PBS: Escaping Eritrea … [Read More...] about ካብ ውሽጢ ቤት ማእሰርታት ኤርትራ
የሃገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታና የመፍትሔ ሃሳቦች
ሌ/ጄ ፃድቃን ገ/ትንሳኤ | July 24, 2016 | Horn Affairs (Amharic)
መግቢያ
ከሃያ አምስት ዓመት ኢህአዴግ የደርግን መንግስት በጦርነት አሸንፎ የሀገራችንን ፖለቲካዊ ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ፤ ቀስ በቀስ እያደጉ የመጡ ፖለቲካዊ ችግሮች በግልፅ ጎልተው መታየት ጀምረዋል፡፡ አሁን ገዥው ፖርቲና ፖርቲው የሚመራው መንግስትም የችግሮቹን መኖር አምኖ ለመፍታት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ መንገር ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ይህ ሁኔታ ለማንኛውም የሀገሩን ደህንነትና ሰላም፤ ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ማህበራዊ ብልፅግና፤ ለሚመኝ ሀገር ወዳድ ዜጋ ያሳስባል፡፡ ከዚህ አንፃር የተለያዩ አስተያየቶች እየተደመጡ ነው፡፡
የትጥቅ ትግሉ ከተጠናቀቀ በኋላ ያኔ ሁኔታው በፈቀደው መሰረት በህዝብ ተሳትፎ ሕገ መንግስት አፅድቀን በዚህ ሕገ መንግስት እየተመራን መጓዝ ከጀመርን ሁለት አስርት ዓመታት በላይ አስቆጥረናል። በነዚህ ያለፍንባቸው ዓመታት ብዙ የተመዘገቡ ድሎች ያሉ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ መሰራት ያለባቸው ብዙ ጉዳዮችም አሉ። በዚህ ፅሁፍ በዋናነት መሰራት በሚገባቸው ጉዳዮች በተለይ ደግሞ የሃገራችን የፖለቲካ ሁኔታ፣ የተረጋጋ ለኢኮኖምያዊ እድገትና ለማህበራዊ ብልፅግና የተመቻቸ እንዲሆን ለማስቻል የፖለቲካ ስልጣን በሰላማዊና ዴሞክራስያዊ መንገድ ለአሸናፊ ፖለቲካዊ ሃይል እንዲተላለፍ ለማስቻል፣ አሁን የሚታየውን ያለመረጋጋት በፖለቲካው ስራ ምን ቢሰራ የተሻለ መረጋጋት ሊፈጠር ይችላል፡፡ በሚለው ጉዳይ ላይ ሃሳቤን ለማካፈል ነው።
ይህ አጭር ፅሁፍ ስድስት ክፍሎች ይኖሩታል፡፡ የመጀመሪያው ፖለቲካዊ ችግሮቹ ምንድን ናቸው መንስኤያቸው ምንድን ነው የሚለውን ጉዳይ ይዳሰሳል፣ ቀጥሎም ይህ አሁን የምንገኝበት ፖለቲካዊ ሁኔታ እንዴት እያደገ መጣ ወደየት ይወስደናል ያሉት አማራጮች ምንድን ናቸው የሚለው ሃሳብ ያነሳል፣ ከዚህ ቀጥሎ የትግራይ ህዝብ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ራሱን ምን ዓይነት ቦታ ላይ ያስቀምጣል የሚለውን ጥያቄ በማንሳት አስተያየቴን አስቀምጣለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ አሁን እያደገ የመጣውን ፖለቲካዊ ቀውስ የፀጥታ ሃይሎች በተለይ የሀገር መከላከያ ሰራዊት እጅን በማስገባት ሊፈታው ይችላል ወይ በሚል ጥያቄ ላይ ያለኝን አስተሳሰብ እገልፃለሁ፣ ቀጥሎም ከዚህ አሁን በግልፅ እየታየ ካለው ፖለቲካዊ ቀውስ እንዴት መውጣት ይቻላል በሚለው ጉዳይ ላይ የሚታየኝን ሃሳብ አቀርባለሁ፡፡ በመጨረሻም ማጠቃለያ ሃሳብ ይኖራል፡፡
እንግዲህ በሃሳብ አቀራረቡ በግልፅ እንደሚታየው ይህ አሁን የምንገኝበት ፖለቲካዊ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ስለሆነ በሰለጠነ መንገድ ተወያይተን ከፍተኛ ጉዳት ከመድረሱ በፊት እንፍታው፣ ችግሩን ለመፍታት ደግሞ በኢህደአዴግና ድርጅቱ በሚመራቸው የመንግስት ይሁን የፖርቲ መዋቅሮች ታጥረን በምናደርገው እንቅስቃሴ ብቻ መፍትሄ ማምጣት አይቻልም፡፡ ከዚህ በላይ ከተጠቀሰው መዋቅር በተጨማሪም ከየፖርቲና የመንግሥት መዋቅር ውጭ ያሉ ፖለቲካዊ ሃይሎችና ምልዓተ ህዝቡ በስፋትና በንቃት ሲሳተፍበት ነው በእርግጠኝነት ችግሩን መፍታት የሚቻለው ከሚል መነሻ ሃሳብ የሚነሳ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በከፍተኛ የህዝቦች መስዋዕትነትና ተሳትፎ የፀደቀውን ህገ መግስታችንን መሠረት አድርገን በህገ መንግስቱ የተቀመጡትን ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶችን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በማድረግና በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ፖለቲካዊ ሃይሎችም ያለምንም ተፅዕኖ ያልተገደበ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ አድርገው በመጨረሻም በገለልተኛ በዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ነፃ ዴሞክራዊያዊና ያለምንም ተፅዕኖ የተከናወነ ምርጫ መሆኑ ተረጋግጦ የተካሄደ ምርጫ የሚሰጠንን ውጤት ተቀብለን ለመጓዝ ቆርጠን ስንነሳ ነው በሚል አስተሳሰብ ላይ ያጠነጥናል፡፡ ይህ ፖለቲካዊ ሂደት ብዙ ስራና ጊዜ የሚጠይቅ ስለሆነ ከአሁኑ መጀመር አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡
በሀገራችን ያለው ፖለቲካዊ ያለመረጋጋት በመጠቀምና ይህንኑ ያለመረጋጋት በማባባስ፣ ከቁጥጥር ውጭ እንዲሄድ የሚፈልጉ የውጭ ሃይሎች ሌት ተቀን እየሰሩ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ለእነዚህ የውጭ ሃይሎች ለማገልገል በመወሰን የሚንቀሳቀሱ የሀገራችን ሃይሎችም አሉ፡፡ እነዚህ ሃይሎ በጋራ የሚፈጥሩትን ፓለቲካዊ ያለመረጋጋትና ከዛም ያለፈ ቀውስ መቋቋምና ማሸነፍ የምንችለው ሃገር ወዳድ የሆኑ ፖለቲካዊ ሃይሎች በሚያማማቸው ፖለቲካዊ መድረሻ ተገናኝተው በመጀመሪያ የሀገራችንን የራሳችንን ችግሮች ስናስወግድ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህንን ደግሞ ህገ-መንግስቱን መነሻ በማድረግ ሊጀመር ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ ቢሆን የሀገር ውስጥና የውጭ ሃይሎች በቅንጅት በሀገራችን ሊፈጥሩት የሚፈልጉትን ቀውስ ማሸነፍ እንችላለን፡፡ አለበለዚያ ለእነዚህ ሃይሎች ምቹ ሁኔታ ካልፈጠርንላቸው ቀውሱን ለመፍታት እየተቸገርን እንሄዳለን የሚል እምነት አለኝ፡፡
ሃገራችን ያለችበት ፖለቲካዊ ሁኔታ
ሃገራችን በአሁኑ ግዜ እጅግ ባልተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ ነው የምትገኘው የሚል እምነት አለኝ። መንግስት የሚያወጣቸው መግለጫዎችም ይህንኑ ያመላክታሉ። ሰፊ የመልካም አስተዳደር እጦት እንዳለ፣ በግልባጩም ብልሹ አስተዳደር በተለያዩ መንግስታዊ መዋቅሮች እንደተስፋፋ፣ የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ከፍተኛ እንደሆነ፣ የመንግስት ገንዘብና ንብረት ብክነት በስፋት እንደሚታይ፣ ትልቅ ተስፋ የተጣለባቸው ሃገራዊ ፕሮጀክቶች በግዝያቸው እንደማይጠናቀቁ ይህ ደግሞ አገሪቱን ለክፍተኛ ችግር እያጋለጣት እንደሆነ ይገለፃል። በተለያዩ የሃገራችን አካባቢዎች በተለያዩ ምክንያቶች (የማንነት ጥያቄ፣ የኢኮኖሚ ተተቃሚነት ጥያቄ፣ የፍትሕ መጓደልና፣ የመልካም አስተዳደር እጦት ወዘተ) በኦሮምያ፣ በደቡብ ህዝቦች፣ በአማራ፣ በትግራይ የህዝብ መነሳሳትና መንግስት ጥያቄዎቹን እንዲፈታላቸው በሰላማዊ መንገድ እየጠየቁ ይገኛሉ፡፡
በርግጥ እንደ ሃገራችን ያሉ ኋላ ቀር ሃገሮች የተደላደለ ዴሞክራስያዊ ስርዓት እንዲኖራቸው ብዙ ፈተናዎችንና መሰናክሎችን ማለፍና ቀላል ያልሆነ ግዜ መፍጀት እንደሚጠበቅባቸው ይታመናል። ምክንያቱም የሕብረተሰቡ ማህበረ ኢኮኖምያዊ የእድገት ደረጃ የሚያስቀምጠው የግድ መታለፍ ያለበት መሰናክሎች ስላሉ። ይህ የሃገራችን የዕድገት ደረጃ የሚያስቀምጥልን ተፅእኖ ተጨባጭ ተፅእኖ እንደሆነ አውቆ በዚህ ተጨባጭ ሁኔታ ውስጥ ሁነን እየሰራን እንዳለን ታውቆ ካለንበት ሁኔታ ጋር የተጣጣመ ፖሊሲና ስትርቴጂዎችን አውጥቶ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል። ለዚህ ዋና መነሻ ሕገ መንግስት ነው ብየ አምናለሁ።
ይህ ከላይ የተገለፀው ማህበረ ኢኮኖምያዊ የዕድገት ደረጃ የሚፈጥረው ተጨባጭ ተፅእኖ እንደተጠበቀ ሆኖ የሃገራችንን ሁኔታ ያገናዘቡ በማነኛውም ደረጃ በጣም ጥሩ ሊባል የሚችል ያኔ ሁኔታው የፈቀደው ህዝባዊ ተሳትፎ በተደረገበት መንገድ የፀደቀ ዴሞክራስያዊ ህገ መንግስት አለን። ይህ ሕገ መንግስት ህዝቦች ፈቅደው እንዲመሩበት ያወጡት የሃገሪቱ የመጨረሻ ህግ ነው። ሕገ መንግስቱ መሰረታዊ የሆነ የሃገራችን መንግስት አወቃቀርና አሰራር፣ የግለሰብ ይሁን የቡዱን ሰብአዊና ዴሞክራስያዊ መብቶች በሚገባ ያካትታል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው ሰብአዊና ፖለቲካዊ መብቶች ተቀባይነት አግኝተዋል። ይህ በአዲስ መንፈስ ተፈጥሮ ለነበረው የመንግስት ግንባታ (State Building) ጥሩ መነሻ ነበር።
ሕገ መንግስቱ በህዝባዊ የትጥቅ ትግሉ ውስጥ አብዮታዊና ዴሞክራስያዊ መንፈስ የተላበሰ ኢህአዴግ በሚመራው መንግስት እንዲኖር የሚፈለገውን የመንግስት አሰራርና ባህርይ መለክያ (Standard) ይሆናል ብለን ያስቀመጥነው የትጥቅ ትግሉ ድሎች መቋጫ ነበር እላለሁ። የኋ ኋላ ግን ኢህአዴግ ከሌሎች ፖለቲካዊ ሃይሎች፣ በተለይ ደግሞ ኦነግ ጋር በቅንጅት ያስቀመጠውን የመንግስትን አሰራርና ባህርይ መለክያ ይሆናል ያለውን መተግበር እያቃተው ሃገሪቱ ወዳልተፈለገ መንገድ እየገባች ነው።
ከዛ በኋላ ያለው ሁኔታም ሲታይ በርካታ አዎንታዊ ዕድገቶች ተመዝግበዋል። ሕገ መንግስቱን መሰረት በማድረግ የሃገራችን ህዝቦች ከነችግሮቻቸውም ቢሆን ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደርን ልምድ አግኝተዋል። ከዚህ አወንታዊም ይሁን አሉታዊ ልምድ ደግሞ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደርና መብታቸውን ሙሉ በሙሉ ቢጠቀሙ የሚኖረውን ጠቀሜታ ማየት ጀምረዋል። ሕገ መንግስቱ በተግባር ላይ ሲውል እንዲሁ በፁሁፍ እንደተቀመጠው አለመሆኑና አተገባበሩ ላይ ያለውን ጉድለቶችና ችግሮች አውቀዋል። በነዚህ ባለፉት ከሃያ በላይ ዓመታት ደግሞ በተሰራው ማህበረ ኢኮኖምያዊ ስራ ሕብረተሰቡ ስለመብቱ ሕገ መንግስቱ ሲፀድቅ ከነበረው በላይ የተሻለ ግንዛቤና ሕገ መንግስቱ እንዲተገበር ዕውቀትና ፍላጎት አለው። በርካታ የተማረ የሰው ሃይል ተፈጥሮአል። በሃገርቱ የተዘረጋው የመንገዶች የመገናኛ አውታሮች ሕበረተሰቡ በቀላሉ እንዲገናኝ፣ እውቀቱና የሚያገኝው መረጃ የዳበረ እንዲሆንም አስችሎታል። ከዚህ ጋርም ከውጪው ዓለም ጋር ያለን ግንኙነትም በበርካታ ገመዶች እየተተበተበ ይበልጥ እየጠነከረ መጥቷል። ይህ ማለት የግሎባላይዜሽን ተፅዕኖ ሕገ መንግስቱ ሲፀድቅ ከነበረው ሁኔታ የበለጠ ነው ማለት ነው፡፡
እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች በድምር ሲታይ የሕብረተሰቡ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ያለው አስተሳሰብና ለመሳተፍ ያለው ፍላጎትና እውቀት ጨምሯል። በአጭር አነጋገር ዴሞክራስያዊ ስርዓቱ እንዲሰፋ ይፈልጋል። ቢያንስ በሕገ መንግስቱ እውቅና የተሰጣቸው መብቶች ሳይሸራረፉ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆኑ ይፈልጋል። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ መንግስት እነዚህን በሕገ መንግስቱ እውቅና የተሰጣቸው መብቶች የሚገድቡ አሰራሮችና መመርያዎች በማውጣት ዴሞክራስያዊ ምህዳሩ እያጠበበው ይገኛል። ይህ ሁኔታ በሃገራችን ውስጥ ላለው ፖለቲካዊ ቀውስ አንድ ትልቅ ምክንያት ነው፡፡
በሕገ መንግስቱ እውቅና የተሰጣቸውን ስብአዊና ዴሞክራስያዊ መብቶች በተሟላ መንገድ አለመተግበርና፣ ይባስ ብሎም ዴሞክራስያዊ ምህዳሩ እየጠበበ ለመሄድ ሁለት እርስበርሳቸው የሚደጋገፉ ምክንያቶች አሉ ብየ አምናለሁ። አንደኛው የፖለቲካ ስርዓቱ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ወሳኝ ድርሻ ነው፡፡ እነዚህ በመደጋገፍ የስራ አስፈፃሚውን የመንግስት ክፍል የውሳኔ ሰጪነት የሃይል ሚዛን ከሌሎች ክፍሎች የበለጠ እንዲያመዝን በዚህም የተጠያቂነት አሰራር እንዲቀጭጭ፣ ቀስ በቀስ ደግሞ ህዝብ መንግስትን እንዲቆጣጠር እየተገባው የስራ አስፈፃሚው ህዝብን አስፈርቶ የፈለገውን እያደረገ የሚሄድበት ሁኔታ ተፍጥሯል። አሁን መንግስት እየገባባቸው ላሉት የተለያዩ ችግሮች ምንጫቸው ይህ የገዢው ፓርቲና የስራ አስፈፃሚው አካል ገደብ የሌለው ፖለቲካዊና ኢኮኖምያዊ ስልጣንና ሃይል ነው። እነዚህ በየተራ እንያቸው፡፡
ፖለቲካዊ ስርዓቱ
ከፖለቲካዊ ስርዓቱ ስንነሳ የፖለቲካዊ ስርዓቱ ዋነኛ ችግር በገዢው ፓርቲና በመንግስት ያለው ግንኙነት ፈፅሞ ጠፍቶ ገዢው ፓርቲና መንግስት አንድ ከመሆናቸው የሚመነጭ ነው። በተለያየ ግዜ በብዙዎች በሞያው ጠለቅ ያለ እውቀት ካላቸው ሊቃውንት እንደተገለፀውና በረጅም የሰው ልጆች ታሪክ እየተረጋገጠ የመጣው የመንግስት አወቃቀር ልምድ እንደሚታወቀው መንግስት ሶስት ትልልቅ ክፍሎች አሉት። የስራ አስፈፃሚው፣ የሕግ አውጪው እና የሕገ አተረጓጎም (አፈፃፀም) ስርዓቱ ናቸው። እነዚህ አካላት የስራ ክፍፍላቸው፣ የስልጣን ዳርቻቸው በግልፅ የታወቀ አንዱ አንደኛውን እየተቆጣጠረ ሕግ ባስቀመጠለት ገደብ ውስጥ ብቻ ሆኖ እየሰራ መሆኑ እየተያዩ የሚሰሩበት ስርዓት እንዲኖር ነው ጥረት የሚያደርገው። የዳበረ ኢኮኖሚ ባላቸውና ይህንን ኢኮኖሚ መነሻ አድርገው ዴሞክራስያዊ ስርዓታቸውን ረዘም ባለ ግዜ የገነቡ አገሮች ታሪክ እንደሚገልፀው የስልጣን ክፍፍሉ ስርዓት ከመንግስት አካላት አልፎ በሕብረተሰቡም ውስጥ ይታያል። የፖለቲካ ሃይሉና የኢኮኖሚ ሃይሉ ተነፃፃሪ ነፃነት ኖሯቸው በዚህ ስልጣን መሰረት የመንግስቱ አወቃቀርም የተስተካከለበት አካሄድ እናስተውላለን።
ከነዚህ ከላይ የተገለፁት የመንግስት አካላት የሕግ አውጪው ክፍል (ፓርላማ) በቀጥታ ከህዝብ የተመረጠ ስለሆነ የተለያዩ የሕብረተሰቡ አስተሳሰቦችንና ጥቅሞችን የሚወክል እንዲሆን ነው የሚጠበቀው። ይህ የሕግ አውጪው የመንግስት ክፍል ዋናው ስራው ህግ ማውጣትና የስራ አስፈፃሚውን የመንግስት አካል መቆጣጠር ነው። የስራ አስፈፃሚው በመንግስት ስልጣን እና ሃብት የማዘዝ እና ስራዎችን እለት ተእለት የማስፈፀም ስልጣን ስላለው ይህንን ስልጣኑን ያለአግባብ የመጠቀም እድሉ የሰፋ ነው። የሕግ አውጪው አካል ህዝብ በውክልና የሰጠውን ስልጣን በመጠቀም የስራ አስፈፃሚው በሕግ ከተሰጠው ስልጣን ውጪ በመውጣት የህዝቦችን ሰብአዊና ፖለቲካዊ መብቶችን እንዳይጥስና የሃገርን ጥቅም እንዳይጎዳ ይቆጣጠራል፡፡ አስፈላጊ ሲሆንም ይህንን የሚገድብ ህግ ያወጣል፡፡
ይህንን ስራ በታሰበው መንገድ ለመስራት እንዲያስችለው ደግሞ ለሕግ አውጪው ተጠሪ የሆኑ የተለያዩ አካላትን ያቋቁማል፤ ከነዚህም ውስጥ የሰብአዊ መብት ኮሚሺን፣ የኦዲት ኮሚሽን፣ የምርጫ ቦርድ ኮሚሽን፣ የፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ሌሎች በሀገሪቱ ፖለቲካዊ አወቃቀር ከማንኛውም ፖርቲ ጋር መዋቅራዊ የሆነ ግንኙነት እንዲኖራቸው የማይፈልጉ አካላትም የዚህ የመንግስት አካል ተጠሪዎች ይሆናሉ፡፡ እዚህ ውስጥ ለምሳሌ የፕሬዝዳንቱ መስሪያ ቤት፣ ሰራዊቱ፣ ቢሮክራሲውም በዚህ ይጠቃልላል፡፡ እነዚህ በድምር በእንግሊዝኛው አጠራር ስቴት (state) ተብሎ የሚታወቀውን ስያሜ ይይዛሉ። እዚህ ታሳቢ የሚሆነው ነገር ምንም እንኳን ከፍተኛውን ድምፅ በማግኘት የስራ አስፈፃሚውን የመንግስት ክፍል በአንድ የምርጫ ዘመን የሚቆጣጠረው አንድ ፓርቲ ቢሆንም በሕግ አውጪው (ማለት በፓርላማው) ውስጥ ግን የብዙ ፓርቲዎች አስተሳሰቦች ውክልና ስለሚኖር የሕብረተሰቡን ፍላጎቶችና አስተሳሰቦች በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ይንፀባርቃል። በሕግ አውጪው የሚቋቋሙት ኮሚሽኖችም ይህንን ስብጥር ያንፀባርቃሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው፤ ስለዚህ ስቴት በሚባለው ስያሜ ውስጥ ያሉት አካላት ብዙ ግዜ የሃገሪቱን ዘለቄታዊ ጥቅም ያስጠብቃሉ የሚላቸውን ፖሊሲዎችንና ስታራቴጂዎችን በማውጣት የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳው ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል እንዲሆን በማስቻል በሰላማዊና ዴሞክራስያዊ መንገድ ሕገ መንግስቱን ጠብቀው ሲያሸንፉ ስልጣን እንድይዙ፣ ሲሸነፉ ደግሞ ስልጣኑን እንዲለቁ የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት ዋነኛው ተግባሩ ይሆናል። የተረጋጋ ሰላማዊ ዴሞክራዊያዊ ስርዓት በቅጡ እንዲሰራ ማስቻል ዋነኛው ተግባሩ ስለሆነ አንድ በአንድ ወቅት አሸንፎ ስልጣን የያዘ ፓርቲ ለዘላለም በስልጣን ላይ እንዲኖር ዋነኛ ስራውን አያደርግም፡፡
ከዚህ ቀጥሎ የሃገሪቱን ሕግ ተከትሎ ባንድ ወቅት በምርጫ ተወዳድሮ ያሸነፈ አንድ ፓርቲ የስራ አስፈፃሚውን ዋነኛ የስልጣን ቦታውዎች ይቆጣጠራል። ይህ ሁኔታ ከሃገር ሃገር እንደ ሕገ መንግስቱና እንደ ምርጫው ውጤት ሊለያይ ይችላል። አንድ የፖለቲካ ፖርቲ ብቻውን ስልጣን የማይቆጣጠርበት ሁኔታ ከተፈጠረ ፖርቲዎች በቅንጅት ስልጣን የሚጋሩበት ሁኔታ ሲመጣ የሥራ አስፈፃሚው የስልጣን ክፍፍሉም በዚሁ መሠረት ይስተካከላል፡፡ በሃገራችን አሁን ባለው ሁኔታ በምርጫ ያሸነፈ ሃይል የስራ አስፈፃሚውን የመንግስት ክፍል ይቆጣጠራል። ይህ ፓርቲ በምርጫ ወቅት እሰራዋለሁ ያለውን ስራ ለህዝብ አቅርቦ በህዝብ ተመርጦ ለአምስት ዓመት እንዲያስተዳድር እድል የተሰጠው ፓርቲ ነው፡፡ የገባውን ቃል ለማስፈፀም እንዲመቸው የስራ አስፈፃሚውን የመንግስት ክፍል ይቆጣጠራል። ከዚህ አልፎ ግን የሕግ አውጪውንና የሕገ መተርጎም (Judicial System) ስርዓቱንም የሚቆጣጠር ወይም በሥራ አስፈፃሚው ጫና ውስጥ እንዲሰሩ የሚያስገድድ ከሆነ ስርዓቱ ይፋለሳል። ይህ ለተወሰነ ግዜ አገር እንዲያስተዳድር በምርጫ ስልጣን የተሰጠው የግዜው መስተዳድር ረዘም ላለ ግዜ እሱን እንዲቆጠጠሩ የተቋቋሙትን የሕግ አውጪውንና እሱ የሚመራቸው የተለያዩ ኮሚሽኖች፣ የሚቆጣጠር ከሆነ ስልጣኑ ገደብ የለሽ ይሆናል።
ከሕግ አውጪው በተለየ መንገድ ደግሞ የሕግ አተረጓጎሙ ስርዓት አለ፡፡ ይህ የስራ አስፈፃሚው አካል ከሕግና ከተፈቀደለት የስልጣን ገደብ አልፎ ስህተት የፈፀመ እንደሆነ ህጉን ለመተርጎምና በዚህ መሠረትም ጥፋተኛውን ለመቅጣትና ለማረም ተብሎ የተቋቋመ የመንግስት ክፍል ነው። በርግጥ የመንግስትን ባለስልጣናት ብቻ አይደለም የሚቀጣው፤ አሁን በምናነሳው ጉዳይ ግን ዋናው ትኩረታችን የመንግስት ባለስልጣናት ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአንድ ሀገር ህግን በመጣስ በህዝቦች፣ በዜጎች ላይ ከፍተኛ ወንጀል መፈፀም የሚችሉት በሀገር ሃብትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጥፋት የሚያስከትል ስህተት ወይም ወንጀል የሚፈፅሙት የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም በሃገር ከፍተኛ ጥፋት የሚያመጣ ጥፋትን፤ የዳኝነት ስርዓቱ ከስራ አስፈፃሚው ነፃ ሆኖ የስራ አስፈፃሚውን ባለስልጣናት ስልጣናቸውን ተጠቅመው የዜጎችን ሰብአዊና ፖለቲካዊ መብቶችን ሲጥሱ የህዝቦችን መብት ሲጋፉ ያገር ሃብት ሲዘርፉ ወይም ሲያባክኑ ተጠያቂ ያደርጋቸዋል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ከስራ አስፈፃሚው ተፅዕኖ ነፃ መሆን አለበት።
አሁን በሃገራችን ያለው የፖለቲካ ስርዓትና አስተዳደር ከዚህ የተለየ ነው። የሕግ አውጪውን አንድ ፓርቲ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮታል፤ ይህ ፓርቲ ደግሞ በዴሞክራስያዊ ማዕከላዊነት መርህ የሚመራ ነው። ይህ ማለት የፓርቲው አባላት በማነኛውም የመንግስት መዋቅር ውስጥ ካሉ የፓርቲውን ፖለቲካዊ አቋም ማራመድ፣ መፈፀም እና ማስፈፀም አለባቸው። (በግላቸው የማያምኑበት፣ የማይቀበሉት ነገር ቢሆንም) ከዚህ ስንነሳ መቶ በመቶ የሕግ አውጪውን የተቆጣጠረ ፓርቲ ለሕግ አውጪው ተጠሪ የሆኑቱን የተለያዩ ኮሚሽኖችንም ይቆጣጠራል። የተለያዩ የፖለቲካ አስተሳሰብና ጥቅሞች የሚንፀባረቁበትን የሚንሽራሸሩበትን ፓርላማ የአንድ ፓርቲ ድምፅ ብቻ የሚያስተጋባበት መድረክ ይሆናል። በአንድ ወቅት የተመረጠን የፖለቲካ ፓርቲ ያቋቋመውን የተወሰነ ግዜ መስተዳድር በሕጉ መሰረት እየሰራ መሆኑን መቆጣጠር ቀርቶ ዋናው የስቴት አሰራርና መዋቅር ለስራ አስፈፃሚው እንደሚመች ያደርግለታል ማለት ነው። በፖለቲካዊ ፓርቲ፣ በስቴትና በወቅቱ መስተዳድር ያለው የስልጣን ክፍፍል፣ ቁጥጥር በሙሉ ይጠፉና ስራ አስፈፃሚው በፈለገው መንገድ ሁኔታዎች ይመቻቹለታል ማለት ነው። በሃገራችን ያለው ሁኔታ ይህ ነው፡፡
