PBS: Escaping Eritrea … [Read More...] about ካብ ውሽጢ ቤት ማእሰርታት ኤርትራ
ከፍተን ብናየው? የሻዕቢያና የኦነግ መስተፋቅር
አስፋ ጫቦ (ዳላስ፣ ቴክሳስ) | undated | ኢትዮጵያ ዛሬ
እንደመግቢያ
ዛሬ ትንሽ መጻፍ የፈለኩት በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና በኢሳይያስ አፈወርቂ መካከል ያለውን የቆየ ጥብቅ ትስስር በመጠኑ ለመፈተሽ ነው። መነሻ የሆነኝ እንግሊዝ አገር ሎንዶንና አሜሪካ፤ አትላንታ፣ ጆርጂያ የኦሮሞ “ምሁራንና ብሔርተኞች” ያደርጉት ስብሰባና የሰጡት መግለጫ ነው። ያ ራሱን ችሎ መነገር ያለበት ስለሚመስለኝ እመለስበታለሁ። የዚህኛው ዓላማ እዚያ ሰበሰባ ላይ ተካፋይ ከነበሩት “ነፃ አውጭዎች” አንዱን ኦነግን በጨረፍታ ለመታዘብ ነው።
እዚያ ከመዝለቄ በፊት ኢሳይያስ አፈወርቂን ለመግባቢያ ያክል በመጠኑ መዳሰስ፤ ማየትና ማሳየት እሞክራለህ።
ብዙ የአፍሪቃ መሪዎች (ፕሬዝዳንቶች) “የዕድሜ ልክ ፕሬዚዳንት” (President for Life) የሚል ማዕረግ ነበራቸው። እኔ ወድጄዋለሁ! በየአራት ወይ ስድስት ዓመቱ ምርጫ እየተባለ ጊዜም ገንዘብም ከሚባክን “ወደዳችሁም ጠላችሁ የራሳችሁ ጉዳይ” ብሎ እቅጩን መናገርን የመሰለ ነገር የለም። ከዚያ ውስጥ አንዱ፤ ጂን ቤዴል ቦካሳ (Jean-Bédel Bokassa)፤ የመካከለኛ አፍሪቃ ሪፐብሊክ “ንጉሠ ነገሥት! (Emperor) ሆኖ አረፈው። እሱም እውነቱን መናገሩ ነበር። አንድምታውን ወዲያ ትተን “የዕድሜ ልክ ፕሬዚዳንትም ማለት ያው ንጉሠ ነገሥት ማለት አይደል!?” ማለቱ መሰለኝ።
ይህ ነገር የኛው የነበረውን፣ አሁን የጎረቤት “አገር”፣ “ፕሬዚዳንት” የሆነውን ኢሳይያስ አፈወርቂን አስታወሰኝ። “የኛው የነበረውን” ያሰኘኝ የደሴ ልጅ መሆኑ፤ የቀደማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ ተማሪ የነበረ መሆኑ፤ ከሁሉም በላይ ጣሊያን ኤርትራ ብሎ የሰየማት የባህረ ነጋሽ ልጅ መሆኑ ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ተረት፣ ትንግርት (Mythology) ተብሎ የሚነገረው አብዛኛው የተሸመነው ባሕረ ነጋሽ ነውና። የዚህ፣ ጣሊያን ኢትዮጵያን የወረራት ዘመን፣ 1928 ዓ.ም.፣ የተመሠረተው የ“ጥቁር አንበሳ” ጦር ጠቅላይ አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል በላይ ኃይሌለአብም ኤርትራዊ ነበር። የጥቁር አንበሳ ሕገመንግሥት አንቀጽ አንድ “ሕዝበ ኢትዮጵያ ንሰአ ወልታ ወኩናት ወተንስእ ውስተ ረደትየ“ ይላል። የአቶ ታደሰ ሜጫን “ጥቁር አንበሳ” መጽሐፍ ያነቧል። የአቶ ሐዲስ አለማየሁን ትዝታ ማንበብም ስለሌተናል ኮሎኔል በላይ ኃይሌለአብም ያለንን የበለጠ ያጠነክረዋል። የትዝታ ፈለግ በሚለው መጽሐፌ ውስጥ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለነበረው መለስ ዜናዊ የጻፍኩትን ግልጽ ደብዳቤ ማንበቡም የተሻለ የሚያብራራው ይመስለኛል። (ይኸ እግረ መንገዴን መጽሐፍ ማሻሻጤ ይሆን?) አባቱ፣ አቶ አፈውርቂም የመቀሌ ማዘጋጃ ቤት ሠራተኛ አልነበሩም? በልጃቸው ምክንያት ተጠርጥረው ታስረው ኖሮ፤ ”አባት በልጁ ምክንያት አይታሰርም!” ብሎ፣ ለመንግሥቱ ኃይለማርያም ነግሮ ያስፈታው የደኅንነት ሚኒስትር የነበረው ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደሥላሴ አልነበረም? የግንኙነታችንን ጥልቀት ለማስታወስ ያክል ነው። ያ ጥልቀት የማታ-ማታ አጓጉል ሆኖ አረፈ ለማለትም ነው!
ኢሳይያስ አፈወርቂን ያክል ለረዥም ዘመናት ንጉሠ ነገሥት ኹኖ የቆየ መሪ አፍሪቃ ውስጥ አሁን ያለ አይመስለኝም። ኃይለሥላሴ ነበሩ። እሳቸውም ባልጠበቁት መንገድ “ነበሩ!” ሆኑ።
ኢሳይያስ የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን አቋርጦ በረሃ ገባ። ሸፈተ። ከ50 ዓመት በፊት ነው። ጀበሐ ErItrean Liberation Front (ELF) ሆነ። ጀበሐን በላ! ሻዕቢያን (EPLF) ፈጠረ! ከዚያ በኋላ ያልሆነው ነገር የለም። የሆነው ሁሉ እንኳን እኔ እሱም ሳይጠፋው አይቀርም።
****
ከፍተን ብናየው!
