PBS: Escaping Eritrea … [Read More...] about ካብ ውሽጢ ቤት ማእሰርታት ኤርትራ
ለኢሕአደግ መንግሥት የቀረበ አቤቱታና ምክር –
ጣሰው ደስታ (ኮሞዶር) | January 8, 2017 | zehabesha.com
በአሜሪካ ወዳጆቻችንም እንደተጠየቁት፣ ሁለተኛ፣ እናንተም በአቶ አርአያ ዘሪሁንና በአቶ አሰፋ ማሞ አማካኝነት እንደጠየቃችሁኝ፣ ሦስተኛ፣ በልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም አበረታችነት፣ አራተኛ፣ በክቡርደጃዝማች ዘውዴ ገብረሥላሴ ጠያቂነት አብሬአችሁ አገሬ እንድገባ በ1991 እንደ አውሮፓያን አቆጣጠር ተጠይቄ እንደነበር ታውቃላችሁ።
አብሬአችሁ አገሬ ያልገባሁትና የመመለሱን ሃስብ ያልተቀበልኩበት ምክንያት እንደሚከተለው ነው። የምወዳት ባለቤቴ፣ የምወዳቸው የባለቤቴ አባትና እናት በጠቅላላውም የምወደውና የማከብረው የትግራይ ሕዝብ አካልና ልጆቹ መሆናችሁን በማቃለልና ከቁምነገር ያለመቁጠር ሳይሆን የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመግዛት በወቅቱ የቀየሳችሁትን ፖሊሲ በማስተዋል ነበር። የቀየሳችሁት ፖሊሲ ፋሽሽት አገራችንን ሲወር ከቀየሰው ፖሊሲ ጋር በጣም ተመሳሳይ ከመሆኑም ባሻገር መንግስቱ ኃይለማሪያም ጥሎላችሁ የሄደውን የኮሚኒስት አሰራር ያለሐፍረት እንደምትቀጥሉበት ስላመንኩ ነው።
ያደኩበትንና ለከፍተኛ ማዕረግ የበቃሁበትን የምወደውን የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል በትንንሽ ጀልባዎች ጀምረን ከ 1955-1991ዓም ድረስ ለ 36 ዓመት በኖርዌይ በታላቋ ብሪታያናና በአሜሪካ እርዳታ የተቋቋመውን በብዙ ጎበዝ ኢትዮጵያዊያኖችና ኤርትራዊያን ጉልበት የተገነባውን የባሕር ኃይል የማፍረስ ዕቅዳችሁ መሆኑን በመረዳት፣ በሌለ ገንዘብ በወዳጆቻችን በስዊድንና በአሜሪካን ዕርዳታ የተቋቋመውን የአየር ኃይል እንደምትበትኑ ስላወኩኝ፣ በከፍተኛ በድሃው ሕዝብ ወጪ ሰልጥነውና ተምረው የቆዩትን የጦር ኃይልንና የፖሊስ ሠራዊትን ለማፍረስ እንደወሰናችሁ ስለተገነዘብኩ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያን የባሕር ግዛቷን ለማሳጣት፣ ያለሕዝብ ፈቃድ ለማስገንጠል ስለተነሳችሁ፣ ከእናንተ ጋር በመተባበር መቆምና መስራት ኢትዮጵያዊነቴን መካድና በአገሬ ላይ መሸፈት ሆኖ ስለተሰማኝና ስላስችገረኝ ነው።
የታሪክ ኃላፊነትን ተቀብላችሁ መንግሥት ከሆናችሁ በኃላ፣ ሕዝቡን በጎሳ፣ በቋንቋ፣ በክልል ከፋፍላችሁ ሕዝቡ በክፉ እንዲተያይ አደረጋችሁ፣ አገራችንን ከጎሳችሁ በወጡ የአገዛዝና የአመራር ትምሕርት ስልትና ልምድ በሌላቸው ካድሬዎች ለመግዛት ወሰናችሁ፣ ይህም አሰራር ብዙ ኢትዮጵያዊያንን ከማሳዘኑም በስተቀር ብዙውን ሕዝብ የሁለተኛ ዜግነት ስሜት ተቋዳሽ እንዲሆን ከማድረጉም በላይ ባዕድነት እየተሰማው