PBS: Escaping Eritrea … [Read More...] about ካብ ውሽጢ ቤት ማእሰርታት ኤርትራ
በኢትዮጵያ ያለው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ነውን? (ክፍል ሁለት)
ይገረም አለሙ | undated | ኢትዮጵያ ዛሬ
በክፍል አንድ ጽሁፌ አንድን ሥርዓት ሕገ መንግሥታዊ ሊያሰኙት የሚበቁ በርካታ ጉዳዮችን ትተን በሕገ መንግሥቱ ላይም የሚነሱ ክርክሮችን አቆይተን ሕገ መንግሥቱ ባለው መልኩ እንኳን የማይከበር አንዳንድ አንቀጾቹም እስከመኖራቸው የማይታወቁ መሆኑ ብቻውን ሥርዓቱን ሕገ መንግሥተዊ ሊያሰኘው እንደማይችል ጠቅሻላሁ። ለዚህ መከራከሪያ ይሆናሉ ያልኳቸውን ጭብጦችም በማንሳት ከሕገ መንግሥቱ አንቀጾች የተወሰኑትን በማስረጃነት ለማቅረብ ነበር የተሰናበትኩት።
ሕገ መንግሥቱ ከያዛቸው 106 አንቀጾች ውስጥ መከበር የተነፈጋቸውና እስከመኖራቸው የማይታወቁት ሚዛን ይደፋሉ። በተለይ ደግሞ በምእራፍ ሶስት የተገለጹት መሰረታዊ መብቶችና ነጸነቶች የተጻፉት ሕገ መንግሥቱን አማላይ ለማድረግ ብቻ ነው። ጥቂቱን በቅደም ተከተል እንያቸው።
አንቀጽ 11 የመንግሥትና የኃይማኖት መለያየት፣
አንቀጽ “11/3 መንግሥት በኃይማኖት ጣልቃ አይገባም ኃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፣ ” ይላል። ጥያቄ ላስቀድም፤ ዜጎች በመንግሥት ታጣቂዎች ሲጨፈጨፉ የሀይማኖት አባቶች ግድያውንና ገዳዮችን ማውገዝ ቀርቶ ግድያ ይቁም ብለው ድምጻቸውን ቢያሰሙ በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ መግባት ይባላል? ከሆነስ የመብት ጥያቄ የሚያነሱ ዜጎችን አውግዞ የመንግሥትን ግድያ በመደገፍ ርምጃው ተጠናክሮ ይቀጥል ብሎ መግለጫ ማውጣት መንግሥት ከጣልቃ ገብነት በዘለለ እየተቆጣጠራቸው መሆኑን አያሳይም?
የመንግሥትን በኃይማኖት ጣልቃ ገብነት ለማሳየት ብዙ ማስረጃዎች መዘርዘር ይቻላል። በዘመነ ወያኔ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሁለት ጳጳሶች ተሾመዋል። አቡነ ጳውሎስ ከአሜሪካ፣ አቡነ ማትያስ ከእስራኤል ተጠርተው። ሁለቱም ደግሞ ትግረኛ ተናጋሪዎች ናቸው። ይህ የሆነው እንደ ጀነራሎችና ቁልፍ የምኒስትር ቦታዎች ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ለሊቀ ጳጳስነት የሚመጥን ሰው ባለመገኘቱ ይሆን! አይደለም፣ አባ ደፋር አቦይ ስብሀት አቡነ ጳውሎስ ሞተው የጳጳስ ምርጫ ዝግጅት ሲደረግ የምንፈልገው ጳጳስ ካልተሾመ እኛ ትግራይ ላይ የራሳችንን ጳጳስ እንሾማለን በማለት የተናገሩት ነው እውነቱ።
የሙስሊሙንም ብንመለከት፣ ሕገ መንግሥቱን አምነውና ተማምነው የኃይማኖት ነጻነት ጥያቄ ያቀረቡ ዜጎችን አሸባሪ ብሎ ማሰር፤ የእምነቱ አባቶችን ምርጫ በቀበሌ ጽ/ቤት ማካሄድ፣ ዜጎች ያልፈቀዱትን አስተምህሮ እንዲቀበሉ ማስገደድ ወዘተ፣ ታይቷል። በሌሎች እምነቶችም እንዲህ ጎልቶ ባይወጣም ነጻ አለመሆናቸውን ከድርጊቶቻቸው መረዳት ይቻላል። በመሆኑም በሁሉም ኃይማኖቶች ውስጥ የሚታየው የመንግሥትን በኃይማኖት ጣልቃ መግባት ብቻ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠራቸው መሆኑን ነው።