ኢሳይያስ አፈወርቂን በአካል ያየሁት ነሐሴ 1981 ዓ.ም. አፍሪቃ አዳራሽ ወያኔና ሻንጣ ተሸካሚዎቹ አዲስ አበባ ገብተው ባዘጋጁት “የሠላምና ዲሞክራሲ ጉባዔ” ላይ አፍሪቃ አዳራሽ ነበር። ነገሩ፣ ማለትም ስብሰባው ሠላምንም ዲሞክራሲንም ለመቅበር መሆኑ አሁን ቁልጭ ብሎ ይታየኛል። ያኔ ጥርጣሬ ብቻ ነበረኝ።
ያዘጋጁት፣ ወይም ከመጋረጃው ጀርባ ሆነው ያዘጋጁት ፖል ሔንዝ (Paul Hanze) እና ኸርማን ኮኽን (Herman Cohn) ይመስሉኛል። ፖል ሔንዝ የዝነኛ የሲ.አይ.ኤ. (CIA) ሰላይ ነበር። የነመለስ ዜናዊ የነፍስ አባት (Godfather) ነኝ ብሎ የጻፈውን አንብቤያለህ። ኮኽን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር (State Department) የአፍሪቃ ጉዳይ ሚኒስትር ነበር። አሁን ደሞ ስለኢትዮጵያ ሲያላዝን ሰማሁት። አዲሱ ጭምብል (Mask) መሆኑ መሰለኝ።
ሁለቱም የረዥም ጊዜ የሥራ ውጤታቸውን ለመመረቅ አዲስ አበባ መጥተው ነበር። ፖል ሔንዝ ሊያገኘኝ ፈልጎ ሰው ቢልክብኝ “ይቅርብኝ! አልኩት። ኮኽንን ግን ብሔራዊ ቤተመንግሥት (ኢዩቤልዩ ይባል የነበረው) ግቢ ከመለስ ዜናዊ ጋር ለብቻቸው ፈንጠር ብለው ሲነጋገሩ ጣልቃ ገብቼ አነጋገርኩት። መለሰ ዜናው በዐይኑ ሊገስጸኝ ሞክሮ ነበር። አንዳንድ ሰዎች ተግሳጽም አይገባቸውም መሰለኝ። እዚያ ውስጥ ሳልመደብ የምቀር አይመስለኝም።
ሌላ ስለ ፖል ሔንዝ ትዝ የሚለኝ አሜሪካ የመጣሁ ሰሞን ካላገኘሁት ብሎ የሕግ ትምህርት ቤቱ መሥራችና የዩንቨርስቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት በነበሩት በዲን ፓል በኩል ቢጨቀጭቀኝ፤ እሳቸውም “ሊረዳህ የሚችል ሰውኮ ነው! ብቻ ጠንቀቅ በል!” ብለውኝ ላገኘው ቢሮው ተቀጣጠርን። ሔንዝ ሥራው ዋሽንግተን ዲ.ሲ. Rand Corporation የሚባለው ግዙፍ የስለላ ማቀነባበሪያ ኩባኒያ ውስጥ ነበር። ምሳ ሊጋብዘኝ እምድር ቤት ይዞኝ ወርዶ የመጀመሪያው ጥያቄ “ከየተኛው ጎሣ (Tribe) ነህ?” የሚል ነበር። ገርሞኝ “አልገባኝም!” አልኩት። “እንደምታውቀው ኢትዮጵያ ሁሉም ጎሣ አለውና …” ሲለኝ “ያንተስ?” አልኩት “እኔማ አሜሪካዊ ነኝ!” አለኝ “እኔም ኢትዮጵያዊ …!” በዚህ ፈግጠው! ፈግጠው! ተባብለን ምሳዬንም ሳልበላ ተለያየን። የነፍስ አባቴ (Godfather) ሊሆን ፈልጎ ይመስለኛል። ይኸው ሳልጠመቅ ተለያየን!
ይኸኛው ነገርን ነገር ያነሳዋል መሆኑ ነው።
***
በዚህ “የሠላምና ዲሞክራሲ” የአፍሪቃ አዳራሽ ስበሰባ የኢትዮጵያ ጉዳይ በሦስት ቀን ተጠናቀቀና አራተኛው ቀን ለኤርትራ ተመደበ። ይህ ከመሆኑ አንድ ቀን በፊት ለቡና እረፍት ተደርጎ የነበረ ጊዜ የቢ.ቢ.ሲ. (BBC) ተወካይ የነበረ ላስት (Last) የሚባል ጋዜጠኛ አገኘኝና “ምስኪን አሰፋ እንዴት ታሳዝናለህ” (Poor Assefa I pity You!) አለኝ። ከአንድ ወር በፊት Ominibus በሚባል የቢ.ቢ.ሲ. ፕሮግራም ለተላለፈ ቃለ መጠይቅ አድርጎ “ምስኪን እስረኛ!” ብሎ ገንዘብ ብጤም ሰጥቶኝ የነበረ ነው። “ምን ሆኜ ነው የማሳዝነው?” አልኩት። “ይህንን ሦስት ቀን ሙሉ የኦሮሞ ነጻ አውጭ ድርጅት (ኦነግ) ከእናንተ ጋር ያሉ መስሎህ ስትዳክር!” አለኝ። “ታዲያስ?” ስለው “ሎንዶን ለተዘጋጀው ስበሰባ ከመሔዳቸው በፊት ወያኔ ሻዕቢያና ኦነግ ኤርትራ፤ ተሰነይ ከተማ ተሰብስበው የመጨረሻውን ውሳኔ ሁሉ ተስማምተው ነው የመጡት። ከእናንተ ጋር ሳይሆን ኦነግ ከወያኔና ከሻዕቢያ ጋር ነው የወገነው!” አለኝ። ጨስኩ! ሌሎችም ለሦስት ቀን ግራ አጋብተውኝ የነበሩት ጭብጦች ፍንተው ብለው ታዩኝ። ስበሰባው እንደገና እንደተጀመረ በኦነግ ተወካዮች፣ በማውቃቸው ወዳጆቼና በኔ ስር ሆነው ይሠሩ በነበሩት ላይ ፈነዳሁ። ከኔ ፍንዳታ ይልቅ ጎልቶ ትዝ የሚለኝ የሲዳማው የአቶ ወልደአማኑኤል ዱባለ ነበር። ጣቱን ኦነግ መቀመጫ ላይ ሰትሮ “ትላንት ለምኒልክ ዛሬ ደግሞ ለትግሬዎች ሸጣችሁን!” አለ። ይህ ሁሉ በወቅቱ በድምጽም በምስልም የተቀረጸ ስለሆነ አጥኝዎች ቢፈልጉት ሊያገኙት የሚችሉ ይመስለኛል።
ይህ ኢሳይያስ አፈወርቂን በተጨማሪ መነጽር እንድምለከተው ሌላ ቀዳዳ ከፈተልኝ!