ተጨንቆ የሚኖር ሕዝብ እንዲሆን አድርጎታል። ይህንን ድርጊቶች ስመለከታቸው ታላላቅ መሪዎቻችን፣ እነንጉሥ ኢዛና፣ አጼ ካሌብ፣ አጼ ዮሃንስ ከወጡበት የትግራይ ምድር ወጣታችሁ ወይም ተፈጣራችሁ ለማለት አስቸግሮኛል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ስልጣን ከያዛችሁ ጀምሮ ሕዝቡ የሚያቀርብላችሁን ጥያቄ፣ ለምሳሌ ያህል በ1984 በየአውራጃው ህዝቡ ላቀረበው የጎሳ ተቃውም ፖለቲካ የተሰጠው የኃይል እርምጃ ፣ የቀድም የመከላከያ ሠራዊት ባልደረቦች ላቀረቡት አቤቱታና ልመና የተሰጠው የጥይትና የቦንብ መልስ ፣የሲዳማ ሕዝብ መብቱን ስለጠየቀ የደረሰበት ጭፍጨፋ፣ የዲሞክራሲ መብቱን ለማስከበር ለሰላማዊ ሰልፍ በወጣው ሕዝብ የምትፈጽሙት ጭፍጨፋ፣ በቅርቡ በወለጋ፣ በአርሲ፣ በሐረር፣ በሸዋ፣ በባሌ፣ በቤገምድርና በጎጃም በጠቅላላው የመብት ጥያቂዎች ላይ የተወሰደውና በመወሰድ ላይ የሚገኘው የኃይል እርምጃ፣ በ ሺ የሚገኙ ሰዎችን በእስር ቤት በማጎር መስራት የሚችሉትን የውጭና የሀገር ውስጥ ሰዎችን በማማረር ስራ ሊፈጥሩ የሚችሉትን በማጉላላት፣ለታዳጊ ትውልድ በቂ ስራ መፍጠር ስላልቻላችሁ፣ ኢትዮጵያን ለሰው የማትመች ሃገር አድርጋችሁአታል።
የምወለደው ከኦርሞው፣ ከአማራውና ከጉራጌው ጎሳና ቤተሰብ ቢሆንም በሞት በተለየችኝና፣ ልጆችን ባፈራችልኝ የ33 ዓመት ጥሩ ጓደኛዬ በነበረችው ባለቤቴና፣ ለእናቷም፣ ለአባቷም ባለኝ ፍቅር የትግራይ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ያለውን ፍቅር አውቃለሁ። በተጨማሪም ከትግራይ ኢዲዩ (EDU) ታጋዮች ጋር ባሳለፍኩት ጊዜ የትግራይ ሕዝብ ምን ያህል ኢትዮጵያን እንደሚወድም አውቃለሁ። በሰሜን ኢትዮጲያ ደርግን ለመጣል በተዋጋሁበት ዘመን ሁሉ የትግራይ ሕዝብ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ሉዓላዊነት፣ እንደዚሁም ለክብሯ የቆመና በሐገር ፍቅር ስሜት የተገነባም፣ አኩሪ ጨዋና የኢትዮጵያ የታሪክ መሰረት መሆኑን ተገንዝቤአለሁ። ኢድዩ(EDU) ውስጥ የነበሩ የትግራይ ታጋዮች ለኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላም ይሰጡና ያሳዩ የነበረው ፍቅርና አክብሮትንም አስታውሳለሁ። ባንዲራውን ከራስጌው አድርጎ የሚተኛ አገር ወዳድ መሆኑንም አውቃለሁ። የትግራይ ሕዝብ የኢትዮጵያን ባንዲራ እንደዚህ አንደሚያከብር እንዳልነበረ እናንተ ወያኔዎች ግን የኢትዮጵያን ባንዲራ የጭነት አህያ የጀርባ ልብስ በማድረግና፣ በመረጋገጥ፣ በማቃጠል ያሳያችሁት የንቀትና፣ የጥላቻ ስሜት ከየት እንደመጣ ግራ የሚያጋባ ነው።
