩዋቸውን ለየሁ፣እነዚህም ጥቂት የሚባሉ አልሆኑምና በአንድ ክፍል ቢካተቱ ጽሁፉን ሊያረዝሙት ሆነ። ታዲያ አንባቢን ላለመሰልቸት በድረ ገጽ የሚወጣ ጽሁፍም የተመጠነ መሆን አለበት ብየ ስለማምን በሁለት ክፍል ማድረጉን መረጥሁ።
ስለሆነም በተከታዩ ጽሁፍ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት አለን? ለሚለው ጥያቄ ምላሹ የለም የሚል እንዲሆን የሚያበቁትን ከበሬታ ከተነፈጋቸውና አንዳንዶቹም ከነመኖራቸው የማይታወቁ ከሚመስሉት የሕገ መነግሥቱ አንቀጾች የተወሰኑትን ይዤ እመለሳለሁ። እስከዛው ግን ስለ ሕገ መንግሥት መከበር አለመከበር ሲነሳ አስቀድሞ ሊጠቀስ የሚገባውን፣ ሕገ መንግሥቱ ስለ ራሱ የበላይነትና ተከባሪነት የደነገገውን እንይና የተጠቀሱት ምን ያህል ተፈጻሚ ሆነዋል የሚለውን ሕገ መንግሥቱ ከጸደቀበት 1987 እስካሁን በሀገራችን ከሆነው ጋር በማስተያየት የየራሳችንን ብይኔ አንስጥ።
አንቀጽ 9 የሕገ መንግሥት የበላይነት
9/.1 ሕገ መንግሥቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ነው፤ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሰራር፣ እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይንም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም።
9./2 ማንኛውም ዜጋ የመንግሥት አካላት፣ የፖለቲካ ደርጅቶች፣ ሌሎች ማህበራት እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው ሕገ መንግሥቱን የማክበርና የማስከበር፣ ለሕገ መንግሥቱ ተገዢ የመሆን ኋላፊነት አለባቸው፤
በአንቀጽ 9/1 የተደነገገውን በመተላለፍ ከሕገ መንግሥቱ የሚቃረኑ አዋጆች ወጥተዋል፣ባለ-ሥልጣናት በንግግርም በድርጊትም የሚፈጽሙዋቸው ተግባራት ሕገ መንግሥቱ መኖሩንም የሚያውቁ የማይመስሉ ናቸው፤ ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ይልቅ የባለ ሥልጣናቱ ትዕዛዝ፣ በአዋጅና በመመሪያ ከሚተላለፈው በላይ ልማዳዊ አሰራር የተንሰራፋበት ሥርዓት ነው ያለን።
አንቀጽ 9/2 ላይ የሰፈረውንም ስናይ ዜጎች ተወያይተው ያረቀቁት፣ በድምጻቸው ያጸደቁትና ይሁንታቸውን የቸሩት ባይሆንም የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት እስከ ተባለ ድረስ ባይወዱትም ያከብሩታል፣ እንዲሻሻል ቢታገሉም ይገዙበታል። በአንጻሩ ባለሥልጣናቱ ህዝቡ አንዲያከብረው ሲናገሩ በማጥቂያ መሳሪያነት ሲገለገሉት እንጂ እነርሱ አክብረውት ሲሰሩ አይሰተዋልም።
በተለይ ደግሞ መሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶች ተብለው በሕገ መንግሥቱ ምዕራፍ 3 በ31 አንቀጾች ከተዘረዘሩት ድንጋጌዎች አንጻር ሲመዘኑ በሕገ መንግሥት ሳይሆን ፕ/ር መስፍን በ1997 ምርጫ ወቅት አንዳሉት በሕገ አራዊት የሚመሩ ነው የሚመስሉት። በሕገ አራዊት የሚመራ መንግሥት ያቋቋመው ሥርዓት ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ሊባል አይበቃም።
አንድዬ የማሪያም ልጅ ሞልቶ ከተረፈው ዕድሜ ሳይነፍገን በክፍል ሁለት ለመገናኘት ያብቃን። አሜን!