ይህ ከላይ የተገለፀው ሁኔታ ኢህአዴግ ስራዬና፣ ፕሮግራሜ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ስላገኘ ያመጣሁት ውጤት ነው ይለናል። እዚህ ማለት የምፈልገው ኢህአዴግ ለሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲመረጡ ቀስቅስ የሚለው የለም። ግን በሕገ መንግስቱ የተቀመጡትን ሰብአዊና ፖለቲካዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ ተግባር ላይ የሚውሉበትን ሁኔታ እንዲፈጠር ከሌሎች ፖለቲካዊ ሃይሎች ጋር ሆኖ ይስራ፡፡ ይህንን የሚገድቡ የተለያዩ መመሪያዎችና አሰራሮችን ያስወግድ የመጫወቻ ሜዳውን ለሁሉም ለራሱም ጭምር እኩል እንዲሆን ያድርግ፡፡ ሌሎቹን የፖለቲካ ፓርቲዎች በመመሪያዎችና ህጎች አይገድባቸው፡፡ ህዝብ ላይ የተጫነውን በፀጥታ ሃይሎች አስፈራርቶ የማስተዳደር አካሄድ ይነሳና በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ የሚፈጠረው ችግር ይወገድ፡፡ እንደ ማነኛውም ፓርቲ ኢህአዴግም የፖለቲካ ቅስቀሳውን ያካሂድ፣ በኋላም የምርጫውን ውጤት በፀጋ ይቀበልና ውጤቱን እንየው፡፡
አሁን በሃገራችን ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰላማዊ መንገድ በምርጫ ስልጣን ከአንድ ፓርቲ ወደ ሌላ የሚሸጋገርበት ሁኔታ እጅግ በጣም ጠባብ የሆነበት በመሆኑም በከፍተኛ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ የገባንበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
በዚህ አጭር ፁሁፍ በመንግስት (state) በግዜው መስተዳድር (regime)እና በምርጫ አሸንፎ ለተወሰነ ግዜ ስልጣን የያዘ ፓርቲ (incumbent party) ምንነታቸውና በመሃከላቸው ያለውን ዝምድና በሰፊው ለመግለፅ አይመችም፤ ሆኖም በእነዚህ አካላት ያለው ግልፅ የስልጣን ክፍፍል፣ የስራ ዝምድና ካልታወቀና ሙሉ በሙሉ ተግባር ላይ ካልዋለ አሁን አገራችን ውስጥ የሚታየውን በሕገ መንግስት እውቅና ያገኙ ሰብአዊና ዴሞክራስያዊ መብቶች ሲጣሱ የሚያስቆምና የሚቆጣጠር አካል ይጠፋል። ለተወሰነ ግዜ ስልጣን የያዘው ፓርቲ በስራው ጥራት ተቀባይነት እያገኘ ዳግመኛ እየተመረጠ የሚሄድበት ሁኔታ ጠፍቶ ፓርቲው ባወጣቸው አዋጆችና መመርያዎች ፖለቲካዊ ምህዳሩን በማጥበብ ዕድሜውን የሚያራዝምበት ሁኔታ ይፈጠራል። የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በስልጣን መባለግ፣ ሙስና በግልፅ መንግስት በሚያምንበት ደረጃ ቢታወቅም ፓርቲው (የስልጣን ግዜውን ለማራዘም ውስጠ ፓርቲ ቀውስ ተፈጥሮ እንዳይዳከም) በቁርጠኝነት አይዋጋቸውም። በአጠቃላይ አንድ ዴሞክራስያዊ ስርዓት እየዳበረ መሄዱ የግድ ተፈላጊ የሆነው የቁጥጥርና የተጠያቂነት ስርዓት በተለያዩ የሕብረተሰብ ውክልና ያላቸው ፖለቲካዊ ተቋማት የማይደረግ ስለሆነ የአንድ ፓርቲ ስራ ተደርጎ ሰለሚወሰድ ለማረምም ለማስተካከልም አስቸጋሪ ሆኗል።
ይህ ሁኔታ አሁን በስልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ ብቻ የሚመለከት አይደለም፤ ሌላ ፓርቲ ስልጣን ቢይዝም መሰረታዊ አወቃቀሩ አሁን ካለበት ካልተለወጠ ይብስ እንደሆነንጂ አይሻሻልም። የአንድን ሃገር ፖለቲካዊ ስርዓት ማስተካከልና ዜጎችዋን የሚጠቅም፣ ዜጎቹ በየግዜው እየወደዱትና እየተደሰቱበት እንዲሄድ የማድረግ የረዥም ግዜ ስራ ቅን ሐሳብ ላለው አንድ ሰው ወይም እሚበጅህን እማውቅ እኔ ብቻ ነኝ ለሚል አንድ ፓርቲ የሚተው ጉዳይ አይደለም። ዜጎች በትግላቸው በየግዜው እያስተካከሉት፣ እንዲመቻቸው እያደረጉት የሚሰራ ጉዳይ ነው። በሃገርችንም ከዚህ የተለየ ሊሆን አይገባም፤ አይችልምም።
ኢኮኖሚያዊ ሁኔታው
ሁለተኛው የኢኮኖሚ ስርዓታችን ጉዳይ ነው፡፡ አሁን ያለው የሀገራችን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴና ታሪካዊ አስተዳደጉ የዜጎች በመንግስት ላይ ተፅዕኖ የመፍጠር አቅም የሌለው መንግስት በአጠቃላይ የስራ አስፈፃሚው ክፍል ደግሞ በተለይ የፈለገውንና ያመነበትን ለማድረግ የሚከለክለው የሌለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ምንም እንኳን በቅርብ ግዜ የመንግስት ግብር የመሰብሰብ አቅም እየተጠናከረ የመጣ ቢሆንም፤ የሃገራችን ኢኮኖሚያዊ ልማት ዝቅተኛ በመሆኑ ከሃገር ውስጥ የሚሰበሰበው ገቢም መጠኑ አነስተኛ በመሆኑ መንግስት በሃገሪቱ ስራ ለመስራት የሚያስፈልገውን ትልቁን ገንዘብ ከውጭ ሃገር (በእርዳታ ወይም በብድር አሁን ደግሞ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መልክ) ነው እሚያገኘው። ከዚህ በተጨማሪም መንግስት ራሱ ከሚቆጣጠራቸው የልማት ድርጅቶችና ከሀገር ውስጥ ገቢ በሚያገኘው ነው እሚንቀሳቀሰው። ይህ ማለት መንግስት ሰፊ የሆነ ኢኮኖምያዊ ነፃነት አለው ማለት ነው። ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ በተወካዮቹ በኩል (በፓርላማ) አድርጎ ፖሊሲዎቸን በስራ አስፈፃሚው የመጫን ጡንቻው በጣም ደካማ ነው፡፡ የፖለቲካ ስልጣን የያዘ ሃይል በሃገሪቱ ኢክኮኖምያዊ ሂወትም ላይ ከፍተኛ ስልጣን አለው። በሃገራችን ዋና አሰሪ መንግስት ነው፤ የተለያዩ ኮንትራክቶችን የሚሰጠው፣ ትላልቅ ፕሮጅክቶችን የሚያከናውነው የስራ አስፈፃሚው ነው። የስራ አስፈፃሚው ከፈለገ ሃብታም ያደርግሃል አለበለዝያ ደግሞ በድህነት እንድትኖር ይፈርድብሃል። መንግስት በዜጎች ኢኮኖምያዊ ሂወት ላይ እጅግ በጣም ከፍተኛ ተፅእኖ አለው። ይህ በየደረጃው ያለው የስራ አስፈፃሚው አካል ተግባር ላይ የሚያውለው ስልጣን በዜጎች ሂወት በፖለቲካዊ አቋማቸውም ጭምር ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው፡፡ በአድርባይነት ወደ ስልጣን የሚወጣው አካል በቢልየኖች ላይ የሚወሰን ስለሚሆን የዜጎችን ሰርቶ የመጠቀም ጉዳይ በሱ ፍላጎት ስር ይወድቅና በላብና በጥረት ሳይሆን ሎሌነት የመጠቀምያ መሳሪያ ይሆናል።
ኑሮን አሸንፎ ለመቀጠል የፖለቲካ ጠባይን “አሳምሮ” የመንግስትና የፓርቲ ባለስልጣናት የሚፈልጉትን ፖለቲካዊ ጠባይ መያዝ በሌላ አነጋገር አድርባይ መሆንን ይጠይቃል። ለዚህ ሁሉ ተብሎ የፓርቲ አባል መሆንና ከፍተኛ ደጋፊ መስሎ መታየትም “አዋጪ” መንገድ ይሆናል። በፖለቲካዊም በኢኮኖምያዊም እንቅስቃሴ እንደፈለገ ማድረግ የሚችል አረ ተው ባይ የሌለው ፓርቲና መንግስት በሃገራችን ነግሷል። በእንዲህ ዓይነት ፖለቲካዊና ኢኮኖምያዊ ሁኔታ በመንግስት ባለስልጣናትና ከነሱ ጋር የተጠጉ ተጠቃሚዎች ሙስና፣ በአቋራጭ ለመበልፀግ መሯሯጥ (ኪራይ ሰብሳቢነት የሚባለው) ብልሹ አስተዳደር መንገስ ባህርያዊ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በሌላው የሕብረተሰብ ክፍል ፍርሃት፣ አድርባይነት ቢያስከትል አይገርምም።
አሁን በዓለማችን በአጠቃላይ በሀገራችን ደግሞ በተለይ ሀገራት ሊከተሉት ስለሚገባ የኢኮኖሚ ፖሊሲና አቅጣጫዎች (Developmental state VS Neo-Liberal political economy) አስተሳሰብ ላይ ስነ ሃሳባዊ ክርክር በዚህ ፅሁፍ ለማድረግ አይመችም፡፡ ግን የNeo-Libral political economy አስተሳሰብ ለሀገራችን ይጠቅማል የሚል አስተሳሰብ እንደሌለኝ መግለፅ እፈልጋለሁ፡፡ መንግስት የሀገር ሉዓላዊነትና ደህንነት በመጠበቅ ፖሊሲዎችን በማውጣትና ግብር በመሰብሰብ ብቻ ታጥሮ ይቀመጥ፣ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው ለገበያ ብቻ ይተው የሚል አመለካከት የለኝም፡፡ እንደ ሃገራችን በመሰሉ በጣም ኋላቀርና ከፍተኛ ድህነት ባለበት ሃገር ብቻ ሳይሆን በጣም በበለፅጉት ሃገራትም መንግስት በሃገር ኢኮኖሚ ማሳደግ ላይ ከፍተኛ ድርሻ አለው። በማደግ ላይ ባሉት ሃገራት ደግሞ ድርሻው ይጨምራል፤ ግን የመንግስት በሃገር ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ ያለው ድርሻ ለመወጣት ሲንቀሳቀስ በምን ዋጋ ነው የሚሰራው ነው ትልቁ ጥያቄ። የሚጠቅምህን እኔ አውቅልሃለሁ ስለዚህ የምሰራውን ዝም ብለህ ተቀበል ብለን ህዝብን አግልለን ነው የምንሰራው ወይስ በሰፊ የህዝብ ተሳትፎ አሳምነን ጥቅሙን አውቆ እየደገፈው መከፈል ያለበት መስዋእትነት ካለ ተቀብሎ እየከፈለ በሌላ አነጋገር ከሰፊ ዴሞክራስያዊ ተሳትፎ ጋር ነው የምናካሂደው፡፡ የህዝብን ሰፊ ዴሞክራስያዊ ተሳትፎ ገድለን ግን የስራ አስፈፃሚውን ጡንቻና ኪስ አሳብጠን በሌላ አገላለፅ ለሙስናና ለብልሹ አስተዳደር ምቹ ሁኔታ ፈጥረን ከዚህ የተነሳ ደግሞ በሃገራችን ከፍተኛ ፖለቲካዊ ችግር ፈጥረን ነው ወይ የምንተገብረው? ነው ምርጫው።
አሁን እየሄድንበት ያለነው የመንግስት በሃገር ኢኮኖምያዊ ግንባታ ላይ ያለው ሚና በጣም ከፍተኛ ዋጋ እሚያስከፍለን ይሆናል ብየ አምናለሁ። ይህንን የመንግስት በኢኮኖምያዊ ግንባታ ላይ ያለው ሚና በሰፊ ዴሞክራስያዊ ተሳትፎ ህዝብ እየተቀበለው እያመነበት በወከላቸው የህዝብ ተመራጮች በኩል ደግሞ እየተቆጣጠረው እና እየወሰነበት የሚካሄድ መሆን ይኖርበታል። አሁን ኢህአዴግ በተቆጣጠረው ፓርላማ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የሚደረገው እንቅስቃሴ ተፈላጊውን ውጤት እንዳላመጣ ግልፅ ነው። የስራ አስፈፃሚው አካል የፈለገውን ነገር ከማድረግ የሚያግደው ተቆጣጣሪ አካል የለም።
ይህ በህዝብ ተቆጣጣሪነት የሚካሄድ የመንግስት በኢኮኖምያዊ ህይወት ያለው ሚና ተግባር ላይ ሲውል ግዜ የሚፈጅ ብዙ ውጣውረድና ህዝብን የማሳመን ስራ እንደሚፈልግ አንዳንዴም የስራ አስፈፃሚው ከፈለገው ውጪ ውሳኔዎች ሊወሰኑ እንደሚችሉ ግልፅ ነው። ይህ ሃገር ከተረጋጋና ከተወሰነ ግዜ በኋላ ወደ ኋላ እንዳይመለስ በቀጣይነት ግለቱን እየጨመረ የሚያድግ ኢኮኖሚና ዴሞክራስያዊ ስርዓት መገንባት ከፈለግን መከፈል ያለበት ዋጋ ነው።
በማጠቃለል፣ አሁን አገራችን ያለችበት ሁኔታ የህዝብ አመኔታ በመንግስት ላይ በጣም ዝቅተኛ የሆነበት፣ በህዝቦች መሃከል ያለው መቀራረብ እና መዋደድ የቀነሰበት፣ ጥላቻ እየበረታና በግልፅ እየተነገረ፣ የህዝቦች የእርስ በርስ መናቆር እንዳይመጣ የሚፈራበት ስለሆነም ውስጣዊ አንድነታችን በጣም የላላበት፣ የመንግስት መዋቅር የመፈፀም አቅሙ ደካማ የሆነበት፤ ከዚህ የተነሳም ህዝቡ ተስፋ የቆረጠበት፣ በያካባቢው ፖለቲካዊ ችግሮች ሲነሱ በታጠቀ ሃይል (ፖሊስና መከላከያ) የሚፈታበት፣ ህዝቡ አሁን የሚታየው ችግር ይፈታል፣ አይፈታም፣ እንዴት ይፈታል እያለ ከፍተኛ ጥርጣሬ ውስጥ የገባበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው።
አሁን ወዳለንበት ሁኔታ እንዴት ገባን?