ከዚያም የስብሰባው ሊቀመንበር የነበረው አቶ መለስ ዜናዊ የኢሳይያስ አፈወርቂን ንግግር በጥሞና እንድናዳምጥ መመሪያ ሰጠንና ተዘጋጅቼ ማዳመጥም መመልከትም ጀመርኩ። መጀመሪያ ልብ ያልኩት የኢሳይያስን አቀማመጡንና የሰውነቱ አያያዝ (Body Language) ነበር። የተቀመጠው በቀኝ በግራው በሰዎች ተከቦ ወጣና ጎላ ያለ ወንበር ላይ ነበር። የተኮፈሰና የሚኮፈስ (Preposterous and pompous) መሰለኝ። ፊታቸውን አኮሳትረው፣ “ትንፍሽ ትይና ወዮልሽ!” የሚል መልክ ይዘው ክፍል የሚገቡ አንዳንድ አስተማሪዎችን አስታወሰኝ። ከዚያ ንግግሩን በትግሪኛ ጀመረ።
የመጀመሪያው ወደ አማርኛ አስተርጓሚ ዶክተር በረከት ሀብተሥላሴ ነበር። ዶክተር በረከት ሀብተሥላሴን አውቀዋለህ። በንጉሡ ዘመን እዚሁ አፍሪቃ አደራሽ የቀደሞሙ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ማኅበር (Alumni Association) ያዘጋጁት ስብሰባ በረከት ተናጋሪ እኔ አዋኪ ሆነን ተለያይተናል። ሕግ ትምህርት ቤት ነበርኩ። ከትላንትና ወዲያ ሲያገኘኝ “አስፋ እንደገና አፍሪቃ አዳራሽ ተገናኘን!” አለኝ። “ልክ ነው! ሆኖም በተለያየ በር ነው የመጣነው!” አልኩትና ተሳሳቅን። የመጀመሪያ አስተርጓሚው በረከት ነበር ብያለሁ። አንድ አምስት ደቂቃ አንዳስተረጎመ ኢሳይያስ “አልቻልክም!” ብሎ አስወገደውና በሌላ አጠር ባለ ሰውዬ ተካው። ይህ አጠር ያለ ሰው አንድ 7 ደቂቃ አስተረጎመና “አልቻልክም!” ተብሎ ተወገደ። የዚያን ጊዜ መለስ ዜናዊ፣ ከወዲያ ማዶ ከሊቀ መንበርነቱ ወንበር እጁን አውጥቶ “እኔ አስተረጉማለሁ!” አለና ተፈቅዶለት! ቀጠለ! አንድ አራት ደቂቃ እንዳስተረጎመ “አልቻልክምና!” ተብሎ ተወገደ። አራተኛ ሌላ ሰው መጣና የኢሳይያስ ንግግር ተፈጸመ። የተጨበጨበ መሰለኝ። ልብ አላልኩም! እኔ ልቤም ማስተዋሌም ያተኮረው ኢሳይያስ አፈወርቂና እዚህ አሳዛኝና አስቂኝ ቲያትር (Tragic Comedy) ላይ ነበር። ከይዘቱ ይልቅ ቅርጹ ላይ!
አስቂኝነቱ ቀርቶ አሳዛኝነቱ ጎልቶ የሚወጣው ይህ ሁሉ የሚደረገው “የጋራ ቤታችን!” ላይ መሆኑ ነው!
የኔ የማኅበራዊ ገፆች (Facebook etc) ወዳጆቼ (Friends) በአብዛኛው ወጣቶች ስለሆኑ ዶክተር በረከት ሀብተሥላሴን ላያውቁት ይችላሉ። በረከት የሐረር ልጅ፤ የግዕዝ ሊቁ የአለቃ ሀብተሥላሴ ልጅ ነው። ስለዚህም የቤተክህነት ትምህርትም አለው። እንደአለቃ ለማ እንደመንግሥቱ ለማ! ማለት ነው። ዶክተርነቱ በሕግ ከእንግሊዝ አገር ነው። እንግሊዝ ልከው እንዲማር ያደርጉት ኃይለሥላሴ ነበሩ ተብሏል። የሐረር ልጅ ናቸውና! አባቱንም ያውቃሉና!
በረከት በንጉሡ ዘመን የኢትዮጵያ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ነበር። ሕግ ትምህርት ቤትም ያስተምር ነበር። መጀመሪያ ያየሁት ለዓለም አቀፍ ዝምታ ፍርድ ቤት (International Moot Court Competition) የሕግ ተማሪዎች የማጣሪያ ወድድር ስናደርግ ከፈረንጆች ጋር ዳኛ ኹኖ የመጣ ጊዜ ነበር። በደርግ ዘመን ደግሞ የመርማሪ ኮሚሽን ሊቀመንበርም ሆኖ ነበር። ሊቀመንበር እያለ ነው ሻዕቢያን የተቀላቀውና አማካሪ የሆነው። ስለሻዕቢያም ስለኢትዮጵያም መጻሕፍት ጽፏል። ከዚያ ሁሉ በኋላ ኢሳይያስ ሌላው ይቅርና ለአስተርጓሚነት እንኳን አትበቃም ብሎ እዳሪ ጣለው።
በረከት ሀብተሥላሴ ተምሳሊት (Template) የሚሆን ይመስለኛል። የአስቆሮቱን ይሁዳንም ያስታውሰኛል። ወንጌሉ እንደሚለው ይሁዳ ጌታውን የሸጠበትን ሰላሳ ብር አልበላባትም! አልጠጣባትም! ይልቁንም ራሱን ሰቀለ! ገንዘቡም “ራሱን የገደለ ገንዘብ ለሌላ ጉዳይ አይሆንም ብለው የመቃብር ቦታ ገዙበት። “አልቄዳ” የሚባለው ነው። የደም መሬት! ወያኔ ይህንን “የደም መሬት!” ትዕይንት አድርጎት አቅርቦታል ልበል? ጎበዝ! ጠንቀቅ ነው ደጉ!