አንቀጽ 16 የአካል ደህንነት መብት፣
“ማንኛውም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ መብት አለው፤” ይህ አንቀጽ በግልጽ የሚያሳየው በሀገሪቱ ውስጥ ነዋሪ የሆነ ዜጋም ሆነ አልሆነ በማንም፣ በምንም፣ መቼምና በማናቸውም ቦታ ጉዳት እንዳይደርስበት የመንግሥት ጥበቃ አንደሚያገኝ ነው። በሀገራችን እየሆነ ያለው ግን ከዚህ በተቃራኒ ጥበቃ እንዲያደርግ ግዴታ የተጣለበት መንግሥት ጉዳት አድራሽ መሆኑ ነው። ይህ ሕገ ድርጊት ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ የሚከተለውን በአንቀጽ 18/1 የተደነገገውንም የሚጥስ ነው።
አንቀጽ 18 ኢሰብዓዊ አያያዝ ስለመከልከሉ፤
“18/.1 ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት ኢሰብዓዊ ከሆነ ወይንም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው፤ ” ሰሞኑን በማህበራዊ መገናኛ የተሰራጩት የግድያና የደብደባ ምስሎች ብቻ ለዚህ በቂ ማስረጃዎች ይሆናሉ። እናክል ከተባለም በማእከላዊ ምርመራና በየእስር ቤቶች በዜጎች ላይ (በተለይ በፖለቲካ አስረኞች ላይ) የሚፈጸሙ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ይጠቀሳሉ። ኢሰብዓዊ ድርጊት ተፈጸመብን የሚል አቤቱታ የሚቀርብላቸው ፍርድ ቤቶች ሰምቶ ዝም ባይ መሆናቸውም ተጨማሪ ማስረጃ ይሆናል። እነዚህ ድርጊቶች አይደለም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መንግሥት የሚባል ተቋም እንኳ የለሌበት ባለሥልጣኖች ያሻቸውን የሚሰሩበት ሥርዓት ነው የሚመስለው።
አንቀጽ 20 የተከሰሱ ሰዎች መብት
“20/3 በፍርድ ሂደት ባሉበት ግዜ በተከሰሱበት ወንጀል እንደ ጥፋተኛ ያለመቆጠር በምስክርነት እንዲቀርቡም ያለመገደድ መብት አላቸው፤” ይሄ አንቀጽ እስከመኖሩም የሚታወቅ አይመስለኝም። ዜጎች ወንጀል ተፈብርኮላቸው ተይዘው ገና ማእከላዊ ሳይደርሱ ባለሥልጣናት በመገናኛ ብዙኃን ብቅ እያሉ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር አውለናል ይላሉ። ፈጸሙዋቸው የሚሉዋቸውን የፈጠራ የወንጀል አይነቶች በመዘርዘርም በቂ መረጃና ማስረጃ አለን በማለት ይፎክራሉ፤ ነገሩ በዚህ ብቻ ሳያበቃ ዶክመንተሪ ፊልም ተቀነባብሮ በኢቲቭ ይተላለፋል። በዚህ ሁኔታ ታሳሪዎቹ ገና ሳይከሰሱ ጉዳያቸው ፍርድ ቤት ሳይቀርብ ከተያዙበት ቅጽበት ጀምሮ ጥፋተኛ ይባላሉ፤ ፍርድ ቤቱም ይህንኑ ያጸድቃል። ታዲያ ይህን የሚያደርጉ ባለሥልጣኖች የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20/3 ድንጋጌን ያውቃሉ ማለት እንደምን ይቻላል?