ሀገራችን አሁን ከምትገኝበት ፖለቲካዊ ሁኔታ እንዴት ገባን ብሎ ዕድገቱን ወደኋላ መለስ ብሎ ማየት ተገቢ ይመስለኛል። ከዚህ ተምረን ችግሩን ለመፍታት እንድንችል፡፡ ኢህአዴግ በመራው የትጥቅ ትግል እና ከዚያም በኋላ በነበሩት ጥቂት አመታት ፀረ ዴሞክራስያዊ የሆኑ አስተሳሰቦችንና ተግባሮች አልነበሩም ባልልም መሰረታዊ ባህሪው ግን ህዝባዊና ዴሞክራስያዊ ነበር የሚል እምነት አለኝ። የዚህ ዴሞክራስያዊ ባህሪ መቋጫ በህዝብ ተሳትፎ የፀደቀው ሕገ መንግስት ነው እላለሁ።
አንድ ለህዝቦች ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ከፍተኛ መስዋዕትነት በሚጠይቅና በመሠረቱ አብዮታዊ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የታገለ የፖለቲካ ድርጅት እንዴት ፀረ ዲሞክራዊያዊ ይሆናል የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ በእኔ እምነት በውስጡ ፀረ ዴሞክራዊያዊ የሆኑ ባህርያትም የነበሩበት ግን በመሠረቱ ዴሞክራሲዊያ የነበረ የፖለቲካ ድርጅት በሂደት በየጊዜው በሚወስዳቸው ፖለቲካዊ ውሳኔዎችና እንቅስቃሴዎች እየተለወጠ ፀረ-ዴሞክራሲ እየሆነ ይመጣል ብዬ አምናለሁ፡፡ በተለያየ ጊዜ የፖለቲካ ድርጅቱን የሚፈታተኑ ትላልቅ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በሚወስዳቸው አቋሞች ቀስ በቀስ የነበረበትን ቦታ እየለቀቀ ይሄዳል፡፡ ኢህአዴግም ውስጥ የሆነው ጉዳይ ይህ ነው እላለሁ፡፡ እንደኛ ሀገር በመሰሉ በጣም ዝቅተኛ በሆነ ማህበር ኢኮኖሚያዊ የዕድገት ደረጃ ላይ ባሉ ሀገሮች የዴሞክራዊያዊ ስርዓት ግንባታው ቅን አስተሳሰብና በጎ ፍላጎት ባላቸው ግለሰቦች ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ አይሳካም፡፡ በህብረተሰቡ ያሉ የተለያዩ አስተሳሰብ፣ ፍላጎት ያላቸው በህብረተሰቡም የራሳቸው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረት ባላቸው ሃይሎች አስተሳሰባቸውንና ፍላጎቶቻቸውን በተደራጀ መንገድ በግልፅ አቅርበው በሚያደርጉት ሰላማዊ ትግልና የዚህ ትግል ውጤት ሆኖ ነው የሚያድገው፡፡ ታሪክ የሚነግረን ይህንኑ ነው፡፡
በአንድ ሀገር ዴሞክራዊያዊ ስርዓት ስር እየሰደደ በቀጣይነት እያደገ እየተገነባ እንዲሄድ የሚፈልጉ መሪዎች፤ ፖርቲዎች፤ ይህንን ሁኔታ አውቀው ሊገነባ ለሚፈልገው የተደላደለ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠርና ማመቻቸት ሲችሉ ነው፡፡ ግለሰቦች ወይም ፖርቲዎች ትክክለኛ የመሰላቸውን የእነሱን አስተሳሰብና ፍላጎት ብቻ ህብረተሰቡ ላይ በመጫን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት አይችሉም፡፡ ከዚህ አንፃር ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ ህብረተሰቡ ላይ መሠረት ያላቸው በተገቢው መንገድ ከተመሩና ዕድል ከተሰጣቸው ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ በተደላደለ መሠረት ለማስጀመር ይጠቅሙ የነበሩ ፖለቲካዊ ክስተቶች ተፈጥረው በተገቢው መንገድ ሳንጠቀምባቸው ቀርተን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታውን በመጉዳት ተፈተዋል፡፡ በዚህ ሂደትም ኢህአዴግ የመንግስትን ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ ቀሰ በቀስ ፀረ ዴሞክራስያዊ ባህርያቱ እያደጉ መጡ እላለሁ። ለዚህ አስተዋፅኦ የዳረጉ ብዙ ነገሮች ይኖራሉ፤ እነሱን ሁሉን መዘርዘር አስፈላጊ አይመስለኝም። ግን የመንግስት ስልጣን ከተያዘ በኋላ የኢህአዴግን ዴሞክራስያዊነት እሚፈታተኑ ሶስት ትልልቅ ክንዋኔዎች ተፈፅመዋል። እነዚህም ክንዋኔዎች የተፈቱበት መንገድ የኢህአዴግን ፀረ ዴሞክራስያዊነት ያጎሉ ከዛም በላይ ተቋማዊ (Institutionalize) እንዲሆን ያስቻሉ ናቸው ብዬ አምናለሁ። እነሱም:
አንደኛ፥ ከኦነግ ጋር የነበረን ቅራኔ አፈታት
ሁለተኛ፥ በህወሃት ውስጥ የተፈጠረውን የውስጠ ፓርቲ ቀውስ አፈታት
ሶስተኛ፥ የ1997 ዓ.ም ምርጫ ተከትሎ በተፈጠረው ቀውስ የተፈታበት አግባብ ናቸው። እነዚህን አንድ በአንድ እንያቸው፡፡
የደርግ መንግስት ከወደቀ በኋላ የሽግግር መንግስቱ ቻርተር በመሰረቱ በኢህአዴግና በኦነግ (የኦሮሞ ነፃነት ግንባር) መካከል በተደረሰበት ስምምነት ፀደቀ፤ ጊዝያዊ የሽግ ግር መንግስትም በዚህው ስምምነት መሰረት ተመሰረተ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በኢህአዴግና በኦነግ በተፈጠረው አለመግባባት ኦነግ ከመንግስት ወጣ፣ ውግያዎቹም ተካሄዱ። በዚህ ሂደት ጥፋቱ የማን ነበር የሚለውን ጥያቄ ለታሪክ እንተወውና ይህ ክስተት ግን በኢትዮጵያ ሊመሰረት ይችል የነበረውን የሃይል ሚዛን መሰረት ያደረገ ውስጣዊ የቁጥጥርና የተጠያቂነትን አሰራር ለመመስረት የሚያስችል የነበረ እድል እንድናጣ በማድረግ የዴሞክራስያዊ ስርዓት ግንባታውን ሂደት በከፍተኛ ደረጃ ጎድቷል የሚል እምነት አለኝ። ኦነግ የራሱ ችግሮችና ስህተቶች የነበሩት ቢሆንም በወቅቱ ግን የኦሮሞ ህዝብ ፍላጎትና ስሜት የሚያንፀባርቅ የፖለቲካ ሃይል ነበር።
ከዚህ በላይ ደግሞ ከኢህአዴግና ይህ ድርጅት ከሚመራበት አስተሳሰብ፣ የፖለቲካ እምነትና ባህል ወጣ ያለ በራሱ መንገድ የተፈጠረ ስለነበረም ኢህአዴግ ውስጥ የነበረውን ስብስብ የመገዳደር (Challenge የማድረግ) አቅምም ፍላጎትም የነበረው ድርጅት ነበር። ይሁን እኒጂ ኦነግ ደግሞ ብቻውን ኢትዮጵያን እንደፈለገ ማድረግ የሚችል የፖለቲካ ሃይል አልነበረም። ይህ ሁኔታ በሚገባ ቢያዝ ኖሮ ጤናማ የሆነ የቁጥጥርና የተጠያቂነት ስርዓት ለመገንባት፤ የስራ አስፈፃሚ የሆነው የመንግስት አካልን የሃላፊነትና የተጠያቂነትን አሰራርን የምንቆጣጠርበት የፖለቲካ ስርዓት የመመስረት ዕድሉ የሰፋ ነበር የሚል እምነት አለኝ። ይህ አካሄድ ችግሮች አይኖርበትም ነበር ለማለት ሳይሆን የተፈጠረው ሁኔታ የተፈታበት መንገድ ግን ሕገ መንግስታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ማጥበብ ላይ ቀላል ያልሆነ ድርሻ ነበረው እላለሁ።
ከህገ መንግስቱ መፅደቅና በምርጫ የቆመ መንግስት ከተመሠረተ በኋላ በኢህአዴግ ውስጥ በፓርቲና በመንግስት ምን ዓይነት ግንኙነት መኖር ይገባዋል የሚል ሃሳብ እየተብላላ እያለ ኤርትራ ወረረችን። ይህ ወረራ በኢህአዴግ ውስጥ በተለይ በህወሃት መታየት ጀምሮ የነበረውን የሃሳብ ልዩነት አጉልቶ አወጣው፡፡ ከኤርትራው ጦርነት በኋላ በ1993 ዓ.ም በህወሃት ውስጥ የተፈጠረው መከፋፈልና ይህ መከፋፈል የተፈታበት መንገድ ሌላ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ ከፍተኛ ጥቑር ጠባሳ ያስቀመጠ ፖለቲካዊ ክስተት ነበር። የክፍፍሉ አጀንዳዎች ምንምን ነበሩ፣ የትኛው ወገን ትክክለኛ፣ የትኛውስ ስህተት ነበር የሚለው አሁንም ለታሪክ እተወዋለሁ። አጀንዳው ምን ይሁን ምን መከፋፈሉን ለመፍታት የተወሰደው እርምጃ የድርጅቱን ሕገ ደምብ የጣሰ፣ ድርጅት ፈረሰ በሚል ማስፈራርያ የውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ህይወትና አሰራርን በመጣስ ገደል ውስጥ የከተተ ክስተት ነበር። ጉዳዩ በህወሃት ውስጥ የነበሩ በፖለቲካው ከፍተኛ ሚዛን የነበራቸው ሰዎች ለምን ወጡ አይደለም። አወጣጣቸው የውስጠ-ፓርቲ ዴሞክራሲ ያልተከተለ፣ የተወሰነ ሃይል ሌላውን ክፍል ከውስጠ ፓርቲ አሰራር ውጪ የፀጥታ ሃይሎች ተጠቅሞ ያባረረበት አሰራር ነበር። ይህንን ተከትሎም ከፓርቲ ከወጡ ሰዎች ውስጥ በጣም በሚገርም ፍጥነት የሃገር ፓርላማ ተስብስቦ ችግር ሊፈጥሩ ይችላሉ ተብለው የተጠረጠሩትን ሰዎች ወህኒ ቤት ለማሰርና እዛም ለማቆየት የሚያስችል ሕግ በአንድ ቀን ወጣ፤ በፍርድ ቤት በዋስ የተለቀቀው ስየ አፍታ ሳይቆይ ወደ እስር ቤት ተወረወረ።
ይህ ዕድሜያቸውን ሙሉ በትግል ያሳለፉ፣ በድርጅቱና በመንግስት የሃላፊነት ቦታ የነበሩ ትላልቅ ሰዎች ግማሹ ወደ ውህኒ ግማሽ ወደ መንገድ ተወረወረ።አንድ የፖለቲካ ድርጅት በውስጡ ራሱ ያስቀመጠውን የውስጠ ፓርቲ ዴሞክራስያዊ አሰራር በምንም ምክንያት ይሁን ራሱ ካፈረሰ ከዛ በኋላ ማቆምያ የለውም። እነዚህ ከላይ የተገለፁት ሰዎች የውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ በሚፈቅደው መሰረት መብታቸውን ያላስጠበቀና፣ ቢሳሳቱም ይህንን ችሎ በዴሞክራስያዊ መንገድ የማይፈታ ድርጅት ለተቀረው የሕብረተሰብ ክፍል ዴሞክራስያዊ መብት ያስጠብቃል ብሎ ማሰብ ለኔ ዘበት ነው የሆነብኝ።
በዚህ ክስተትም በተቀረው የፓርቲው አባልና ሰፊው ሕብረተሰብ ላይ ፍርሃትን ነው የለቀቀው። እነዚህ ሰዎችን ፀረ ዴሞክራስያዊ በሆነ መንገድ የቀጣ ድርጅት ለሌላው ታችኛው ካድሬና የመንግስት ባለስልጣን ምንም ደንታ ሊኖረው እንደማይችል በጣም ግልፅ የሆነ መልእክት ተላለፈ። ሰውን አስፈራርቶ መግዛት እንደ የመንግስት ፖሊሲ ግልፅ ሆኖ ወጣ። ከማሕበራዊ ኑሮ ጋር ተያይዞ ከቦታቸው የተነሱት የህወሃትና የመንግስት ባለስልጣናት መጠየቅ ራሱ ከፍተኛ ቅጣት የሚያስከትል ጥፋት ሆነ። አረ ይሄ ነገር አፈታቱ ትክክል አይደለም ጀግኖቻችን አላግባብ እያዋረዳቹህ እኛንም እንደህዝብ ሃፍረትና ፍርሃት እያላበሳቹሁን ነው ብለው ለጠየቁ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከባድ ማስጠንቀቅያ ደረሳቸው። ይህ ሁኔታ በህወሃት ላይ ብቻ የታጠረ አልነበረም፣ በተለይ በኦህዴድና በዴህዴን ኢዴሞክራስያዊ እርምጃው በተመሳሳይ ሁኔታ ቀጠለ። በኢህአዴግ ውስጥ ለየት ያለ ሃሳብ ማቅረብ እንደ ነውር የሚታይበት ሁኔታ ተፈጠረ። ፍርሃትና ከዚሁ ከፈተኛ ፍርሃትና ሌሎች ፍላጎቶች የሚመነጭ አድርባይነት፤ (Opportunism) እና ሙስና በፓርቲው ካድሬ በሰፊው ተዛመተ።
ከዚህ ጊዜ በኋላ የህወሃት/ኢህአዴግ ባህሪይ የነበረውና የድርጅቱን ዴምክራሲያዊ ባህርይ መጠበቅ ላይ ቀላል ያልሆነ አስተዋፅዖ የነበረው የጋራ አሰራር መርህ (collective Leadership) አንድ ሰው የፈለገውን በሚወስንበት አሰራር ተተካ፡፡ በፓርቲው ውስጥና በሰራዊት ከትጥቅ ትግሉ ወቅት ጀምረው በትግል የቆዩ ነባር ካድሬዎችና የሰራዊት አባላት የራሳቸው ስብእናና አቋም ያላቸው እየተመነጠሩ ተባረሩ ወይም ራሳቸውን አገለሉ፡፡ እንደኔ አመለካከት ይህ ክስተት ሌላው የውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ ገድል በመክተት የዴሞክራሲ ምህዳሩን ያጠበበ ፖለቲካዊ ክስተት ነበር፤ አሁን ለደረስንበት ሁኔታም ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል።
በመቀጠልም ኢህአዴግ የውስጠ ፓርቲውን ችግር ፈትችያለሁ ባለበትና ለሕብረተሰቡም ለዓለም ህዝብም ዴሞክራስይዊ መልክ ለማሳየት በመፈለግ የ1997 ዓም ምርጫን ትንሽ ከፈት አደረገ። ሰፋፊ ክርክሮች ተደርገው ምርጫው ተካሄደ። በዚህ ምርጫ ተቃዋሚዎች ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ የድጋፍ መጠን አገኙ፤ በተለይ በርእሰ ከተማዋ አዲስ አበባን ሙሉ በሙሉ አሸነፉ። ኢህአዴግ ያልጠበቀውና ያልተዘጋጀበት የፖለቲካ ክስተት ነበር፤ እጅግም ተደናገጠ። ተቋዋሚዎቹም የተስማሙበትና ግልፅ የሆነ የፖለቲካ ስትራቴጂ የነበራቸው አይመስልም።
ተቃዋሚዎች የሀገሪቱን ፖለቲካዊ ስልጣን በአጠቃላይ ለመቆጣጠር ፍላጎት በማሳየት በጠቅላላው ምርጫ አሸንፈናል አሉ፡፡ ትክክለኛ ቁጥሮቹን እኔ አላውቃቸውም ግን ኢህአዴግ በአመነበት ደረጃ እንኳን ተቀብለው በሰላማዊ መንገድ ቢሳተፉ ምናልባት አሁን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ የተለያ ይሆነ ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ አዲስ አበባን ሙሉ በሙሉ ማስተዳደር በፖለቲካዊ ስርዓቱ ያለው ጫና በጣም ትልቅ ነው፡፡ ከዛ በተጨማሪም በፖርላማው ውስጥ እስከ ከ1/3 ድምፅ በላይ አግኝተዋል ተብሎ ታምኖበት ነበር፡፡ እነዚህ ሁለቱ ተደምረው በኢህአዴግ የሚመራው የሥራ አስፈፃሚ የፈለገውን ማድረግ የማይችልበት ሁኔታ ይፈጠር ነበር፡፡ ቀደም ብሎ እንደተገለፀው በራሳቸው መንገድ የመጡ፤ የሕብረተሰቡ ድጋፍ ያላቸው ፖለቲካዊ ሃይሎች ስለነበሩ በህግ አውጭው አካል የሚደረጉ ውይይቶች የተለያዩ ሃሳቦችንና አማራጮችን የሚያቀርቡ፣ ሕብረተሰቡ ይህንን እንዲያውቅ ለቀጣይ ምርጫ ደግሞ ቀላል ያልሆነ ትምህርት እንዲቀስም በእውቀት ላይ የተመሠረተ ምርጫ እንዲያደርግ ይረዳው ነበር፡፡ ውሳኔዎችም ካላቸው ጠቀሜታ እየተመዘኑ የሚወስኑበት ሁኔታ ይፈጥር ነበር፡፡ ይህ ክስተት በድርድር ቢፈታ ኖሮ ዴሞክራሲያዊ ሂደቱን በከፍተኛ ደረጃ ይጠቀም ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡
ከዚህ ከ1997 ዓ.ም ምርጫ ጋር ተያይዞ የሚነሳ አንድ መጥፎ ጠባሳ አለ፡፡ ይኸውም በምርጫ እኔ አሸንፊያለሁ እኔ አሸንፊያለሁ በሚል የተሟሟቀ ክርክር ውስጥ ቅንጅት በግልፅ በአደባባይ ዘረኛ የሆነ ፕሮፖጋንዳ ማስፋፋት ጀመረ፡፡ ውስጥ ለውስጥ በተደራጁ ሃይሎችም ይህንን ፀረ የትግራይ ተወላጆች የሆነውን ዘመቻቸውን አስፋፋው ይህንን ዘረኛ አስተሳሰባቸውን በተገቢው መንገድ አላስተባበሉም፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ ይህንን አድሃሪ ዘረኛ ፕሮፖጋንዳ አስተጋባው ሊፈጁህ ነው፡፡ የሩዋንዳ ዓይነት መገዳደል ይከሰታል ማለት ጀመረ፡፡ ይህ ሁኔታ ሕብረተሰቡ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በትክክለኛ መንገድ ሳይሆን የፖለቲካ ሃላፊዎች በሚፈልጉት መንገድ እንዲያይ አደረገው፡፡ ቢያንስ የትግራይ ተወላጅ የሆነውን አስደነገጠው፡፡ ይህ ለፀረ ዲሞክራሲያዊ ሃይሎች ምሽጋቻውን ለማጠናከር ጠቀማቸው፡፡ ይህ መጥፎ የፖለቲካ ጨዋታ የፈጠረው ጠባሳ እስከ አሁንም ድረስ ሙሉ በሙሉ አልሻረም፡፡ አሁንም እንደመጠቀሚያ መሳሪያ ይነሳል፡፡
በዚህ ሁኔታ ኢህአዴግ ከተቃዋሚዎች የሚሰነዘርበትን ተቃውሞ መቋቋም የቻለው በመቶዎች የሚቆጠር የሰው ሂወት በመግደል ነው። የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችንና አባላትም ወህኒ ወረዱ። በዚህ ሂደትም ሁለት ግልፅ የሆኑ መልእክቶች ተላለፉ። አንድ፥ የፖለቲካ ስልጣን እንዲሁ በቀላሉ በምርጫ አሸንፍያለሁ ስለተባለ እንደማይሰጥ። ሁለት፥ የመንግስትን ስልጣን የተቆጣጠረው አመራር ስልጣኑን በሰላማዊና ዴሞክራስያዊ መንገድ ለመጋራት ያሸነፈን የፖለቲካ ሃይል በሰላማዊ መንገድ ማስተናገድ ሳይሆን የፀጥታ ሃይሎችን ተጠቅሞ እንደሚያጠፋ ግልፅ ሆነ። የኢህአዴግ መንግስት በፖለቲካዊ አስተሳሰብ ብልጫና ይህ ብልጫ የሚያስገኝለትን የሕብረተሰብ ድጋፍ ሳይሆን የመንግስት ስልጣን በመቆጣጠሩ የሚያገኘው የፀጥታ ሃይሎች ድጋፍ በስልጣን መቆየት መወሰኑን ግልፅ አደረገ።
ይህ ክስተት በፓርቲው ብቻ ታጥሮ የነበረውን ፍርሃትና አድርባይነት ወደ ጠቅላላ ሕብረተሰቡ እንዲጋባ አደረገ፡፡ መንግስትን በተለይ የፀጥታ ሃይሎችን ፈርቶ ተሸማቆ እነሱ መስማት የሚፈልጉትን እየተናገሩና እነሱን እያስደሰቱ መኖር “አዋጭ” የፖለቲካ ባህርይ ሆነ።ክዚህ እየተነሱም ሃላፊዎች የሚፈልጉትን የፖለቲካ አቋም፣ ቃላቶች ሳይቀይሩ አለቆችን ለማስደሰት መደጋገም ከፓርቲው አልፎ ወደ ሕብረተሰቡ በስፋት ገባ። ገዢውን ፓርቲ ፈርቶና “ፀባይን አሳምሮ” በአድርባይነት መኖር ዋነኛው የፖለቲካ “ጥበብ” ሆነ፡፡
በመሆኑም ከላይ የተገለፁት ሁኔታዎች እርስ በርሳቸው እየተደጋገፉ በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ራሱ የፖለቲካ ድርጅቱ በመሪነት ያፀደቀው ሕገ መንግስት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ባልቻለበት ሁኔታና፣ ሕገ መንግስቱን የሚገድቡ የተለያዩ ሕጎችን በማውጣትና በፀጥታ ሃይሉ ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚችሉበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። በኔ እምነት ጨቋኞች ህዝቡን ጨቁነን እንገዛለን የሚል ግልፅ የፖለቲካ ውሳኔ ወስነው የጭቆና ስርዓት አይዘረጉም። በአህአዴግ ውስጥ ያለው ሁኔታ በንግግር እኛ እናውቅልሃለን ለህዝብ ጥቅም ቆመናል እየተባለ በተጨባጭ ሂደቱ ግን ህዝብን እያስፈራሩና እየጨቆኑ መግዛት ሆኗል።
ሆኖም ይህ ከላይ የተገለፀው ሁኔታ ረጅም መቆየት ስለማይችል ሕብረተሰቡ ከሚሸከምው በላይ ስለሆነበት የመንግስት የስራ አስፈፃሚው አካል በሕብረተሰቡ ላይ የሚፈፅመው በደል ስለበዛበት፣ ከዚሁ ጋርም የኑሮ ውድነቱ፣ ስራ አጥነቱ፣ ለችግሮቹ መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ ግልፅ አቅጣጫዎች አለማየቱ ጋር ተቀላቅሎ የኢህአዴግ መንግስት በምርጫ መቶ በመቶ አሸንፍያለሁ ባለበት ማግስት በከፍተኛ የህዝብ ተቃውሞ እና ሌሎች ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ገብቷል። ይህ ሁኔታ ደግሞ ቢያንስ ችግሮቹ የሚገለፁበትን መልክ በማንሳት በግልፅ ችግር አለብኝ እንዲል አስገድዶታል። ከላይ ከተጠቀሰው ፖለቲካዊ ሁኔታ ተነስቼ ሃገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ ሶስት ቢሆኖች (scenarios) ያሉ ይመስለኛል።
ቢሆኖች (Scenarios)
አንደኛ ቢሆን አገሪቱ ከውስጥ የህዝብ ጥያቄ በሚፈጠረው ብጥብጥ ምናልባት የውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነትና የሃይል ጫና ተጨምሮበት መንግስት መቆጣጠር ከሚችለው በላይ ሁኖ የመንግስት መፈራረስና ሁከት መፍጠር ሊመጣ ይችላል። ይህ አማራጭ የመከስት እድሉ አነስተኛ እንኳን ቢሆን እንደ አንድ ሊሆን የሚችል ጉዳይ ታይቶ እንዳይከሰት መስራት ያስፈልጋል። የመሆን እድሉ ግን ዜሮ አይደለም። ባላፈው በኦሮምያ ተፈጥሮ የነበረው የህዝብ አመፅ የመንግስት መዋቅር ላይ በተለይ በክልሉ መንግስታዊ መዋቅር ላይ ፈጥሮት የነበረ ጫና በጣም ከፍተኛ ነው። በፌዴራል መንግስት የፀጥታ ሃይሎች ጣልቃገብነት ነው አመፁ የቆመው። አመፁ በስፋትም በግዜም ቢቀጥል ኖሮ በተጨማሪም ሌሎች ተጓዳኝ የህዝብ አመፆች ቢነሱ ኖሮ በማዕከላዊ መንግስት ላይ ሊፈጠር ይችል የነበረው ችግር መገመት አይከብድም።
ሁለተኛ ቢሆን ረዘም ላለ ግዜ አሁን ባለው ቀውስ ውስጥ መቆየት ነው። ይህ ከሁሉም አማራጮች የመሆን እድሉ የላቀ ነው። አሁን በስልጣን ላይ ያለው ገዢ ፓርቲ በጠቅላላ ይሁን በተወሰነ ክፍሉ መጠነኛ ለውጦችን በውስጡ በማድረግ በግልፅ ያመነበትን የመልካም አስተዳደር እጦትና ሙስና ቴክኒካዊ፣ አስተዳደራዊ ትርጉም በመስጠት በዚህ ዓይነት ማዕቀፍ ውስጥ በመሆን ለመፍታት በመሞከር የተወሰነ ግዜ የጣላቸው የስራ ሃላፊዎችን በማስወገድ ከቀውሲ ለመውጣት ግዜ ለመግዛት በመፈለግ የሚፈጠር ሁኔታ ሊመጣ ይችላል። አሁን በስልጣን ላይ ያለው ገዢ ፓርቲ በተፈጥሮ ሊያደላበት የሚችል የመጀመርያ ምርጫው የሚሆን በመሆኑ የመከሰት ዕድሉ የሰፋ አማራጭ ነው። ይህ አማራጭም ችግሩን ለተወሰነ ግዜ ሊያዘገየው እንደሆነ እንጂ አይፈታውም።
ለተወሰነ ግዜ በማዘግየት ችግሩ ይበልጥ ስር እየሰደደ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለውም እድል እየጠበበ እንዲሄድ ያደርጋል። በዚህ ግዜም በሃገሪቱ ያለውን ቀውስ እየተባባሰ ከመሄዱም በላይ በመጨረሻም በጣም አውዳሚ በሆነ መንገድ ችግሩን ለመፍታት ለሚፈልጉ ሃይሎች የተመቻቸ ሁኔታ ይፍጥርላቸዋል። ስለሆንም ፈጥኖ የሚታየው የመፍትሔ አቅጣጫ የመሆን እድሉም የሰፋ አማራጭ ሆኖ ሳለ ለሃገሪቱ አሁን የሚያስከፍለው ዋጋ ይህን ኋላ በሚያስከትለው ነውጥ እጅግ የከፋው ነው፡፡ ይህ ሁኔታ እስከ አሁን ድረስ የተመዘገቡትን ድሎች ጠራርጎ ያጠፋል፡፡ አገሪቱን ወደኋላ ይመልሳል ብቻ ሳይሆን ቀጥሎ የሚመጣውም ምን ዓይነት ስርዓት እንደሆነ መተንበይና መገመት አይቻልም፡፡ እነዚህ ሁለት አማራጮች በጊዜ ሊለያዩ ካልሆነ በስተቀር በጣም ተመሳሳይ ናቸው። በራሳቸው መንገድ የሚከሰቱም ስለሆኑ እንዳይከሰቱ ምን እናድርግ በሚለው ሃሳብ ላይ ካልሆነ በእነሱ ላይ ብዙ መናገር አይቻልም።
ሶስተኛ ቢሆን ሰላማዊ፣ ስርዓት ያለው፣ በንቃት የሚመራ፣ ለውጥ መጀመር ነው። ይህ ማለት አሁን በሃገራችን ፖለቲካዊ ቀውስ እንዳለ በማመን ይህንን ቀውስ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን ተከትለን በሰፊ የፖለቲካዊ ሃይሎችና የምልአተ ህዝቡ ተሳትፎ ለመፍታት የሚያስችል ፖለቲካዊ ሂደት መጀመር ነው። ይህ አማራጭ ከላይ የተገለፁትን ሌሎች ቢሆኖች እንዳይከሰቱ ለማድርግ ያስችላል። በመሆኑም በሃገራችን የወደፊት እድል ያገባናል የምንል ዜጎች በሙሉ ተንቀሳቅሰን እውን እንዲሆን ማድረግ አለብን የሚል እምነት አለኝ። የዚህ ፖለቲካዊ ሂደት ዓላማና እንዴት ሊፈፀም ይችላል የሚለውን ሃሳብ መጨረሻ ላይ እመለስበታለሁ።
የትግራይ ህዝብ
በሃገራችን ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ስላለው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጉዳይ ስናነሳ የትግራይን ህዝብ ለብቻ ነጥሎ ማንሳት ለምን አስፈለገ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ተገቢ ጥያቄ ነው። እዚህ ላይ ማንሳት የምፈልገው ጉዳይ የትግራይ ህዝብ በታሪኩ ራሱን ኢትዮጵያ ለምትባለው ሃገር መመስረትና በታርኳ ውስጥ በተለያዩ ውድቀቶችም ይሁን ድሎች ዋና ተዋናይ አድርጎ ነው የሚያስበው። ከዚህ ውጭ በሌላ መንገድ አያስብም። አሁንም ችግሮችን ስናነሳና መፍትሔ ስንፈልግ በዚህ በታሪክ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው አስተሳስብ ውስጥ ሁነን ነው። የትግራይ ህዝብ ለብቻው የሚያስበው መፍትሔ አልነበረም፣ የለም። አሁን ባለው ከላይ የተገለፀው የሃገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ተነስተን መፍትሔ ስናፈላልግ የትግራይ ህዝብ ምን ማድረግ ይጠበቅበታል? አሁን ባለው የፖለቲካ ሁኔታ ራሱን እንዴት ያስቀምጣል? ለሚለው ጥያቄ መፍትሔ ሲፈለግ ለትግራይ ህዝብ ብቻ የተለየ ከዛ አንፃር ብቻ የተቃኘ ሳይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራስያዊ ስርዓት ለማስፈን፣ ከዚህ ስርዓትም እንደ ማነኛውም የኢትዮጵያ ህዝቦች እኩል ተጠቃሚ እንዲሆን በማሰብ ነው።
የትግራይ ህዝብ ይህ አሁን ያለውን የፖለቲካ ስርዓት ለማምጣት ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በመሆን ታግሎ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሎ ያመጣው ነው። በመሆኑም እስካሁን ድረስ ይሁን ለወደፊትም ስርዓቱን ለህዝብ ጥቅም እንዲውል ከማድረግ አንፃር ያለው ድርሻ ከፍተኛ ነው። በተለይ ደግሞ እንደ ህዝብ በዘለቄታው ጥቅሙ የሚከበርለት በሕገ መንግስት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራስያዊ ስርዓት ሲገነባ ስለሆነ።
አሁን በትግራይ ወጣቶችና ጉዳዩ ያሳስበናል ብለው የሚያምኑ የትግራይ ተወላጆች ቀደም ብሎ በተነሳው ጥያቄ ላይ ግልፅ የሆነ ሃሳብ የለም፡፡ በመሃል አገር ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች በትግራይ ተወላጆች ላይ ጥላቻ ይንፀባረቃል። የትግራይ ህዝብ በስርዓቱ እላፊ ተጠቃሚ እንደሆነ ተደርጎ ይወራል፣ ይታያል። ተጨባጭ ሁኔታው ደግሞ ከዚህ የተለየ ነው። በርግጥ ሁኔታውን ህዝብን በማጣላት እንጠቀማለን ብለው የሚመኙ ፀረ ዴሞክራሲ ሃይሎች ያራግቡታል። እነዚህን ሃይሎች ካሰቡትና ከተመኙት ውጭ ማሳመን አይቻልም። ግን ደግሞ ተጨባጭ የህዝቦች መራራቅ አለ። ይህ ለምን መጣ? እንዴት እንፍታው ብሎ ማሰብና መወያየት ተገቢ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም የትግራይ ተወላጅ በመሆኔና ከዚህ ህዝብ ጋር በተለያዩ ሁኔታዎች ሁኜ ስለታገልኩና ስላታገልኩ ሁኔታውን በተሻለ አውቀዋለሁ፤ ስለዚህ የሚታየኝ ሃሳብ የማቅረብና ቢያንስ ይህ አሳሳቢ ጉዳይ የሕብረተሰቡ አጀንዳ ሆኖ እንድንወያይበት፣ ሃሳብ እንድንለዋወጥበት ማድረግ ይገባል ብየ ስላመንኩበት ነው።