እንዳልኩት በረከት አገርን ለከዱ፤ ለሚከዱ ሁሉ ተምሳሊት (Template) የሚሆን ይመስለኛል!!
ለመሆኑ ኢሳይያስ አፈወርቂ ያንን ሁሉ አስተርጓሚ “አልቻላችሁም!” የሚለው ምኑን ነበር? ትግርኛውን አይመስለኝም! ወይም በኔ ደረጃ ያለ ትግሪኛ አትረዱም ማለት ይሆን? አማርኛ አትችሉም ነው? ይህን ማለት ደግሞ ኢሳይያስ አማርኛ ማወቅ ብቻ ሳይሆን እስኪያርም ጠንቆቆ ያውቃል ማለት ይሆናል። ወይም “ማን አለኝ ከልካይ!” መሆኑን በዚህ መድረክ ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ሊያስመሰክር ይሆን? ወይም ይህ መሪያችሁ ነኝ የሚለውን መለስ ዜናዊን እንኳን እንደመሪ ከመጤፍም አልቆጥረውም የሚል መልዕክት ለኢትዮጵያ ሕዝብ መላኩ ይሆን? ወይም ማንንም ምንንም በአደባባይ ለማዋረድ ብቃትና እወቀት ያለኝ ሰው ነኝ እወቁልኝ ይሆን? በዚያም በዚህ ብትሉ የኔን ያክል አዋቂ ቀርቶ እኔ የምለውን፤ የምናገረውን መረዳት የሚችል እንደሌለ እዩልኝ ነው?
የሥነልቡና አዋቂዎች (Psychaitrists) ምን ይሉ ይሆን? በሽተኛ መሆኑን ይቀበላሉ! የበሽታውን አይነት ምን ይሉት ይሆን? አንዳንዱ የአንጎል፣ የአዕምሮ፣ የሕሊና ሕመም ታክሞ የማይድን ነው ይሉታል። ለምሳሌ Sciopath የሚሉት! “እቡይ!” እንደማለት! “እቡየ ዐይን ወስሱሀ ልብ ኢይትሀወር ምስለየ” ይለዋል ዳዊት።
በኢሳይያስ ንግግር ወቅት በኔ ጭንቅላት፣ በኔ ሕሊና፣ በኔ አዕምሮ የሚተራመሱት ይህንና ይህንን የመሳሰሉ ጥያቄዎች ነበሩ።
አሁን የኢሳይያስንና የኦነግን የቆየና “የፀና” ግንኙነት በዘመን ረድፍ ለማስቀመጥ እሞክራለሁ።
- በዘመነ ደርግ በድርቅ ከተጠቁ የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለየም ከወሎ ሠፋሪዎች አሶሳ ሰፈረው ነበር። አንድ ምሸት የሰፈሩበት መንደርም፣ ሠፋሪዎች ጭምር በጥይትና በእሳት ጋዩ። ይህንን ያደረገው የሻዕቢያና ኦነግ ሕብረት ነበር። መንገድ መሪ ኦነግ መሆኑ በወቅቱ በሕዝብ መገናኛዎች እስኪሰቀጥጥ ተነግሯል። የሚገርም ሌላም ነገር አለ። አሶሳ ወለጋ ክፍለ አገር ውስጥ ይሁን እንጅ፤ ኦሮሞም የኦሮሞ መሬትም አልነበረም! አይደለምም! “ነፃ አውጭ” ነን ቢሉ እንኳን ኦሮሞን እንጅ ቤኒሻንጉልን አይደለም። ሌላው የሚገርመው በወቅቱ የኦነግ መሥራችና መሪ ባሮ ቱሙሳ ምኒልክ ግቢ ከደርግ ጋር እየሠራ ነበር። ከምዕራብ ኢትዮጵያ ወለጋ ነፍሰ ገዳይ ፍለጋ ኤርትራ በረሃ ድረስ ምን ወሰዳቸው? የሃሳቡ አመንጭ ኦነግ ነው ወይስ ሻዕቢያ? ጭካኔ የነጻ አውጭነት አንደኛው ባሕርይ ነው?
- የሚቀጥለው የተሰነይ ስብሰባ ነው። መለሰ ዜናዊ፣ ኢሳይያስ አፈወርቂና ሌንጮ (ዮሐንስ) ለታ በአንድ ግንባር ስር ሎንዶን ለመጓዝ እንደተስማሙ የሚያሳይ የሚጨባበጡበት ፎቶግራፍ በድረገጾች ታይቷል። ምን ነበር የመገናኛና የአንድነት መሠረቱ (Point of Convergance)? ነጥባቸው? ኢትዮጵያን በሚመለከት ማለቴ ነው!
- የሎንዶኑን ስብሰባ ያዘጋጀው የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር (State Department) ነበር። ኸርማን ኮኽን እዚያው ነበር። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ ዲንቃ ጠቅላይ አቃቤ ሕጉን ቢልልኝ ማንደፍሮንና ዶክተር ግርማ ወልደሥላሴን ጨምሮ ሎንዶን ደርሰዋል።
- ስለኢትዮጵያ መልዕከተኞች ጉዳይ የአቶ ተፈራ ኃይለሥላሴን The Ethiopian Revolution መጽሐፍ ማንበቡ ጥሩ ነው። አቶ ተፈራ በወቅቱ በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለነበር የታዘበውን ጽፏል። “ለስደት ቤተሰቦቻቸውን ይዘው መጡ እንጅ ለውይይት አልነበረምም! አይመስልምም” ይላል። እንዳለውም አቶ ተስፋዬና ቢልልኝ ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ወደ አሜሪካ አመሩ። እዚያም ሲደርሱ እነ ዶከተር ግርማን ጣጥለው ወደሚሔዱበት ሔዱ። እኔ መጀመሪያ ዋሺንግተን ዲ.ሲ. ያገኘሁት ዶክተር ግርማን ነበር። “አሰፋ እኔ ያደረጉኝን ያድርጉኝ እንጂ ወደኢትዮጵያ እመለሳለሁ!” እንዳለው ተመለሰ። ከንክኖኝ አንዳንድ ነገር ለመጠየቅ የሚሠራበት የዓለም ባንክ ቢሮ ሔጄ አቶ ተስፋዬ ዲንቃን አነጋገርኩ። ጸሐፊው ቡና አመጣችልኝና ጠጥቼ ብዙም ሳልጠይቅ ወጣሁ። “ለመሆኑ ምንና ምኑ ይጠየቃል?” ብዬ መሆን አለበት!