ይህንን የመሳሰሉ ታላላቅ መሪዎችን ያፈራች የትግሬ መሬት ዛሬ ሕዝቡን ዕርስ በዕርስ የሚያጋጩትንና ሌት ተቀን የሚያስጨንቁትን እነስብሃት ነጋን፣ አባይ ጸሃዬን፣ ስዩም መስፍንንና መሰሎቻቸውን ዘረኞችን ማፍራቷ በጣም ይደንቃል። የትግራዩ ጀግና ራስ አሉላ አባ ነጋ ኢትዮጵያ ሀገራችንን አሳድገውና ለዓለም አስተዋውቀው ጠላቶቻችንን እያሳፈሩ የመለሱ የሃገራችን ታልቅ ባለውለታ ናቸው። በንጉስ ኢዛናና በአጼ ካሌብ መንግሥት ኢትዮጵያ በዓለም ከታወቁት መንግስታት ደረጃ የደረሰችም ነበረች። እስከ ህንድ ውቅያኖስ ድረስ የባህርና የንግድም መስመር ነበራት። በተጨማሪም የክርስትና ሃይማኖትን በመቀበልና በማስፋፋት ከቀይ ባህር ማዶ ድረስ ያሻገረችና ራሷን ቀና ያደረገች የስመ ጥሩዎች አገር ነበረች።
አጼ ዮሐንስ ግብጾች የኢትዮጵያን ሕዝብ በግድ ለማስለም በሞከሩበት ዘመን አይገባም በማለት ሁለት ጊዜ ጦርነት ከፍተው፤ ሁለቱንም ጦርነት ጉራና ጉንዳጉንዲ በተባሉ ስፍራዎች ላይ ከጠላት ጋር ገጥመው በሁለቱም ጦርነቶች ማሸነፋቸው የሁሉም አትዮጵያዊ ኩራት ነው። አጼ ዮሐንስን በ1881 ዓም ደርቡሾችን ከጎንደር ሲያስወጡ መተማ ላይ ለአገራቸው አንገታቸውን የሰጡ ጀግና ንጉሥ ናቸው። የሚገርመውና የሚደንቀው እነዚህ ስመ ጥሩ መሪዎች የወጡባትን የትግራይን ምድር የወያኔ አመራር ትግራይ የኢትዮጵያ አካል አደለችም፣ እኛም ኢትዮጵያዊ አይደለንም፣ ዓላማችን የኢትዮጵያን ብሔረሰቦች አናክሰንና አበጣብጠን፣ በተለይም ኦሮሞውንና አማራውን፣ አለያይተን ግማሽ ጎንደርንና ግማሽ ወሎን ወደ ትግራይ ጠቅልለን፣ ታላቂቷ ትግራይን እንመሰርታለን የሚል ከንቱ ሐሳብን ይዞ መጓዙ ከሓዲነት ነው።
ክቡራንና ክቡራት የኢሐድግ ባለስልጣናት፤
በዋናነትና በቀዳሚነት የማሳስባችሁ የእናንተ እኩይ ድርጊት የትግራይን ሕዝብ በሌላው ኢትዮጵያዊ እንዲጠላ እያደረገ ነው። በዚህም አጋጣሚ ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቼንና ወገኖቼን መምከር የምፈልገው ከተልባ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ እንዳይሆን ሰውን በትግሬነቱ ብቻ ከመጥላት እንቆጠብ። እናንተም የግል ሐብት ለማካበትና የማያዋጣና ያልታሰበበት ትንሽ ትልም በመያዝ ተወዳጁን የትግራይ ሕዝብ ለብጣሽ መሬት ስትሉ ከጎረቤቶቹ ከጎንደርና ከወሎ ህዝብ እንደዚሁም ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ደም ለማቃባትና ለማፋሰስ የምትሰሩትን የተንኮል ስራችሁን እባካችሁ አቁሙ። አሁን በምታደርጉት ህገ ወጥ አሰራር ብዙውን ህዝብ መከራ እንደምታስከትሉበት እወቁት። ኢትዮጵያ ሁለት
ቦታ ከተከፈለች ከዛሬ 25 ዓመት ጀምሮ የፈጠራችሁትን መዘዝ ጥላቻ አይታችሁ መማር ሲገባችሁ እስከ ጭራሹ ሃገሪቷን ዘጠኝ ቦት ለመበጣጠቅ መዘጋጀታችሁ የውድቀታችሁ ማብሰሪያ ምልክት ነው።