አሁን ባለችው ኢትዮጵያ የትግራይ ህዝብ የሚኖረው ድርሻና የሚጫወተው ሚና ምን መሆን አለበት? የትግራይ ህዝብ የስልጣን ዘመኑን በፀጥታ ሃይሎች ድጋፍ የሚያራዝም በየግዜው ከህዝብ እየተነጠለና በህዝብ እየተጠላ የሚሄድን የፖለቲካ ስርዓት ጠባቂና ተከላካይ ነው መሆን ያለበት? ወይስ ሌላ ምርጫ አለው? የትግራይ ህዝብ አሁን ባለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ የሚወስደው የፖለቲካ አቋም ምን ይሁን? ብሎ መጠየቅ ይገባል። በሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦችስ ሕገ መንግስታዊ መብታቸውን የሚጥስ ፖለቲካዊ ስርዓት ጠባቂ ተደርጎ የተለየ ጥቅም የሚያገኝ ጠላት ተደርጎ ነው መታየት ያለበት ወይስ በዴሞክራሲና በእኩልነት ላይ ለተመሰረተ የህዝቦች አንድነት ፣ ለህዝቦች መብት መከበር ለትክክለኛ ፍትሕና ለፍትሃዊ ኢኮኖምያዊ ተጠቃሚነት በፊታውራሪነት የሚታገል ህዝብ ተደርጎ ነው መታየት ያለበት? ብለን እየጠየቅን መልሱን መፈለግ ይኖርብናል።
ወደ ዝርዝር ጉዳይ ከመግባቴ በፊት በህወሃት መሪነት የተካሄደው የትጥቅ ትግልና፣ ይህ ትግል ያስመዘገበው ድል ዴሞክራስያዊ፣ አብዮታዊና ትክክለኛ ነበር የሚል እምነት አለኝ። ደርግን የመሰለ ፀረ ዴሞክራሲ አፋኝ መንግስትን ታግሎ መጣል ዴሞክራስያዊም አብዮታዊም ነበር። ለጭቁን ህዝቦች መብት መረጋገጥ የተደረገ ትግል ዴሞክክራስያዊ ካልሆነ ዴሞክራስያዊነት ምን ሊሆን ነው። ስለሆነም በህወሃት መሪነት በተደረገው ትግል በተለያዩ ደረጃዎች በተራ ተዋጊም በከፍተኛ አዛዥነትም ቦታ ላይ ሆኜ መሳተፌ እኮራበታለሁ። እነዚያን ጀግኖች እየመሩ የእነሱን ጥረት እያስተባበሩ ለድል መብቃት በታሪክ መታደል ነው እላለሁ፡፡ ይህ ማለት በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደገለፅኩት ህወሃት የአማልክት ስብስብ ነበር ስህተት አልነበረውም፣ ችግሮች አልነበሩም ማለቴ አይደለም። በድምር ሲታይ የደርግን ስርዓት ለማሸነፍና ለመጣል በተደረገው ትግል ውስጥ ዴሞክራስያዊና አብዩታዊ ባህሪው ከሁሉም በየግዜው ሲያጋጥሙ ከነበሩ ችግሮች ያመዘነ የበለጠ ነበር። ስለሆነም ነው በአሸናፊነት የዘለቀው የሚል እምነት አለኝ።
የትግራይ ህዝብ የደርግን ጨቋኝ ስርዓት ለመጣል ከፈተኛ ዋጋ ይክፈል እንጂ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች እላፊ ጥቅም ለማግኘት አልተመኘም፤ በተጨባጭም አላገኘም። በፌዴራል መንግስት በርከት ያሉና ወሳኝ የሚባሉ የሚኒስቴር ቦታዎች መያዝና በዚህ ሳብያ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ባላቸው ቅርበት የተወሰነ ጥቅም የሚያገኙ የትግራይ ተወላጆች ካሉ የትግራይ ህዝብ የእላፊ ጥቅም ማግኘት ማስረጃዎች ተደርገው መወሰድ አይችሉም። ይባስ ብሎ በራሱ ጥረት ብዙ ችግሮችን ተቋቁሞ በኢኮኖሚው ረገድ ደህና የተራመደውም በእነዚህ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ተጠግተው ጥቅም ከሚያገኙት ጋር እየተደመረ እንዲታይ ስለዚህም የሌሎች ህዝቦችን አሉታዊ ስሜት ማነሻሻም እየሆነ ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ ያገሪቱ ህግ በሚፈቅደው መሰረት ስራውን ሰርቶ ሃብት አፍርቶ ለመኖር የሚፈልገውም የትግራይ ተወላጅ ቀላል ያልሆነ ስጋት ውስጥ ከቶታል፤ ይህ መሆን የሌለበት ጉዳይ ነው።
የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ህዝቦች የተለየ እላፊ ጥቅም አልፈለገም ሲባል ለሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች የሚሰጠው መብትና ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት ስርቶ መበልፀግ ስብአዊና ፖለቲካዊ መብቶች በሚገባ ተከብረውለት መኖር ደግሞ ማንም ሊከለክለውና ሊነጥቀው አይገባም፤ በእኩልነት በመፈቃቀድ ህዝቦች መብቶቻቸው ተጠብቀውላቸው ተከባብረው የሚኖርባት ሃገር እንድት ሆን ነው ያን ሁሉ ዋጋ የተከፈለው። ይህንን ደግሞ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በመሆን ሊጠብቀው ይገባል፤ ድርሻውን የሚነጥቀው ሃይል እንዲኖር አይፈቅድም።
ከላይ የተቀመጡት ሃሳቦችን መነሻ በማድረግ በእኔ አመለካከትና እምነት የትግራይ ህዝብ የሰብአዊና የፖለቲካዊ መብቶች በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ የህዝቦች አንድነት በፍትሕ ላይ ለተመሰረተ የህዝብ መብት ጥበቃ፤ ይህንን መሰረት አድርጎ ለሚመጣ ኢኮኖምያዊ ብልፅግና ማህበራዊ ልማት ለማምጣትና እነዚህን መብቶች ስፋትና ጥልቀት ኖሯቸው ተግባር ላይ እንዲውሉ የሚታገል መሆን አለበት እላለሁ። እነዚህ በህገ መንግስቱ የሰፈሩ መብቶች ሳይሸራረፉ ሳይገደቡ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆኑ ጊዜው ሲፈቅድ ደግሞ ስፋትም ጥልቀትም እንዲኖራቸው በመታገልና ተግባር ላይ እንዲውሉ በማድረግ ነው፡፡ እንደ ህዝቡ ጥቅሙ የሚከበረው፡፡ ከዚህ ውጭ ግን በተወሰነ ታሪካዊ አጋጣሚ ስልጣን ላይ የወጡ ከሱ የፈለቁ መሪዎችን የስልጣን ዕድሜ ለማራዘም ሲባል መንግስታዊ መብቶችን የሚገድቡ ህጎችና መመሪያዎችን መደገፍ የለበትም እላለሁ፡፡
እዚህ ላይ በርከት ባሉ የትግራያ ተወላጆች የሚነሳ አንድ ጥያቄ አለ፡፡ ይኸውም አሁን ባለው መንግስት ላይ ያለንን “የበላይነት” ካጣን ጠቅላላ መብቶቻችን አንድናጣ መልሰን እንድንጨቆን አድልዎ እንዲፈፀምብን ቢደረግስ ምን ዋስትና አለን? የሚል ነው፡፡ ዋስትናችን በትግላችን ያገኘነው አሁንም ከሌሎች ህዝቦች ጋር ሆነን እየታገልን የምንጠብቀው ሕገ-መንግስታችን ያለምንም ማቅማማት ተግባራዊ ማድረግ ነው። ሌላው ዋስትናችን ህዝቡ ራሱ ነው፡፡ የተወሰኑ የክልሉ ተወላጆች በፖለቲካዊ ሥርዓቱ ወሳኝ በሚባሉ የሥልጣን ቦታዎች ላይ መቀመጥ አይደለም። አሁን በኢትዮጵያ ያለው ሕገ-መንግስት የትግራይ ህዝብ ሙሉ በሙሉ ሊጠብቀውና ሊተገብረው የሚፈልገውን ያህል፣ የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የአፋር፣ የሶማሊ፣ የሐረሪ፣ የደቡብ እና ሌሎች ህዝቦች ሊጠብቁት እና ተግባር ላይ እንዲውል የማይፈልጉበት ምክንያት የለም። አሁን ያለው ሕገ-መንግስት የሚቃወሙ ሃይሎች እንዳሉ አውቃለሁ። ከነዚህ በላይ ግን ሕገ-መንግስቱ ሲጸድቅ በነበረው አብዮታዊና ዴሞክራሲያዊ መንፈስ አለመተግበሩ የሚቃወሙ ይበዛሉ፡፡ ከዚህ የተነሳም ሙሉ በሙሉ ተግባር ላይ ከዋለ ህገ-መንግስቱን የሚጠብቀው፣ የሚያዳብረው ኋይል ይበዛል ያሸንፋል። ይህንን ሕገ-መንግስት መጠበቅ በሚል ሰበብ አሁን ያለውን ስርዓት የመጠበቅ ሸክም ለምን በትግራይ ህዝብ ጫንቃ ላይ ብቻ ይወድቃል?
እዚህ ሊነሳ የሚገባ አንድ ጉዳይ አሁን ያለው የፌዴራል መንግስት አወቃቀር መሠረት ያደረገ ህገ-መንግስታዊ ሥርዓት ሕገ-መንግስቱ እራሱ በሚፈቅደው አሰራር ተቀባይነት ላያገኝ ይችላል። በሌላ አነጋገር አዲስ ህገ-መንግስት ያስፈልጋል የሚል ሐሳብ አሸናፊ ሊሆን ይችላል። ይህ የሕገ-መንግስቱ አሰራር ተከትሎ ህዝቡን አሳምኖ በሰላማዊ መንገድ እስከተፈጸመ ድረስ የህዝብ ፍላጎት ነውና ተቀባይነት ማግኘት አለበት። አሁን ያለው ህገ-መንግስት በህዝብ ዘንድ በፍቃደኛነት ተቀባይነት እንዲኖረው ይህንን ሕገ-መንግስት የሚደግፉት ፖለቲካዊ ሃይሎች ሥራቸው ሰርተው በሰላማዊ መንገድ ካላሸነፉ ተሸንፈዋል ማለት ነው። ስለዚህ ህዝብ በመረጠው መንገድ ሥርዓቱ ይዘረጋል። እኔ ይህ ሁኔታ ሊከሰት ይችላል የሚል እምነት የለኝም፣ ግን ደግሞ የሚበልጠው ህዝብ አምኖበት በፈቃደኝነት ተግባር ላይ የሚውል እንጂ በጸጥታ ሃይሎች እየተጠበቀ ተግባራዊ የሚሆን ህገ-መንግስት ሊኖረን አይገባም።
በዚህ ጉዳይ ላይ በተለይ በቅርብ ቀናት ከብዙዎቹ ጓደኞቼ ጋር ስንወያይ፣ በአንድ የውይይት ወቅት ሃሳቡ ተነሳና “የትግራይ ህዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር ባለው ግንኙነት፤ በተለይ አሁን ጠንክሮ መገኘት አለበት፣ የደከመ መስሎ መታየት የለበትም” የሚል ሃሳብ ቀረበና “ጠንክሮ መገኘት አለበት ማለት ምን ማለት ነው?” በሚለው ተወያየን። ይህ ነጥብ በሌሎችም ይንሳል ብየ ስለማስብ ያለኝን አመለካከት ልግለፅ።
ጠንክሮ መገኘት ማለት የመከላከያና የድህንነት ሃይል በመቆጣጠርና በማሰማራት ኢህአዴግና ይህ ድርጅት የሚመራው መንግስት የሚወስነው ውሳኔ ህዝብ ወደደሞ ጠላም ተቀብሎ እንዲሄድ ለማድረግ መንቀሳቀስ ነው? ወይም በፌዴራል መንግስት በንፅፅር ሲታይ በአገሪቱ ፖለቲካዊ ስርዓት ላይ ወሳኝ የተባሉትን የስልጣን ቦታዎች በብዛት መቆጣጣጠር ማለት ነው? ከዚህ አልፎም በየሄዱበት በተገኘው አጋጣሚ ሃይል ያለን መሆናችንን ለማሳየት መሞከር ነው? በአጠቃላይ ከኢህአዴግ በፊት የነበሩ ገዢ መደቦች ሲያደርጉት የነበረውን ለመኮረጅ መሞከር ነው ጠንክሮ መገኘት ማለት? ምንድን ነው? እኔ የትግራይ ህዝብ በጠቅላላውም የኢትዮጵያ ህዝብ “እንዲጠነክሩ” እፈልጋለሁ፤ አጋጣሚውን ሳገኝም ለዚሁ እሰራለሁ። ለእኔ ጠንክሮ መገኘት ማለት ከሁሉ በላይ የተሻለ ተራማጅ ሕብረተሰብን፤ የተረጋጋ ሰላም የኢኮኖሚ ብልፅግና ማህበራዊ ልማት፤ ዴሞክራስያዊ፤ ፍትሕ የሰፈነበት ሰርዓት፤ ለመመስረት የሚደረግ ጥረት ባለቤት በመሆን ለዚህ ዓላማ ግንባር ቀደም ተዋጊ መሆን ነው።
ከትክክለኛ ዓላማ የሚነሳ ይህ ትክክለኛ ዓላማና ፍትሃዊ በሕግ የሚገዛ ስርዓት የሚፈጥረው ውስጣዊ አንድነት ነው ጥንካሬውን የሚፈጥረው። ክዚህ ቀደምም በትጥቅ ትግሉ ወቅትና በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ጥንካሬውን የፈጠረው ትክክለኛ ፖለቲካዊ አመለካከት ነው፡፡ በህዝቦች እኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነት በሕገ መንግስታዊ ዴሞክራስያዊ ስርዓት ተግባራዊነት ላይ የተመሰረተ እምነት ነው፡፡ ፖለቲካዊ ስርዓቱን ለመከላከል ነው በታላቅ ጀግንነት የተዋጋው፡፡ ይህ ፖለቲካዊ እምነት ነው፡፡ ውስጣዊ ጥንካሬውና ጀግንነቱን የፈጠረው፡፡
በትጥቅ ትግሉ ወቅት የዓፋር፣ የቤንሻንጉል፣ የጋምቤላ፣ የኦሮሞና የአማራ ህዝቦች ከትግራይ ህዝብ ጋር ሆነው በጋራ የተዋደቁት የተለየ ሚስጢር ስለነበረን አይደለም። ያኔ የትግራይ ህዝብ በመሪ ድርጅቱ ህወሃት እየተመራ ሲያራምደው የነበረ ትግል እነሱንም የሚመለከት መሆኑን በንግግር ሳይሆን በተግባር ስላዩት ነው። የትግራይ ህዝብም የሰው ልጅ ሊሸከመው ይችላል ወይ ተብሎ ሊጠየቅ የሚችል ግፍና ጭፍጨፋ ተሸክሞ ከባድ መስዋዕትነት ክፍሎ እንደ ህዝብ በከፍተኛ ጀግንነትና ቆራጥነት የተዋጋው ፖለቲካዊ ዓላማው ትክክለኛ መሆኑን በተግባር እያየው ስለሄደ ነው፤ ከተጨባጭ ተሞክሮም ይህንን ስላረጋገጠ ነው። ጥንካሬ ማለት ይህ ነው። በረጅምና መራራ ትግል የደርግ ስርዓት መፈራረስ የጀመረው በመጨረሻም የደርግን ስርዓት ሲያገለግል የነበረውን የኢትዮጵያ ሰራዊት በአስር ሺዎች እጁን ሲሰጥ የነበረው እኛ የትግራይ ታጋዮች የተለየ ጀግንነት ስልነበረን እነሱ ደግሞ ፈሪዎች ስለነበሩ አይደለም፤ እነሱም ጀግኖች ነበሩ፣ ግን የቆሙለት ዓላማ ከዳቸው፣ የቆሙለትን ፖለቲካዊ ዓላማ አምነው መከላከል ተሳናቸው፡፡ ውስጣዊ ጥንካሬያቸው በየግላቸው መፍረስ ጀመረ፡፡ ሌሎችን ጨቁኖ በመግዛቱ ላይ በተመሠረተ ፖለቲካዊ ዓላማና በብልሹ አስተዳደር የሚመራ ሰራዊት ደግሞ ውስጣዊ ጥንካሬ ይኖረዋል ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ ይህ ለማንኛውም የህዝብን ጥቅም ለማያስጠብቅ ስርዓት ይሰራል፤ ለደርግ ብቻ የተሰጠ ስጦታ አልነበረም።
ሁለተኛው ጉዳይ እኛ ሃገራችንን በጠቅላላ ጠንካራ ለማድረግ ከዚህ ጋር አያይዘን ደግሞ የድርሻችን የሆነውን የትግራይ ህዝብ ጠንካራ ለማድረግ የምንችለው በዋናነት እዛው ትግራይ ውስጥ በሚሰራ ስራ ነው። በፌዴራል መንግስት የሚኖረንን ድርሻ ከላይ የተገለፀውን ፖለቲካዊ ዓላማ (ማለትም በህዝቦች እኩልነትና መፈቃቀድ የተመሰረተ አንድነት እንዲጠነክር፣ ሕገ መንግስቱና ስብአዊና ፖለቲካዊ መብቶችም ሳይሸራረፉ ተግባራዊ እንዲሆኑ የመንግስት ተጠያቂነት እንዲጎለብት ፍትሕ የነገሰበት ስርዓት እንዲሰፍን ውዘተ) እየታገልንና ይህንን ትግል ሳናኮላሽ ክዚህ ጎን ለጎን በትግራይ ውስጥ የአገሪቱ ሕግና አቅማችን የፈቀደልንን ያህል ከላይ ከተገለፁት ፖለቲካዊ ስራዎች በተጨማሪ ኢኮኖምያዊ ብልፅግና ማህበራዊ ልማት እንዲስፋፋ ሌት ተቀን መስራት ይኖርብናል። የትግራይ ክልል በህዝቡ ጥረትና ብቁ አመራር በመስጠት የኢኮኖምያዊ ዕድገትና ዴሞክራስያዊ ስርዓት የሰፈነበት እንዲሆን ማድረግ ይጠበቅብናል። ይህ እንዲሆን የትግራይ ህዝብ ብዙ ዋጋ ከፍልሏል። ይህ እንቅስቃሴ በትግራይ ላይ ብቻ ይደረግ ወይም ከሌሎች ክልሎች እላፊ ያግኝ አላልኩም፣ ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት አቅማችንን አሟጠን እንጠቀም ነው እያልኩኝ ያለሁት፤ የኛ ድርሻ ይህ ነው። ሌሎቹም ድርሻቸውን በበኩላቸው ይወጡ፤ የዚህ ድምር ውጤት አገራችንን ጠንካራ ያደርጋታል።