- የሎንዶኑ ስብሰባ፣ ስብሰባ ካልነው፣ የአሜሪካን መንግሥት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ከፈጸመው ታላላቅ ደባዎች ውስጥ ቀዳሚነት የሚኖረው ነው። ሌላው ሶማሌ ወራን ድሬዳዋ ልትገባ ስትገሰግስ የጦር መሣሪያ ማዕቀብ በኢትዮጵያ ላይ መጣሉ ነው።
- የሎንዶኑ ስብሰባ ሌላ ትልቅ ምስልም ነበረው። መንግሥቱ ኃይለማርያም ከነቤተሰቡ ዚምባቡዌ እንዲሰደድ፣ ጄነራል ተስፋዬ ገብረኪዳን ፕሬዚዳንት እንዲሆንና የኢትዮጵያን ጦር ሠራዊት “እጅህን ለወያኔ ስጥ!” እንዲል፣ መለሰ ዜናዊ፣ ሥዩም መስፍንና ጓደኞቹ በሱዳን የፀጥታ ጉዳይ ሚኒስትር ጄነራል አልፋቲህ አርዋ በሚነዳ አውሮፕላን አዲስ አበባ እንዲገባ፣ እነሌንጮም የተሰጣቸው “የቤት ሥራ” በትክክል እንዲወጡ ማድረግ የአሜሪካን መንግሥት የተቀነባበረ ሥራ ነበር። የረዥም ጊዜ ሴራ ውጤት ነበር!!
- በትክክል ሥራ ላይ ማዋሉን ለመከታተል አዲስ አምባሳደር ባስን (Baas) አዲስ አበባ በአስቸኳይ ላኩ። የነፍስ አባትየው (The Godfather) ኸርማን ኮኽንም የድል ምሸቱ ላይ ለመገኘት አዲስ አበባ መጣ። አምባሳደር ባስም ኢትዮጵያን እስክለቅ ድረስ ብርቱ ወዳጄ ኹኖ ሰንብቷል። ሁለት የአሜሪካን ሴናተሮች ለጉብኘት መጥተው ኖሮ ለነጻነታቸው በዓል July 4th 1991 አሜሪካን ኤምባሲ የጋበዘው ኢትዮጵያዊ እኔና ባለቤቴን ብቻ መሆኑን አስታውሳለሁ። የፖል ሔንዝ ተልዕኮ አይነት የሚያጣ አይመስለኝም!
- ለዚህ የሠላምና ዲሞክራሲ ስብሰባ የመጣም፣ ያመጡትም፣ ደጅ ጠኝውም፣ የድል አጥቢያ አርበኛ ለመሆን ያኮፈክነውም መናኸሪያችን አዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል ነበር። ከወያኔና ሻዕቢያ በስተቀር! የወያኔ ጭፍሮቹ የት እንደሰፈሩ አላውቅም። ሻዕቢያ የሰፈረው የጄኔራል ተፈሪ በንቲ መኖሪያ የነበረው ነው ተባልኩ። ግራ የገባኝ የኦነግ አባሎች የት ደረሱ? የሚል ነበር። ስብሰባ ላይ ሳገኛቸው “እነዚህ ሰዎች ከኛ ነጠሏችሁ!” እላለሁ። በዚያ በስብሰባው መካከል የደቡብ ሕብረት ለመመሥረት ማታ ማታ እንነጋር ስለነበር እንዲገቡበት ፈልጌ ነበር። በኋላ የቢ.ቢ.ሲው ላስት ተሰነይን ሲነግረኝ ግልጽ ሆነልኝ። የኦነግ አባሎች፣ ሌላው ቀርቶ ከኔው ጋር ማዕከላዊ የነበሩት ጭምር ሰፈራቸው ከሻዕቢያ ጋር ጄነራል ተፈሪ በንቲ መኖሪያ የነበረው ሆኖ ተገኘ። እንዲህ አንድ ጡት ጠብቶ ያደጉ የሚያስመስለው ፍቅር፣ ሌሎቻችንን እንዲሸሹ ያደረገው ፍቅር፣ ከየት ወረደ? የሚያሰኝ ነበር። ምን ይሆን? የኢትዮጵያስ ይቅር እውነት የኦሮሞ መሠረታዊ ጥቅም ነው? ጫወታው ሌላ መሆኑ በጥቂት ወራት ታዬ! እመለስበታለሁ!