የዕርስ በርስ እልቂት እንዳይቀጥል ህዝቡንም ከዚህ አሳስቢና አስጊ ሁኔታ ማውጣት የናንተ ኃላፊነት መሆኑንንም አትዘንጉ። አሁን በምንገኝበት ጊዜ ሃይሉም አቅሙም ከማንኛውም በላይ ከእናንተ ዘንድ ስለሚገኝ ለጉዳዩ መፍትሄ ለመስጠት በቀደምትነት የምትችሉት እናንተ ስለሆናችሁ መፍትሄ ለመሻት ተጣጣሩ። መፍትሄ ለመስጠት የሚጎድላችሁ ነገር ቢኖር ማን አለብኝነትና ጥጋብ ብቻ ነው። ስለዚህ ጥጋባችሁን እልሐችሁን ተቆጣጥራችሁና አብርዳችሁ በተዘረፈ ቤት ኪራይ፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ከቻይና በተገኘ ብድር ፣ከአሜሪካ፣ ከእንግሊዝ፣ ከካናዳና ከቻይና በተለገሰ ጠመንጃና ጥይት በኃይል መመካትንና መተማመን አቁማችሁ፣ ከህሊናችሁ ጋር በመታረቅ፣ የተሸከማችሁትን የህዝብ ሃላፊነትና አደራ ተገንዝባችሁ፣ ሕዝቡን በፍቅር ልብ፣ በፍቅር አይን፣ በፍቅር አንደበት፣ ቀርባችሁና የጥጋብ አነጋገራችሁን አቁማችሁ፣ ዕርቅ፣ ሰላምና ብልጽግናን ለመፍጠር ሞክሩ። በጉልበትና በኃይል ለመፍታት የምታደርጉት ሙከራ ሁሉ ችግሩንን ከማባባስ በስተቀር መፍትሄ እንዳልሆነ አይታችኃል ብዬ አምናለሁ። ይሄንን የመሰለ የተንኮል ስራችሁን እርግፍ አድርጋችሁ ትታችሁ ኩራታችሁን ዋጥ በማድረግና ጥፋታችሁን አርማችሁ ከሕዝቡ ጋር ዕርቅና ሰላም እንድትፈጥሩ ይሁን።
በግርማዊ ቀዳማዊ ሐይለሥላሴ መንግስት ስደትና መታረዝን የማያውቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንሆ 42 ዓመት ሙሉ ተጉላላ ። ኢትዮጵያ የሶሻሊዝምና የጎሳ መሞከሪያና መለማመጃ ከሆነችበት ጀምሮ ከፍተኛ የስነልቡናዊ፣ የሃይማኖታዊ፣ የማህበራዊ፣ እንዲሁም የኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ ገብቷል። ከዚህም ባሻገር ሰባዊ መብቱን ተገፎ፣ መሬቱና ንበረቱን ተወርሶ፣ መሳሪያውን ፈትቶ ነጻነትና እኩልነቱን ተገፎ፣ በይስሙላ ምርጫ አውቆና ፈርቶ እየተደለለ በካድሬዎች፣ በጆሮ ጠቢዎች፣ በፖሊሶች፣ በወታደሮች እየተረገጠ በመጉላላት ይኖራል።
በሃይል በመተማመን ከሕዝብ ለቀረበው ጥያቄ የወሰዳችሁት እርምጃ መጨረሻው የሚያምር አይሆንም። አሰራራችሁ ከሕዝቡ ጋር ሆድና ጀርባ ያደረጋችሁ ስለሆነ ይህንን ለማስተካከል የድሮውን አሰራር ለውጣችሁ ሆደ ሰፊ ከሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር መታረቅ ጊዜው ነገ ሳይሆን አሁን ነው። በጨዋና በትልቅ ሰው አሰራር ስነምግባር በተሞላበት፣ ትሕትና በታከለበት፣ መንገድ ቀይሳችሁ አገራችንን በሰላም ለማስኬድ ትችላላችሁ።
ባለፉት 42 ዓመት በሶሻሊዝምና በጎሳ ፖለቲካ ሙከራ በአገራችን ህዝብ ላይ የደርሰው ስደት መከራና ዕልቂት በፋሺሽት ኢጣልያ ከደርሰው ዕልቂት እጅጉን የላቀ ነው። መክሮና ተመካክሮ አንተ ትብስ እኔ ትብስ ተባብሎ መፍትሄ መሻት ብልሕነት ነው። ይህ ሳይሆን ቀርቶ አንድ ቀን የእርዳታው ገንዘብ ሲቆም፣ የዲያስፖራው ስጦታ ሲደርቅ፣ የቻይናው ብድር ሲታገድ፣ ከማዘናችሁ በፊት አሁኑኑ ማሰብና ኢትዮጵያን ከጥፋት ማውጣት የሚገባ ነው። እግዚአብሔር ልቦናውን ይስጣችሁ።