አሁን ትግራይ ውስጥ ያለው ሁኔታ ይህንን ሁኔታ አይገልፅም። የክልሉ ተወላጆች ሃብታቸውንና እውቀታቸውን ተጠቅመው ለማልማት ሲፈልጉ ሁኔታዎች ምቹ አይደሉም። የትግራይ ክልል በመልካም አስተዳደር፣ በኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ ለክልሉ ተወላጆች ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የተመቸ መሆን ሲገባው፤ አሁን ያለው ሁኔታ ግን ከዚሁ የራቀ ነው። ትንሽ በትምህርት ገፋ ያደረገውና ሃብት ያከማቸው ክልሉን እየተወ አዲስ አበባ ላይ ነው ስራውን የሚሰራው። ይህ የትግራይን ህዝብ በቀጣይነት ደካማ እያደረገ የሚሄድ ነገር ነው። ለእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ መፈጠር በመሃል ሃገር ያለው ኢኮኖምያዊ ዕድሎች (Opportunities) አስተዋፅኦ እንደሚያድርግ ይገባኛል። ይህ ኢኮኖምያዊ ዕድል ባለሃብቶችን የመሳብ ዓቅም እንዳለው ግልፅ ነው። ከዚሁ ጋር ግን በትግራይ የተመቻቸ ሁኔታ ባለመፈጠሩ የሚሸሸው ባለሃብት ደግሞ ብዙ ነው። ዋናው ጉዳይ ግን ህወሃትና የክልሉ መስተዳድር እንዴት አድርገን ነው መግፋቱን ትተን መሳብ የምንችለው ብሎ ሌት ተቀን መጨነቅ አለበት። አሁን ላለው ሁኔታ መፈጠር ትልቁን ሃላፊነትና ድርሻ የሚወስደው አሁን ያለው የህወሃትና የክልሉ መስተዳደር ነው። የትግራይ ህዝብ በትግሉ ወቅት ይሁን ከዛ በኋላ ባፈራቸው ከሁሉም የላቀ እወቀት ችሎታና ይህንን ለመተግበር ቁርጠኝነት አላቸው ብሎ በሚያምንባቸውና በዴሞክራስያዊ መንገድ በሚመርጣቸው ሲፈልግም በሚያወርዳቸው ልጆቹ መመራት አለበት። ሁለተኛው ዋስትናችን ራሳችን ይህንን ስራ ስንሰራ ነው፡፡
የመከላከያ ሠራዊት ሚና
ከግንቦት 17-21 1993 እ.ኤ.አ ኢህአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ ከሁለት ዓመት በኋላ አዲስ አበባ ላይ አንድ ትልቅ ሲምፖዚየም ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ይህ ሲንፖዚየም የመወያያ አጀንዳው በሚቀረጸው ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓት ላይ ሰፊ ውይይት ማካሄድ ነበር፣ ሲምፖዚየሙ “Symposium on the making of the new Ethiopian constitution” ተብሎ ነበር የተሰየመው። በአለም አቀፍ ደረጃ እጅግ ከፍተኛ ዝና የተጎናጸፉ ሙሁራን ከተለያዩ አገራት መጥተው በዚህ የአራት ቀናት ሲምፖዚየም በጣም ጥልቀት ያላቸው ሀሳቦችን በተለያዩ መስኮች አቅርበዋል። በዚህ ሲምፖዚየም እኔም በኢትዮጵያ የሚመሰረተው ሰራዊት በተመለከተ ሃሳብ እንዳቀርብ ተጋብዤ ነበር። በስምፖዚየሙ ተገኝቼ ሐሳቡን አቅርብያለሁ። ይህ ፅሁፍ ሲቀርብ እንደ የግል አስተያየት ሆኖ ቢቀርብም በወቅቱ ከመለስ ጋር በስፋት ተወያይተንበታል፡፡ ይህ ማለት በፅሁፍ የቀረቡት ሃሳቦች አስራሩን ተከትለን የድርጅት አመራር ውሳኔ አልተሰጠበትም እንጂ የድርጅቱ የኢህአዴግን በሰራዊት ግንባታ ላይ የነበረውን መሠረታዊ አስተሳሰብ ያንፀባርቅ ነበር ማለት እችላለሁ፡፡ በኋላም በዚህ በቀረበው ጽሁፍ ውስጥ ያሉትን ዋና ዋና ጉዳዮች እንደ መመሪያ ልንጠቀምባቸው ሞክረናል።
በሲምፖዚየሙ በቀረበው ጽሑፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ሀሳቦች ተሰንዝሯል። ያኔ አሁን Security Sector Reform /SSR/ እየተባለ የሚጠራውና እጅግ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘው አስተሳሰብ ገና ሳይታወቅና ስምም ሳይወጣለት በመሰረቱ ይህ አስተሳሰብ የሚመራባቸው አንኳር አንኳር ሀሳቦችን ለሠራዊት ግንባታ ሂደት ልንመራባቸው እንደሚገባ አስቀምጠን ነበር። ሁሉንም እነዚህን አስተሳሰብ እዚህ መድገም አስፈላጊ አይደለም። በዛ ጽሑፍ እንደማጠቃለያ ሆኖ የተቀመጠ አንድ አረፍተ-ነገር ግን እዚህ መጥቀስ አሁን ሰራዊታችን እንደዛ ነው ያለው ወይ? ብሎ ለመጠየቅ ተገቢ ስለመስለኝ እጠቅሰዋለሁ። “We must create a citizen’s army. We must create a military which is loyal to and a servant of the people and which cannot be miss-directed to serve the interest of an elite or of those who might abuse their power. We must create an army which belongs to the people.” ያኔ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰባችን ገና ሳይበከል እያለ ነው ያስቀመጥነው፣ አሁንስ ምን አይነት ሁኔታ ነው ያለው?
እንደእኛ የመሰለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ሽግግር በሚደረግበት ኢኮኖሚው ኋላቀር የሆነና ብዙሃነት በበዛበት አገር የሚገነባ የአገር መከላክያ ሰራዊት ለሕገ- መንግስታዊ ሥርዓቱ ግንባታ አጋዥ እንዲሆን ከተፈለገ ከማንኛውም የፓርቲ፣ የጎሳ፣ የኋይማኖትና የፖለቲካዊ ወገንተኛነት በጸዳ መልኩ ሥራው መስራት ይኖርበታል። ይህ መርህ ከተጣሰ እና ሰራዊቱ እንደተቋም በሚመሩት መሪዎች ወገንተኛ በሆነ ፖሊቲካ ውስጥ የሚገባ ከሆነ የዴሞክራዊያዊ ሥርዓት ግንባታ ያሰናክላል ብቻ ሳይሆን ለአገር ውድቀትና ብተና ምክንያት ይሆናል።
የአገር መከላኪያ ሰራዊት በአገሪቱ በሚደረጉ ፖሊቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ጣልቃ እየገባ ተጽዕኖውን የሚያሳርፍ ከሆነ በሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱ ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተጽእኖ ከባድ ይሆናል። ለዚህ ነው የሰራዊት አጠቃላይ አቅም በስቪል መዋቅሩ ካሉት ሌሎች አካላት የበለጠ እንዳይሆን ጥንቃቄ መደረግ ያለበት። የሰራዊት ቁጥር አስፈላጊ ከሆነ በላይ እንዳይበዛ፣ በጀቱ ከአገሪቱ አቅም ተመጣጣኝ እንዲሆን፣ የገንዘብ አወጣጡ የደረጃው ቁጥጥር እንዲደረግበት በህዝብ በተመረጡ በሲቪል ባለስልጣናት ሙሉ ቁጥጥር ውስጥ እንዲገባ ወዘተ የሚደረገው።
እዚህ አንድ ማንሳት የምፈልገው ጉዳይ የሀገርን በኢንዱስትሪ ዕድገት ለማፋጠን የሚደረገው እንቅስቃሴ በዋናነት በጄኔራሎች የሚመራበት መንገድ አይገባኝም፡፡ በተለምዶ ሜቴክ እየተባለ የሚጠራው አደረጃጀት በሀገሪቱ ያሉትን የሃይል ማመንጫ፣ የስኳር ፋብሪካ፣ የባቡር ሃዲድ ስራዎች እንዲሰራ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ እነዚህ ስራዎች ሃገር ውስጥ ቢሰሩ ጥሩ ነው፡፡ ግን ለምን በጄኔራሎቹ ቁጥጥር ስር ይሆናሉ? በሀገር መከላከያ ውስጥ የሚገኝ ቴክኒካል ብቃት ካለ ታንክን፣ አውሮፕላን፣ ተሽከርካሪዎችን፣ የመገናኛ መሳሪያዎችን ወዘተ ይጠግን ብቃት ካለውም ይፈብርክ፡፡ ከዚህ በላይ ብቃታቸው ተፈላጊ የሆኑ የሰራዊት አባላት ካሉም በሲቭል መዋቅሩ ውስጥ ገብተው ስራውን ይስሩ፡፡ ምንም እንኳን በህግ ራሱን የቻለ አወቃቀር ያለው ቢሆንም አሁን ከሀገር መከላከያ ጋር ያለው ቁርኝት ግን አላስፈላጊ ነው እላለሁ፡፡
ይህ ግዙፍ በጀት ያለው አደረጃጀት በህግ አውጭው አካል ተጠያቂ እንዳይሆን የሀገር የብሄራዊ ደህንነት ጉዳይ እየተባለ የሚሸፋፈን ነገር እንዲኖረ ስለዚህም ተጠያቂነት የሌለው ብክነት እንዲኖር ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ስራ በመስጠትና በመከላከል በሀገሪቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ መቅረት ይችል የነበረ አላስፈላጊ ተፅዕኖ ፈጣሪ ይሆናል፡፡ ይህ በድምር ደግሞ የሀገር መከላከያው ተቋም በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ሂወት ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖይጨምራል፡፡ እንደ መርህ ግን ወደ ተደላደለ ዴሞክራዊያዊ ስርዓት በሚደረግ ሽግግር የሀገር መከላከያ ሃይል በጠቅላላው በሕብረተሰቡ ያለውን አላስፈላጊ ተፅዕኖ የመፍጠር አቅም መቀነስ ነው መሆን ያለበት፡፡ አሁን በሀገራችን ያለው ሁኔታ ይህንን መርህ የተከተለ አይደለም፡፡
አንድ አገር ሉአላዊነቱን ጠብቆ ህዝብ በመረጠው ህገ-መንግስታዊ ሥርዓትና የአኗኗር ዘይቤ ያለምንም የውጭ አገር ኋይሎች ተጽእኖ እንዲመራ በማስቻል የአገር መከላኪያ ሰራዊት እጅግ ከፍተኛ ድርሻ ያለውን ያህል ከዚህ በላይ መስመር አልፎ በአገሪቱ ውስጣዊ ፖሊቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወት ጣልቃ እየገባ ተጽእኖ የሚያሳድርና ለመምራት የሚከጅል ከሆነ ደግሞ በሕገ-መንግስታዊ ስርዓት ግንባታ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ የኖረዋል። በሕገ-መንግስት ዴሞክራዊያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ ያለ አገር ይህንን ከሰራዊት ሊመጣ የሚችለውን አሉታዊ ተጽእኖ መቃወምና መቆጣጠር ይገባዋል። ይህ ካልሆነ በሥርዓቱና በአጠቃላይ የአገሪቱ ቀጣይ ህልውና ከፍተኛ አደጋ ሊደቅን ይችላል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይ አንዳንድ ዘረኛ የሆኑ አስተሳሰቦች ጎላ ብለው ሲነገሩና በአገራችን የህዝቦች መነሳሳት ሲበራከት የትግራይ ተወላጆች፣ የጸጥታ ኋይሉ በአጠቃላይ፣ የመከላከያ ሃይሉ ደግሞ በተለይ እንደመከታ የማየት አዝማምያ ይደመጣል። በነሱ አነጋገር መከላክያ ተጠናክሮ የሀዝብ መነሳሳቱን እንዲቆጣጠርና አገሩን “እንዲያረጋጋ” ፍላጎታቸውን ይገልፃሉ። ይህ የተለየ የተሻለ አማራጭ የመፍትሔ ሀሳብ ከማጣትና በችግሩ ከመጨነቅ የሚመጣ ይመስልኛል፤ ግን ደግሞ ችግሩ ያባብስ እንደሆነ እንጂ አይፈታውም፡፡
በመከላክያ ሃይል ጣልቃ ገብነት የሚጠበቅ የትግራይ ህዝብ መብት ይሁን ጥቅም የለም። ቀደም ብሎ የነበሩ ገዢ መደቦች የፈጸሙትን ስህተት ለመፈፀም ከቃጣን ደግሞ አንችለውም። እነሱን እንኳን ከትግራይ ህዝብ የበዛ ህዝብ፣ የበለጠ ሀብት፣ የተሻለ ተሞክሮ፣ የተሻለ የተማረ የሰው ኋይል ይዘው አልቻሉትም፣ ምክንያቱም አስተሳሰቡ አድሀሪ ስለሆነና ህዝብ ለመጨቆን የሚቃጣ ስለሆነ አይቆምም።
ከላይ የሚታዩት የሰራዊት አዛዞች የትግራይ ተወላጆች በርከት ብለው ቢታዩም ሰራዊቱ የኢትዮጵያ ህዝቦች ስብጥር ነው። በዚህ አካል ውስጥ ወገንተኛ የሆነ ፖለቲካዊ አቋም ከተያዘ ራሱን ተቋሙን ከውስጥ ለማፍረስ እንደወሰነ መታወቅ አለበት። በተቋም ያሉት አባላት የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ልጆች ስለሆኑ በየብሔር ብሔረሰቦቻቸው ተከፋፍለው ተቋሙ ይፈረካከሳል። ይህ ደግሞ ሰበቡ እጅግ ከፍተኛ ነው። የአገር መከላክያ ሰራዊት የአንድን አገር ሉአላዊነት ጠብቆ አንድ አገር እንዲሰራ ከሚያስችሉት ተቋማት ዋናው ምሰሶ ነው። እዚህ ተቋም ውስጥ የሚመጣ መፈረካከስ አገሪቱ በሙሉ ይዞ ነው የሚፈረካክሰው። ስለዚህ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይጠይቃል። ዋነኛው የጥንቃቄ እርምጃ ደግሞ እንደ ተቋም ወደ ወገንተኛ ፖሊቲካ (የብሔር፣ የፓርቲ፣ የኋይማኖት ወዘተ) አለመግባት ነው። ሕገ-መንግስታዊ ተልእኮውን ብቻ መፈጸም ነው። ስለዚህ የመከላክያ ሃይል በማጠናከርና በፖለቲካዊ ጫዋታ ውስጥ እንዲገባ ማሰብ በእሳት እንደመጫወት መሆኑ መታወቅ አለበት።
ከዚህ በተጨማሪ ግን እንደው ድንገት ይህ ጉዳይ ተሳክቶ ሰራዊቱ አገሪቱን ለጥቂት ጊዜ ቢያረጋጋ፣ ውለታ ፈጽሚያለሁ የሚለው ሰራዊት ወይ እራሱ ንጉስ ይሆናል /ደርግ እንዳደረገው/ ወይም አንጋሽ ይሆንና የአገሪቱ ፖሊቲካ ወታደሮቹ በሚፈልጉት መንገድ ያምሱታል። የፈለጉትን ይሰቅላሉ፣ ያልፈለጉትን ያወርዳሉ፤ በዚህ ሂደት አገር ሰላም፣ መረጋጋት፣ ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚባል ነገር ታጣለች። ወታደሮቹ እንደፈለጉ ይፈነጩባታል። ይህ ደግሞ አስርት አመታት ወደ ኋላ መመለስ ነው። ይህን የሚመኝ ንጹህ ህሊና ያለው ዜጋ ያለ አይመስለኝም።