- ከአፍሪቃ አዳራሹ ስብሰባ በኋላ የሽግግር መንግሥትና የሽግግር ምክር ቤት ተቋቋመ። ለጥቂት ወራቶች የሽግግሩ ምክር ቤት አባል ነበርኩ። ኦነግ 8 መቀመጫዎች ነበሩት። በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መጠን ማለት ነው! አራት ሚኒስትሮችም ተሾሙ። ከዚህ ውስጥ ጎልቶ የሚታወሰኝ ምክር ቤቱ ውስጥ ሁለት የኦነግ ተወካዮች፣ ሌንጮ ለታና አብዩ ገለታ ሥራ ነበር። የኢትዮጵያን ብሔራዊ ሠራዊት አፍራሽ ኮሚቴ ሊቃነ መናብርት ሆኑ። የኢትዮጵያ ሠራዊት አይሉትም። “የደርግ ወታደር!” ይሉታል። ለማስረዳት ሞከርኩ። “ደርግ መንግሥት ነው። መንግሥት ሠራዊት የለውም። አገር ነው ሠራዊት ያለው። ከዚህም ሌላ ወንጀለኞች ቢኖሩ በማስረጃ ማረጋጋጥና መጠየቅ እንጅ የአገር ሠራዊት ይፍረስ ተብሎ አይታወቅም!” ከንቱ ጩኸት ሆነ።
- ቢቸግረኝ አንድ ቀን ሌንጮንና አብዩን ቡና ጋብዤ “ይህ ይፍረስ! ይፍረስ! የምትሉት ሠራዊት ኦሮሞኮ ነው። አሁን በደመወዝ መተዳደር የለመደ፤ ከግብርናውም የተፋታውን በትነን በጭፍን እስር ቤት መክተትና ለማኝ ማደርግ …” አልኩኝ። ”ማነው ኦሮሞ ነው ያለህ?” “ይህማ ግልጽ ነው! አንደኛ ሠራዊቱ አብዛኛው የተመለመለው ከደቡብ ነው። ከዚህም ሌላ በኢትዮጵያ ኦሮሞ አብላጫ ቁጥር አለውና …”፤ አልሰሙኝም! ሊሰሙኝም አልፈለጉም! አይችሉምም! እነሱ የወያኔ ጉዳይ አስፈጻሚ እንጅ ባለጉዳይ አልነበሩም! ብቻ የኢትዮጵያ ሠራዊት ፈርሶ ወደ ልመናና ወደስደት ተዳረገ! መፍረሱ አይቀሬ ነበር! ባለጉዳዩ ቢያፈርሰው! የዚያን ዘመን የምክር ቤት ውይይት ያዳመጠ አፍራሹ ኦነግ መሆኑን ያያል። ተመዝግቦ የተቀመጠ ነው!
- የትምህርት ሚኒስትር ኹኖ የተሾመው ኢብሳ ጉተማ ነበር። ሀ ብሎ ያረቀቀው አዋጅ ኦሮምኛ በላቲን ፊደል እንዲጻፍ ነበር። ወዳጄ ስለነበረ ቢሮው ሔጄ “ኢብሳ አብደሀል እንዴ! ኦሮሞን ወደቅኝ ግዛትነት ልትመልሰው ነው!?” አልኩኝ “እንዴት?” ቢለኝ “ቅኝ ግዛት የነበሩት ሁሉ የሚጽፉት በላቲን ፊደልና የሚናገሩትም እሱኑ ነው!” አልኩኝ። የሆነ የነፍጠኛ ደጋፊ የሚል ቀልድ ሲያመጣ “ይህ የአማርኛ ፊደል የአማራ ፊደል አይደለም! የመጀመሪያውና ብቸኛው የጥቁር ሕዝብ ፊደል ነው! ልንኮራበት ይገባል …” አልኩት። አልሆነምና የሆነው ሆነ!
- ምክር ቤቱ ውስጥ የኢሕአዴግ አባል የሆነ “የኢትዮጵያ መኮንኖች ግንባር” የሚባል ባለ 8 መቀመጫ ድርጀት ነበር። ምርኮኛ የነበሩ መኮንኖች ማለት ነው። አንድ ሁለት ሦስት ቀን ያክል ምክር ቤቱ ውስጥ አላያቸውም። አንድ ጥዋት ቡና እረፍት ላይ ሥዩም መስፍንን “ሥዩም እነዚህ መኮንኖቻችን አላያቸውምሳ?” አልኩት። ከት ብሎ ስቆ “አቶ አስፋ ሚናቸውን ጨርሰው ተሸኝተዋል!” አለኝ። “ታዲያ 8ቱ መቀመጫ ምን ይሆናል?” አልኩት። ”ወያኔ ወስዶታል!” አለኝ። ሌላ ጥያቄ ከመጠየቄ በፊት ሔደብኝ።
- የኦሮሞ ነጻነት ግንባርም ልክ የመኮንኖቹ ደረሰባቸው። ታህሳስ ይሁን ጥር 1982 መመሪያ ተሰጣቸው። “ከዛሬ ጀምሮ ምክር ቤቱ ውስጥ ያላችሁን ድርሻ ፈጽማችኋል! ከዛሬ ጀምሮ ከኢትዮጵያ ምድር እንድትወጡ! ካልወጣችህ ወህኒ ቤት ትወርዳላችሁ! ምርጫውን ለእናንተው እንተዋለን!” ተባሉ። ከተሰጣቸው ሁለት ምርጫ ኢትዮጵያን ለቀው መውጣትን መረጡ። አህያ የተጫነችውን ታደርሳለች እንጅ አትበላውም! እንዲሉ።
- ከወያኔ ጋር አዲስ አበባ እንደገቡ አሁን “የኦነግ ተዋጊ ኃይል ነው የምትሉትን ሁሉ ከነመሣሪያው ጦር ካምፕ አስገቡ!” ተባሉ። በታዘዙት መሠረት አስገቡ። ከአገር ቤት መውጣት ወይ እስር ቤት ምርጫ ሲሰጥ እነዚህ ጦር ካምፕ ውስጥ በቁም እስረኝነት ያስረከቡት ተዋጊዎች ደረጃ ወደሙሉ እስረኝነት ተሸጋገር። እጃቸውን ራሳቸው ላይ አድርገው በሴት ወያኔ ወታደሮች እየተነዱ እስር ቤት ወረዱ። እስከዛሬ ዕጣ ፈንታቸው ምን እንደሆነ፣ ከምን እንደደረሰ የጠየቀም፣ ያስረዳም የለም!