አንቀጽ 25 የእኩልነት መብት፤
“ሁሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል ናቸው፣ በመካከላቸውም ማንኛውም አይነት ልዩነት ሳይደረግ በሕግ እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል፤ በዚህ ረገድ በዘር፣ በብሔር፤ ብሔረሰብ፤ በቀለም፣ በጾታ፣ በቋንቋ በኃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ አመጣጥ፣ በሀብት፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ ዋስትና የማግኘት መብት አላቸው። ”ይሄ ተግባራዊ ስላለመሆኑ ለማስረዳት መሞከር ለቀባሪው ማርዳት ይሆናል።
አንቀጽ 39 የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብት፣
“39/.3 ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ህዝብ ራሱን የማስተዳደር መብት አለው። ይህ መብት ብሔር፣ ብሔረሰቡ ህዝቡ በሰፈረበት መልክዓምድር ራሱን የሚያስተዳድርበት መንግሥታዊ ተቋማት የማቋቋም እንዲሁም በክልልና በፌዴራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብትን ያጠቃልላል።” ሚዛናዊ ውክልና ያገኛል የሚለውን ብቻ እንኳን ለይተን ብናይ ይህ አንቀጽ አስታዋሽ የለሽ መሆኑን ነው የምንረዳው። ሚዛናዊ ሲባል ቁጥር ብቻ አይደለም፣ ይህን ያህል ሚኒስትር ከዚህኛው ብሔረሰብ አለ ማለትም ሚዛናዊ የሚለውን አያሟላም። የክልል መስተዳድር ማቋቋምም ብቻውን ራስን የማስተዳደር መብትን አያጎናጽፍም፣
አንቀጽ 46 የፌዴራል ክልሎች፤
“46/.1 ክልሎች የሚዋቀሩት በህዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነት እና ፈቃድ ላይ በመመስረት ነው፣” ፈቃድ የምትለው ቃል ባለቤት የላትም፤ ሆን ተብሎ ወይንስ ተዘንግቶ? ማነው ፈቃጁ? በምን መንገድስ ነው የሚፈቅደው ? ጥያቄው እንዳለ ሆኖ አሁን ያለው የፌዴራል አዋቃቀር ሲከናወን በዚህ አንቀጽ የተገለጹት የህዝብ አሰፋፈር ማንነትና ፈቃድ እስከነመኖራቸውም ተዘንግተው ቋንቋ ብቸኛ መስፈርት ተደርጓል። ደቡብ ክልል ሲታይ ደግሞ ይሄም አልሰራም፣ በአንድ ሀገር ሁለት አይነት የፌዴራል አወቃቀር።
አንቀጽ 50 ስለ ሥልጣናት አወቃቀር፣
“50./ 8 የፌዴራል መንግሥትና የክልሎች ሥልጣን በዚህ ሕገ መንግሥት ተወስኗል። ለፌዴራል መንግሥቱ የተሰጠው ሥልጣን በክልሎች መከበር አለበት፣ ለክልሎች የተሰጠው ሥልጣን በፌዴራል መንግሥት መከበር አለበት።” ክልሎች ይህን አንቀጽ የሚጥሱበት አቅምም ነጻነትም የላቸውም። የፌዴራል መንግሥቱ ግን የክልሎችን ሥልጣን ማክበር አይደለም ከትግራይ ክልል በስተቀር በሌሎቹ ክልሎች ያሻውን ነው የሚያደርገው። የየክልሎቹን ባለሥልጣናት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚሾም የሚሽረውም እሱ በመሆኑ የክልሎች ሥልጣን ከወረቀት ያለፈ አይደለም።