በአጠቃላይ በጸጥታ ኋይሎች ጣልቃ ገብነት የሚፈታ የፖሊቲካ ችግር በኢትዮጵያ ውስጥ የለም። የጸጥታ ኋይሎች በተለይ የአገር መከላክያ ሰራዊት ጥሩ ውጤት የሚያመጣው የትክክለኛ ፖሊቲካ ተቀጥያ፣ የትክክለኛ ፖሊቲካ ማስፈጸሚያ ሆኖ ሲያገለግል ነው። በአጭሩ ሕገ-መንግስቱ ያስቀመጠለትን ተልእኮ ሲፈጽም ብቻና ብቻ ነው። ይህ ደግሞ በብዙ በዚህ ጉዳይ ከፍተኛ ምርምር ያደረጉ ሊቃውንት ተነግሮ ያደረ ጉዳይ ነው።
የመፍትሔ ሃሳቦች
ከላይ እንደተገለፀው ሃገራችን በከፍተኛ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ነው ያለችው፡፡ ይህ ቀውስ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን መሠረት በማድረግ፣ በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚያስችል ፓለቲካዊ ሂደት በቅርብ ጊዜ ካልተጀመረ አገራችን እንደ አንድ ህልውናውና ሉዓላዊነቱን የጠበቀ ሀገር ለመቀጠል አዳጋች በሚሆንበት ሁኔታ ላይ እንደርሳለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ የዚህ አሁን አገራችን የምትገኝበት ፖለቲካዊ ሁኔታ ዋናው ምክንያት ደግሞ በትንሹ በህገ መንግስቱ የተቀመጡትን ሰብአዊና ፖለቲካዊ መብቶች መተግበር አለመቻል ነው፡፡ መፍትሄውም ሰፊ ዲሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ በመፍጠር መጀመር አለበት፡፡ በህገ መንግስቱ ዕውቅና የተሰጣቸውን ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተግባር ላይ በማዋል የሚጀመር ፖለቲካዊ ሂደት ዋና አላማው ዲሞክራሲያዊ ምህዳሩን በማስፋት ህዝብ በመንግስት ላይ ሊኖረው የሚገባውን የመቆጣጠር አቅም መጨመር፣ ተአማኒነት ያለው አስተዳደር ለመመስረትና፣ ከዚያም በኋላ ህገ መንግስታዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓቱ ጥልቀትና ስፋት እየጨመረ፣ እየጎላበት የሚሄድበትን መደላድል ማመቻቸት ይሆናል፡፡
አሁን ሀገራችን ካለችበት ቀውስ ለመወጣት በህገ መንግስቱ የተረጋገጡትን ሰብአዊና ፖለቲካዊ መብቶችን ያለምንም መሸራረፍ ተግባር ላይ በማዋል ሁሉም ፖለቲካዊ ሃይሎች ያለምንም ተፅዕኖ በሰላማዊ ፖለቲካዊ ውድድር የሚሳተፉበትን ሁኔታ በማመቻቸት መጀመር አለበት፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሕብረተሰቡ በሲቪክ ማህበራቱ ይህን በተናጠል በየግሉ በሚያደርገው ሰፊ ተሳትፎ፣ አሁን አገራችን ያለችበትን ፖለቲካዊ ቀውስ በሚገባ እንዲገነዘብ በማድረግ ፖለቲካዊ ተሳትፎውን ከፍ ማድረግ ይገባል፡፡ በሂደትም ህዝብ በመንግስት አሰራር ላይ ያለውን ተፅዕኖ የሚያሳድግበት፣ በሰፊ የህዝብ ተሳትፎ በሚመሠረት ፖለቲካዊ ስርዓትም ይበልጥ መተማመን የሚፈጠርበት፣ ቅሬታዎቹንና የሚያያቸውን ጉድለቶች ሳይሸማቀቅ የሚወያይበት፣ ከዚህ እየተነሳም መፍትሄ የሚያቀርብበት ፖለቲካዊ ሁኔታ መፍጠር አለበት፡፡ ከዚህ ጋር ጎን ለጎንም ህብረተሰቡ፣ ፖለቲካዊ አስተሳሰቡን ከሚስማማውና የሀገራችንን ፖለቲካዊ ችግሮች መፍታት ይችላል ብሎ በሚያምንበት ፖለቲካዊ ፓርቲ ስር በእምነት የሚደራጅበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት፡፡ ይህ ሂደት በጊዜ እየተጠናከረ፣ ሰላማዊና ዴሞክራዊያዊ በሆነ አግባብ ችግሮችን በመፍታት ቀውሱን ማስወገድ የሚቻልበት ሁኔታ እየጎላ መምጣቱን የሚያይበት፣ በመሆኑም በሕብረተሰቡና በፖለቲካዊ ሃይሎች መካከል መተማመን እየጠነከረ የሚሄድበት ሁኔታ መፍጠር ይገባል፡፡
በመጨረሻም ጊዜውንና ሕግን ጠብቆ በሚደረግ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ምልዓተ ህዝቡን ያሳተፈና ተአማኒነት ያላቸው ዓለም ዓቀፋዊ የምርጫ ታዛቢዎች የተሳተፉበት ምርጫ በማካሄድ ሕብረተሰቡ የሚፈልገውን ፖለቲካዊ ፓርቲ እንዲመረጥ ማስቻል ይገባል፡፡ የፖለቲካዊ ሃይሎችም በዚህ ሂደት የሚገኝን የምርጫ ውጤት በፀጋ የሚቀበልበት፣ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግም የሚስማሙበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡
ይህንን ሰፊ እንቅስቃሴ የሚጠይቅ በመጨረሻም በሚቀጥለው የምርጫ ዘመን የሚቋጭ ፖለቲካዊ ሂደት ለማስፈፀም በሀገራችን ካሉት የተለያዩ ፖለቲካዊ ፓርቲዎች ተስማምተው የሚቋቋሙት ይህንን ሂደት የሚመራ መዋቅር መፈጠር አለበት፡፡ ይህ ከፖለቲካ ፖርቲዎች ጋር በመስማማት የሚፈጠር አላማው ከላይ የተገለፁትን ሁኔታዎች ማሳካት የሆነ አካል ከመንግስት የዕለት ተዕለት ሥራ ተለይቶ ዋናው ስራው አሁን ያለውን ቀውስ በመፍታት ከላይ የተገለፀውን ምርጫ ማካሄድ ይሆናል፡፡ በዚህ ወቅት መንግስታዊ መዋቅሩ የመንግስት የዕለት ተዕለት ሥራ ሳይስተጓጎል ሲደረግ እንደነበረው ስራውን ይቀጥላል፡፡ ይህ ሂደት የታለመለትን ግብ እንዲመታና በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ በፍጥነት እስከ መጪው የምርጫ ግዜ ድረስ ከፍተኛ የፖለቲካ ስራ መሰራት አለበት ብዬ አምናለሁ።
እነዚህ ከላይ የተቀመጡትን አላማዎችና የመፍትሄ ሃሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ከመናገርና ከመፃፍ የዘለለ በርካታ ተጨባጭ ስራዎች መሰራት እንዳባቸው ግልፅ ይመስለኛል፡፡ ይህንን ሰፊ ስራ በተለያዩ ሞያ (Discipline) ዕውቀት ያላቸው ሰዎች መጀመሪያ ሃሳቡን በአግባቡ አደራጅተው ቢያስቀምጡትና ከዚህ የተነሳ ዝርዝር ዕቅድ መጥቶለት ቢተግባር የበለጠ ውጤት ይኖረዋል፡፡ ይህ የሚታሰበው እንቅስቃሴ ገዥው ፖርቲና እሱ የሚመራው መንግስትም ችግሮቹን በግልፅ እየተናገረና የመፍትሄ ፍላጎት ያለው መሆኑን እየገለፀ ስለሆነ በውስጡ ያሉትን ችግሮች (ችግሮቹን ለመፍታት የሚደረገውን እንቅስቃሴ የማይቀበሉ ሃይሎች እንደሚኖሩ ግልፅ ስለሆነ) ፈትቶ የችግሩ መፍትሄ አካል ይሆናል ከሚል ይነሳል፡፡
መፍትሄ ሃሳቦች አጠቃላይ ባህርይ ገዥው ፖርቲና ሌሎች የፖለቲካ ሃይሎች በጋር በህገ መንግስቱ የተቀመጡትን መብቶች በሙሉ ሳይሸራረፍ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር ይሆናል፡፡ የተጠቀሰውን ሁኔታ ለመፍጠር ምን መደረግ አለበት የሚለው ሃሳብ የፖለቲካ ሃይሎች ራሳቸው በሚያደርጉት ምክክር፣ መደራደር፣ ዝርዝር አካሄዱ የሚለወሰን ቢሆን ይመረጣል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አንዳንድ መታየት ያለባቸውን ጉዳዮች ለመጠቆም ግን እንደገና መታየት ያለባቸው ህጎች ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ የምርጫ ህግጋት፣ የሰላማዊ ሰልፍ፣ የሚድያ የፓርቲ ምዝገባ ወዘተ በጠቅላላ ህዝቡን አደራጅቶ በነፃ ሃሳቡን ገልፆ የፈለገውን የፖለቲካ ፖርቲ ተቀላቅሎ በፍላጎቱ እንዲመርጥ፣ ፖርቲዎቹም ሃሳባቸውን ተገቢው መንገድ በመንግስት ሚዲያም ጭምር ያለ ተፅዕኖ እንዲገልፁ፣ ከህግ አንፃር ሁኔታዎች ማመቻቸትና ተግባር ላይ እንዲውል ማድረግ፣
መልሶ መደራጀት ያለባቸው አካላት ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ የምርጫ ኮሚሽን፣ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የመንግስት ሚድያ Board ወዘተ፡፡ የጠቅላላ እንቅስቃሴው ውጤት የሚለካው በሕብረተሰቡ ውስጥ ከፍተኛ የመተማመን (confidence building) መንፈስ በመፍጠር ህብረተሰቡ በፖለቲካዊ ሂደት ትልቅ ተስፋ እንዲያሳድር በማደረግና በመጨረሻም ነፃ ዴሞክራሲያዊ መርጫ ተካሂዶ ውጤቱ ተአማኒነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ በማስቻል ነው፡፡
በዚህ ሂደት የፀጥታ ሃይሎች እንደሌሎቹ የመንግስት የስራ አስፈፃሚ አካላት ከማንኛውም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መግባት ሙሉ በሙሉ መቆጠብ ይኖርባቸዋል፡፡ ዋናው ስራቸው የሀገር ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የፖለቲካ ሃይሎች በጋር መድረካቸው የተሰማሙበት ማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ከማንኛውም የተጠቃ ሃይል (የመንግስት ይሁን የፖለቲካ ሃይሎቹ) የሚያሰማሩት የህዝቡን ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ለመገደብ ወይም የእንቅስቃሴውን ውጤት በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ተፅዕኖ ለመፍጠር የሚደረግ እንደቅስቃሴ መቆጣጠር አለባቸው፡፡
ማጠቃለያ
በኔ አመለካከት ሃገራችን ለመፍታት አስቸጋሪ ወደሆነ ፖለቲካዊ ቀውስ ልትገባ ትችላለች። ከዚህም አልፎ እንደ አንድ ሉአላዊነቷን ያስጠበቀች ሃገር ለመቀጠል የማትችልበት ደረጃ ልትደርስ ትችላለች ብዬ አስባለሁ። ይህንን ለማስቀረት የሚያስችል የመሰለኝ ሃሳብ አቅርብያለሁ፤ የኔ ሃሳብ ብቻ ነው ትክክል የሚል አቋም የለኝም። ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ ስለሆነ በሰለጠነ መንገድ የመንደር ስድቡና አሉባልታውን አስቀርተን በጉዳዩ ላይ እንነጋገርበት የሚል ሃሳብ አለኝ። ችግር መኖሩ መንግስት በግልፅ ያመነበት ስለሆነ ችግሩን መደበቅ አይቻልም። የችግሩ መንስኤዎች ምንድን ናቸው? እንዴትስ ይፈታሉ? በሚለው ሃሳብ ላይ ደግሞ የተለየ አስተሳሰብ ካለ (የመንግስት የገዢው ፓርቲ ይሁን የሌላ የፖለቲካ ሃይል) እንስማው። በአጠቃላይ አሁን ሃገራችን በምትገኝበት ሁኔታ ላይ ያለ ፍርሃት ሙሉ ዴሞክራስያዊ መብታችንን ተጠቅመን እንወያይበት።
በእኔ አመለካከት ይህ አሁን የሚታየው ፖለቲካዊ ችግር ከፖለቲካዊ ስርዓቱ አወቃቀርና የኢኮኖሚ ሁኔታው የሚነሳ ስለሆነ ስርዓታዊ (Systemic) ነው የሚል እምነት አለኝ። ስለሆነም ነው ኢህአዴግ ችግሩን እያየ እያወቀው እየተነጋገረበት እያለም ለመፍታት ያስቸገረው ብየ አምናለሁ። ለወደፊትም በገዢው ፓርቲ መዋቅርና ገዢው ፓርቲ በቀየሰውና በሚመራው የህዝብ እንቅስቃሴ ብቻ አይፈታም የምለው። ከገዢው ፓርቲ፣ ገዢው ፓርቲ ካዋቀረው መዋቅርና እሱ ከሚመራው የህዝብ እንቅስቃሴ በተጓዳኝና እኩል እንደሱ ሌሎች የፖለቲካ ሃይሎች ሕገ መንግስቱን መሰረት አድርገው የሚያደርጉት ሰፊ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ተጨምሮበት ነው ችግሩን መፍታት የሚቻለው የሚል እምነት አለኝ። የዚህ ሁሉ መቋጫው ደግሞ ነፃ፣ ፍትሃዊና በገለልተኛ ዓለም ዓቀፍና ሃገራዊ ታዛቢዎች ይህ መሆኑ የተመሰከረለት ምርጫ በማካሄድ ህዝብ የመረጠውን መንግስት ሲመሰረት ነው። ጉዳዩ ቀስ በቀስ እየተፈታ የሚሄድ ብዬ አምናለሁ። ህዝብ መንግስትን በተለይ የስራ አስፈፃሚውን መቆጣጠር ሲችል ነው አሁን እየታዩ ያሉ ችግሮች የመፍትሔ መንገድ የሚበጀላቸው ብየ አምናለሁ።
ዴሞክራሲና ነፃ የህዝብ ምርጫ በአንድ ወቅት ስልጣን ላይ ያለን ፓርቲ ፍላጎትና ምኞት ማሳክያ መሳርያዎች አይደሉም። ሕገ መንግስታዊ ዴሞክራስያዊ ስርዓት እፈልጋለሁ ብሎ ያመነ ፓርቲ ከዚህ ጋር አብሮ ሕገ ወጥ በሆነ የጉልበት መንገድ እኔን ብቻ እንጂ ሌላውን ፓርቲ እንዳትመርጥ ማለት የለበትም። ሕገ መንግስታዊና ዴሞክራስያዊ ስርዓት ሂደት ነው፤ ውጤት ደግሞ በህዝብ ፍላጎት የሚወሰን ነው። በአንድ ወቅት በስልጣን ላይ ያለ ፓርቲ የዴሞክራስያዊ ሂደት ውጤት ማሸንፍም መሸነፍም መሆኑ አውቆ፣ አምኖ ተቀብሎ መሄድና በዚህ መንገድ መስራት አለበት። አንድ ፓርቲ “ዘላለም” በስልጣን ላይ ለመቆየት የሚመኝ ከሆነ አስተማማኙ መንገድ ሕገ መንግስታዊ ዴሞክራስያዊ ስርዓት አይደለም።
**********
* ፀሐፊውን ሌ/ጄ ፃድቃን ገ/ትንሳኤ በtsadkanbayru@yahoo.com ማግኘት ይችላሉ፡፡
* ከዚህ ቀደም ከሌ/ጄ ጻድቃን ገ/ትንሳኤ ጋር ያደረግናቸውን ቃለ-መጠይቆች እና ምላሾች ለማግኘት ይህን ሊንክ ይጫኑ፡- General Tsadkan GebreTinsae
* ሌፍተናንት ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ ነባር የህወሓት ታጋይና አመራር ሲሆኑ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ኤታማጆር ሹም ሆነው አገልግለዋል፡፡ በዓለም ዓቀፍ ፖሊሲና ትግበራ በማስተርስ ዲግሪ እና በቢዝነስ አድሚኒስተሬሽን በማስተርስ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