ኦነግ፣ ኢሳይያስ አፈወርቂና የአትላንታ ስብሰባ
- የአትላንታ፣ ጆርጂያ የኦሮሞ “ምሁራንና ብሔርተኞች” ስብሰባ አንድ ግብ አስቀምጧል። “የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ለነጻነት የሚበቃ፤ እንደኤርትራ፤ ትግሬና ደቡብ ሱዳን መሆን አለበት!” ይላል። ጎበዝ! “ቸር ተመኝ! ቸር እንድታገኝ!” ይባላል። ፈረንጅ ደግሞ “ለከዋክብቱ አነጣጥር ብትስት እንኳን የባህር ዛፉን አናት ትመታለህ!” (Aim to the Stars! If you miss, You Will Hit the Top of the Tree! ይላል። ኢሳይያስ መላው ዓለም ማዕቀብ አድርጎበት፣ ከዛሬ ነገ የዓለም ጦር ፍርድ ቤት ይቀርባል እየተባለ የሚባንን ጉድ ነው። ወያኔ እንደሚታየው ጣዕረሞት ላይ ነው። የደቡብ ሱዳን የሚባለው አገር የከሸፈ አገር (failed State) ነው ወይስ አገር ነው? እየተባለ ነው። በቃላት እንኳን ቢሆን ለዚህ ለታላቁና ገራ-ገሩ የኦሮሞ ሕዝብ ከዚህ የተሻለ አድማስ መቅረጹ በተገባ ነበር። የአትላንታውን ስብስብ አድማስ መፈለጊያ መነጥር መሰለኝ። የተሻለ መነጽር ባይኖር ወይ መግዛት ወይም መዋስ በተገባ ነበር።
- ወያኔ “ከኢትዮጵያ ጥፉ!” ብሎ ካባረረ ከ1982 ጀምሮ ኦነግ ብዙ የውስጥ ትርምስ የገጠመው ይመስለኛል። አንዴ ስለታዘብኳቸው ዝርዝሩን ብዙም አልከታተልም። “ወትሮም የኦሮሞ ሳይሆን የአንድ መንደር ሥልጣን ፈላጊዎች ጥርቅም ነበር!” በሚል ማን ይምራ ማን የሚል ትርምስ የተፈጠረ ይመስለኛል። አብዩ ገለታ ዋሽንግቶን ዲስ የነበሩትን የኦነግ ልጆች ቢሮ ነጥቆ “እኔን ሹም!” አለ። አንድ ቀን በአካባቢው ነበርኩና ልጠይቀው ቢሮ ሔድኩ። ልክ ለኢሳይያስ እንዳልኩት ተኮፍሶ ጠበቀኝ። የዚህ የምክር ቤቱንና የማባረሩን ጉድ ያነሳብናል በሚል ፍርሐት በሩን መዝጋቱ መሰለኝ። ሥራ የበዛበት ለማስመስል ብዙ አስጠበቀኝ። በኋላ ቢሮው ስገባ የጄነራል ታደሰ ብሩን ፎቶግራፍ በትልቁ ግርግዳው ላይ አየሁና፣ ፈገግ አልኩኝና “እኒህ ደግሞ ማናቸው?” አልኩት። ገርሞት “አታውቃቸውም እንዴ? ጄነራል ታደሰ ብሩ ናቸው!” አለኝ። ”ኦነግ ነበሩ እንዴ?” አልኩት ጄነራል ታደሰ ብሩ ኦሮሞን ለማስተማርና ንቃተ ሕሊናውን ከፍ ለማድረግ የጀመሩት ጥረት ተጣሞ ተተርጉሞ የታሰሩ፣ በኋላም በአሳሳቾች ለአጉል ወሬ የተዳረጉ፤ ጀግና ኢትዮጵያዊ ነበሩ።በስም መነገድ የሚባለው የዚህ አይነቱ ይሆን?
- ሌላው የኦነግ ቅርንጫፍ የተከፈተው ኤርትራ፣ አስመራ ነበር። መሪዎች ነን የሚባባሉት የተፈራረቁ ይመስለኛልና በሙሉ አላውቃቸውም። አሁን ካሉት፣ ወይም አለን ከሚሉት አንዱ ኦቦ ዳውድ ኢብሳ ነው። በኢትዮጵያ የተቀጣጠለውን የኦሮሞ ሕዝብ አመጽ የምመራው እኔ ነኝ የሚል መግለጫ ባለፈው ወር ሰጥቶ አንብቤ ድፍረቱን አደነኩ። ዳውድ ኢብሳ እንደአንዳርጋቸው ጽጌ ኢሳይያስ የማይጠረጥረው የኢሳይያስ ታማኝ ነው። ታማኝ መሳሪያ ነው አላልኩም! አሁን ለመሳሪያነት ብቁ ሆኖ አልተገኘም! በንግድ ሥራ ተሠማርቶ መካካለኛው ምስራቅ ይመላለሳል። አሥመራ ውስጥ ቆንጆ መኪና ከሚነዱት ውስጥ አንዱ ተስፋዬ ገብረአብ ነው። ያችን መኪና ለተስፋዬ የሸጠው ዳውድ ነው።
- የአትላንታው ስብሰባ ለዳውድ ልክ በወያኔ ቋንቋ አንድ “ኮማንድ ፖስት” ሰቶታል። የምዕራብና የምስራቅ ኮማንድ ፖስት ይለዋል።
- ሌላው የደቡብ ኮማንድ ፖስት፣ ቦረናን፣ ባሌንና አርሲን የሚያጠቃልለው ኮማንድ ፖስት አዛዥ ጄነራል ከማል ገልቹ ነው። ከማል ገልቹ በምርኮኝነት ተይዞ፣ ኦፒዲኦ የሆነ የወያኔ ሰው ነበር። እስከ ዛሬ ሦስቴ ከድቷል ማለት ነው! ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በሽ-በሽ የሆነ ነገር ቢኖር ዶክተር መሆንና ጄነራል መሆን ዋንኛ ይመስለኛል። ከማል ገልቹም “ጄነራል ኹን ተባለ ጄነራልም ኾነ!” የምንለው ነው። “ብርሐን ይሁን አለ ብርሐንም ሆነ!” መጽሐፍ እንዲል። የአርሲ ልጅ ነው።
- ከማል ገልቹ አሁን አምባሳደር ነው። የኢሳይያስ አፈወርቂ አምባሳደር ኹኖ ለተልዕኮው ምሥራቅ አፍሪቃ ከተላከ ሰንብቷል። በአርሲ አካባቢ እንቅስቃሴ እንዲያደረግ ነው የተላከው። ይህ የአትላንታው ጉባዔ የሰጠውን ኮማንድ ፖስት ማጠቃለሉን እርግጠኛ አይደለሁምና አጣራለሁ።
- ከማል ገልቹ ዩጋንዳ ከመላኩ በፊት ታማኝነቱን ለማረጋገጥም፣ አንድ የበላይ አካል ተቆጣጣሪም ስለሚያስፈለገው ኢሳይያስ አንድ የሻዕቢያ ጄነራል ልጅ ድሮለት ሚስቱም አብራው ሔዳለች። ለተጨማሪ ጥንቃቄ ሲባል፣ ከማል ገልቹ ሳያውቅ፣ የከማል ገልቹን አንድ ልጅ ከኢትዮጵያ አስመጥቶ በመያዣነት አስቀምጦታል። ልጁ መያዣ መሆኑን ከማል ገልቹ አይውቅም ነበር። አሁን ማወቅ አለማወቁን እርግጠኛ አይደለሁምና አጣራለሁ።
- እንግዲህ ከዚህ ተነስተን የግድ መድረስ ያለብን ድምዳሜ ያለ ይመስለኛል። ሁሌም 2+2=4 ነውና! ይህም፣ ከማል ገልቹና የአትላንታ ስብስብ በአንድ “ኮማንድ ፖስት” ይመራሉ ማለት ነው። ያ ከሆነ ደግሞ “የኮማንድ ፖስቱ” ጄነራል ሳሞራ የኑስ ሳይሆን ጄነራል ኢሳይያስ አፈወርቂ መሆኑ ነው። ከዚህም ሌላ የአትላንታው ስብሰባ ኢሳይያስ አፈወርቂን እንደፈር ቀዳጅ የትግል ተምሳሌት (Role Model) አድርጎ ተቀብሎታልና! ይህ በጽሁፍ ማስረጃ የተደገፈ ነው ማለት ነው። ይሰውረን!