በዚህ አድራጎቱም የሚተላለፈው በሕገ መንግሥቱ የሰፈረውን የክልሎች ሥልጣን ብቻ ሳይሆን ለፌዴራል መንግሥት የተሰጠውንም ሥልጣን ነው። ለዚህ ደግሞ አሁን እየሆነ ያለ ተጨባጭ ማረጃ ላቅርብ። አንቀጽ 51 በንኡስ አንቀጽ 14 ላይ “ከክልል አቅም በላይ የሆነ የጸጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም በክልል መስተዳደር ጥያቄ መሰረት የሀገሪቱን የመከላከያ ኃይል ያሰማራል፣” በማለት ለፌዴራል መንግሥቱ ሥልጣን ይሰጣል። ነገር ግን በወረዳ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ህጻናት ሰልፍ ወጡ ሲባል እንኳን የሚዘምተውና የሚገድለው የመከላከያ ኃይሉ ነው። ጸጥታ ሳይደፈርስ ክልሉ ከአቅሜ በላይ ነው ብሎ ሳይጠይቅ።
ይህ ደግሞ ሌሎች የሕገ መንግሥቱን አንቀጾች በተጨማሪነት የሚጥስ ተግባር ነው። የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 52/2/ሰ “የክልሉን የፖሊስ ኃይል ያደራጃል፣ ይመራል፣ የክልሉን ሰላምና ጸጥታ ያስጠብቃል፤” በማለት ሥልጣን የሰጠው ለክልል መስተዳድሩ ሆኖ ኮሽ ባለ ቁጥር መከላከያ ማዝመት የክልሎችን ሥልጣን መጣስ የፌዴራል መንግሥቱንም የሥልጣን ገደብ አለማክበር ነው። የዚህ አድራጎት ሕገ ወጥነት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 87/3 የሰፈረውን “የመከላከያ ሰራዊት የሀገሪቱን ሉአላዊነት ከመጠብቅ በተጨማሪ በዚህ ሕገ መንግሥት መሰረት በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የሚሰጡትን ተግባሮች ያከናውናል፣” የሚለውንም የሚጨምር ነው። ላለፉት ስምንት ወራት በኦሮምያ በቅርቡ በአማራ የተሰማራው የመከላከያ ኃይል በፌዴራል መንግሥቱ ማን አለብኝነት እንጂ ወይ ክልሎቹ ጠይቀው ወይ የአስቸኳይ ግዜ ታውጆ አይደለም።
ስለ መከላከያ ካነሳሁ አይቀር አንድ አንቀጽ ላክል። አንቀጽ 87/1 “የሀገሪቱ የመከላከያ ሰራዊት የብሔሮች፣ የብሔረሰቦችና የህዝቦችን ሚዛናዊ ተዋጽኦ ያካተተ ይሆናል” ይላል። ሚዛናዊ ሲባል በአዛዥነቱም በታዛዥነቱም ቦታ ነው። ሕገ መንግሥት ጥሳችሁ ጀነራል እናንተ ብቻ ሆናችሁ ሲባሉ በትግሉ ወቅት ልምድ ያካበትን ስለሆነ ምንትስ ምንትስ እያሉ የሚያሰሙት ጩኸት ይህን አንቀጽ ላለማክበር ምክንያት ሊሆን አይችልም። በመጀመሪያው ክፍል በጠቀስኩት አንቀጽ 9/1 ሕገ መንግሥቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ነው፣ ማንኛውም ሕግ ልማዳዊ አሰራር እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም” ተብሎ የተደነገገው አክባሪ ቀርቶ አስታዋሽ አላገኘም እንጂ አንዲህ አይነቱ የማን አህሎኝነት ድርጊት እንዳይኖር ነበር።
አንቀጽ 89 ኢኮኖሚ ነክ ዓላማዎች፤
“89/2 መንግሥት የኢትዮጵያውያንን የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ለማሻሻል እኩል እድል እንዲኖራቸው ለማድረግ ሀብት ፍትሀዊ በሆነ መንገድ የሚከፋፈልበትን ሁኔታ የማመቻቸት ግዴት አለበት፤” ጽድቁ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ የሚያስብል አንቀጽ ነው። የተጠቀሰው ሁሉ ቀርቶ ዝርፊያው በቆመ።
“89/5 መንግሥት መሬትንና የተፈጥሮ ሀብትን በህዝብ ሰም በይዞታው ሥር በማድረግ ለህዝቡ የጋራ ጥቅምና እድገት እንዲውሉ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፤” ከዚህ አንቀጽ ተግባራዊ የሆነው መንግሥት በይዞታው ስር ማድረጉ ብቻ ነው። መሬታቸውን የሚቀሙት ዜጎች ተጎጂዎች ናቸው። አካባቢውም ሆነ አጠቃላይ ሀገሪቱ የሚያገኙት ጥቅም የለም። ተጠቃሚዎቹ በዝምድና ተሰባስበው፣ በጋብቻ ተሳስረው በፖለቲካ አስተሳሰብ አንድ ዓላማ ይዘው ሀገሪቱን እየገዙ ያሉት ጥቂት በጣም ጥቂት ሰዎች ናቸው።
አንቀጽ 102 ምርጫ ቦርድ
“102/1 በፌዴራልና በክልል የምርጫ ክልሎች ነጻና ትክክለኛ ምርጫ በገለልተኝነት እንዲካሄድ ከማንኛውም ተጽእኖ ነጻ የሆነ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ይቋቋማል፤” ሕገ መንግሥቱ ይህን ቢልም የነበረውና አሁንም ያለው ምርጫ ቦርድ ምን እንደሆነ የሚታወቅ ነው። ወያኔ ያለ ምርጫ የሥልጣን ቡራኬ እንደማያገኝ፤ በሕገ መንግሥቱ በተደነገገው መሰረት ነጻ ምርጫ ቦርድ ቢቋቋም ደግሞ እያሸነፈ ሥልጣኑን ማስቀጠል እንደማይችል ስለሚያውቅ፣ የሚያዘውን ምርጫ ቦርድ አቋቋሞ በየአምስት ዓመቱ ምርጫ እያካሄደ ሥልጣኑን ያድሳል።
ወያኔ ሕገ መንግሥቱን አክብሮ ነጻ ምርጫ አስፈጻሚ ማቋቋም ቀርቶ ምርጫ ቦርድ በነጻነት የሚሰራ ተቋም ሆኖ ይደራጅ ብሎ መጠየቅን ሕገ መንግሥታዊውን ሥርዓት በኃይል ለማፍረስ መንቀሳቀስ ነው ብሎ ይወነጅላል። ለዚህ ደግሞ የቅንጅቶችን የክስ ፋይል ማየት ይቻላል።
ብዙ መጥቀስ ቢቻልም ሕገ መንግሥቱ እየተከበረ ላለመሆኑና አንዳንዶቹ አንቀጾቹም ጭራሽ ከነመኖራቸው የማይታወቁ ስለመሆናቸው የቀረቡት በቂ ማሳያ ይመስሉኛል። በመሆኑም ሕገ መንግሥታዊ ሊያሰኙት የሚችሉት ሌሎች መመዘኛዎች ቀርተው ራሱ ለራሱ አንዲመቸው አድርጎ የጻፈውንና በሻው መንገድ ያጸደቀውን ሕገ መንግሥት የማያከብር መንግሥት ያቋቋመው ሥርዓት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ሊባል አይበቃም። ስለሆነም ትግሉ ወያኔ እንደሚለው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት የማፍረስ ሳይሆን የአገዛዝ ሥርዓትን አስወግዶ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን የመትከል ነው።