- ከዚህ ሌላ ኢሳይያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ ላይ ካደረጋቸው ደባዎች ጥቂቶችን፤ የምታውቋቸውን ልጠቃቅስ። የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)ን መሠረተ እንኳን ማለት ባይቻል የኢትዮጵያን አየር መንገድ አውሮፕላን አምስት ጊዜ አስጠልፏል። አለቃቸው የነበረው ክፍሉ ታደሰ ”ያ ትውልድ” በሚለው መጽሐፍ ገልጾታል።
- በብርሃነ መስቀል ረዳ የሚመራው የኢሕአፓ ሠራዊት ከሻዕቢያ ጋር በመሆን ለሁለት ዓመት የኢትዮጵያን ጦር ወግቷል። ”ይድረስ ለባለታሪኩ” የሚለውን እዚያው የነበረውን፣ የተስፋዬ መኮንንን መጽሐፍ ማንበብ ነው።
- ብርሃነ መስቀልንና ጓደኞቹን አሲምባ ያስገባው የካቲቲ 25፣ 1967 የኢትዮጵያ የገጠር መሬት የታወጀ ዕለት ነው። ስላቁ ደግሞ እነብርሃነ መስቀል መሬት ላራሹ እያሉ ወይም እያስመሰሉ ሲዘምሩና ሲሰማሩ የነበሩ መሆናቸውና መሬት ለአራሹ የሆነ ዕለት አሲምባ መግባታቸው ነበር።
ለማጠቃለል
- ይህ ነገር የራሱ እግር አውጥቶ አልጠቃለል ብሎኛልና በግድም ቢሆን መቆም ያለበት ይመስለኛል። ከፈለኩት በላይ ረዘመብኝ።
- ኢሳይያስ ይህንን ለምን ያደርጋል? ነው። ከሕመሙ ሌላ፣ በረከት ሀብተሥላሴን አስተርጓሚ አትሆንም ይበለው እንጅ ምክሩን ተቀብሎታል። የዶክተር በረከት ምክር፣ መጽሐፍ የጻፈበትም፣ኢትዮጵያ የምትባል አገር በሠላም ከኖረች ኤርትራ ጠንካራና ታይዋን አይነት ልትሆን አትችልም ነው። አሁን ያንን ወያኔ ወደማሳካቱ ተቃርቧል። ከማል ገልቹ አምባሳደርም የሆነው ለዚሁ እቡይ ተልዕኮ ነው።
- ዋናው ዋናው፤ በጣምም የሚያሳዝነኝ የኦነግ ጉዳይ ነው። ኦሮሞ “ኦሮሚያ” የሚባል አገር መሥርቶ “መንግሥት ይሁን!” እንኳን ቢባል ከራያና አዘቦ አንስቶ እስከባምባሲ መሬት ወይም መሬታቸው ያደረጉት አላቸው። አኩሪና ዝነኛ ታሪክ ያለው ላለፈው 600 ዓመታት ብዙ ዝነኛ የኢትዮጵያ ነገሥታትም የጦር መሪዎችም ያፈራ ታላቅ ሕዝብ ነው። ይህንን፣ የዚህን ሕዝብ ስምና ዝና አንግቦ ሻንጣ ተሸካሚ፤ ደጋግሞ ሻንጣ ተሸካሚ መሆን፣ ሕዝቡን የሻንጣ ተሸካሚነቱ አካል፣ አምሳል ማድረግ የሕዝቡን ክብር ዝቅ ማድረግ ወይም የራስን የታመመ የሥልጣን ጥማት ቅድሚያ መስጠት ይመስለኛል።
- መውደድን፣ ማፈርን፣ መናደድን፣ መኩራትን፣ መደሰትን ተፈጥሮ በተፈጥሮ ለሰው ልጅ የለገሰችው ስሜቶች ናቸው። እነዚህ የኦነግ መሪዎች ነን የሚሉት ይህ ጸጋ በተለይም ማፈር የሚሉት እንደተሰጣቸው እርግጠኛ ነኝ። ሊያስተውሉትና ሊፈልጉት ተግባራዊ ማድረግም ይገባቸዋል እላለሁ! ይገባልም!
- ይህንን የምናገረው እንደሰው ነው። ማንም ሰው ደሴት አይደለም No Man is an Island የሚለው የJohn Donne ግጥም የምወደውና የማምንበትም ነው።